የኢኮኖሚው እይታ በመቶ ቀናት ውስጥ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ መንበረ ስልጣናቸው በመጡበት ወቅት የመጀመሪያ ንግግራቸውን ሲያደርጉ ሁላችንም ከመቀመጫችን ብድግ ብለን በጭብጨባ ተቀበልናቸው፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ ቢሉ በአገራችን የሰፈነውን የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ላይ ያላቸው አቋም በወቅቱ ተከስቶ ለነበረው አለመረጋጋት እልባት ይሰጣሉ ተብሎ ስለተገመተ ነው፡፡ እኝህ ሰው በመልካም ንግግራቸው የመላ ኢትዮጵያውያንን ቀልብ ስበዋል፡፡ ከዚህ መልካም ንግግራቸው መካከልም አንድነት፣ ፍቅር፣ ይቅርባይነትና መደመር የፊት መስመር ተሰላፊ መፈክሮቻቸው ናቸው፡፡ እነዚህ መፈክሮች በአንድ ላይ ሲዋሃዱ ደግሞ መሰረት የሌለው የዘር ፖለቲካ ውስጥ አይነተኛ መድኃኒት እንደሚሆኑ ተገምቷል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶች የኢኮኖሚውን እድገት ወደ ኋላ እንዳይጎትተው ስጋትን አሳድሯል፡፡ ምክንያቱም ሰላም ከሌለ ገበያ የለም ገበያ ከሌለ ደግሞ እድገትና ልማት የለም፡፡ ከሰላም ውጭ ንግድ አይታሰብም፡፡ በመሆኑም በአገር ላይ ትልቅ ኪሳራን ይጋርጣል፡፡ ሰላም ለኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡

ከአገራት ጋር ሰላም ሲወርድ የጦር መሳሪያ ወጭ ስለሚቀንስ ኢኮኖሚን በመልካም ሀኔታ ያራምዳል፡፡ ከአንድ ወር በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ያበሰሩት ነገርም ለኢኮኖሚው ተስፋ ሰጭነቱ የራሱ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ “በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የነዳጅ ድፍድፍ የሙከራና ውጤቱን የምናይበት ቀን ነገ ነው እሚሆነው፤ እስካሁን ባለው የቅድመ ጥናት ሙከራዎች ከፍተኛ እምቅ ሀብት መኖሩ ተረጋግጧል” ብለዋል፡፡ እንደ ነዳጅ ያሉ የተፈጥሮ ሃብቶች አግባብ ባለው መልኩ ጥቅም ላይ ይዋሉ እንጂ በመቶ ቀናት ውስጥ ብስራቱ መሰማቱ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ተስፋ ሰጭ ሆኗል፡፡ ምክንያተም ለሚደረገው የዕድገት ጉዞ ራሱን የቻለ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡

የአገሪቱ አምራች ኢንዱስትሪ የሚጠበቅበትን የውጭ ምንዛሬ ማምጣት ተስኖት አለመረጋጋትም ተጨምሮበት የውጭ ምንዛሬም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡ ፋና ቴሌቬዥን እንደዘገበው ከሆነ ዘላቂ መፍትሄ አይሁን እንጂ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ሁለት ቢሊዮን ዶላርን በኢትዮጵያ ለሚደረግ  የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አንድ ቢሊዮን ዶላር ደገሞ የውጭ ምንዛሬ ለማቃለል በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ይህ ከሆነ ከሳምንታት በኋላ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ተሰብስቦ የወለድ ምጣኔ ከፍ አለ ወይስ ዝቅ አለ የሚል የሚተራመስ የገበያ ዓይነት ኢትዮጵያ ውስጥም በጥቁር የውጭ ምንዛሬ ገበያው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ታይቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እንዳሉት “የዶላር ምንዛሬ በተወሰነ ደረጃ ቀንሷል፤ ሰምታችሁ ከሆነ አዳዲስ ዶላሮች እየገቡ ስለሆነ በጥቁር ገበያ የያዛችሁ ሰዎች በፍጥነት በባንክ ገበያ እንድታወጡት ካልሆነ እንናንተም ችግር ውስጥ ስለሚያስገባ ታሳቢ አድርጉ” የሚል ምክር አዘል መልዕክት ተናገሩ፡፡ ከዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በኋላ ይመነዘርበት የነበረው የጥቁር ገበያ ዋጋ 36 ብር ወደ 29 ብር ከሃምሳ ሳንቲም በመግዛታቸው የምንዛሪያቸው ተመን ወደ ባንኮች ተመን እየተጠጋ ነው፡፡ ይህ የሚያመለክተው ደግሞ በጥቁር ገበያው የሚገዛው ሰው ቀንሷል የሚለውን ነው፡፡ በሌላ በኩል ለጥቁር ገበያው ምንዛሬ የሚያቀርበው ሰው ቁጥርም ወርዷል ማለት ነው፡፡ ይህ አገሪቱ ለተያያዘችው የለውጥ ጉዞ መልካም ዜና ሆኗል፡፡ ስለሆነም በዘላቂነት ከታገዘ ለኢኮኖሚው ዕድገት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ውስጥ መግባቱ የአገሪቱ ዕዳ 26 ቢሊዮን ተሻግሮ ከፍተኛ የሚባል ጫና ላይ መግባቱ በሌላ በኩል ደገሞ የምጣኔ ሀብት አፈፃፀምን ከፍ ማድረግ ማስፈለጉ ትልቅ ውሳኔን አገሪቱ እንድትወስን ሆነች፡፡ ባለፉት መቶ የዶክተር ዐቢይ የሥራ ቀናት በመንግስት እጅ ያሉት ሆቴሎች፣ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክና የተለያዩ የማምረቻው ዘርፍ ኢንዱስትሪዎች በግንባታና አገልግሎት  በመስጠት ላይ ያሉትንም በሚያካትት መልኩ በየደረጃው ወደግል የማዘዋወር ውሳኔ ተላልፏል፡፡

በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ወደ ግሉ ዘርፍ እንዲተላለፉ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎችና የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ድርጅት ትልቁን ድርሻ መንግስት ይዞ ቀሪው አክስዮን ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች፣ በውጭ ለሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎችና ለሌሎች የውጭ ባለሃብቶች እንዲተላለፉ ተወሰኗል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህንን ተናገሩ “ላለፉት ሃያ ዓመታት በመንግሥት እጅ ተይዘው የቆዩ ትላልቅ የመንግሥት ኩባንያዎች የአገር ውስጥ ባለሃብቶች፣ ዲያስፖራዎች፣ በዘርፉም የላቀ ዕውቀት፣ ሃብት ያላቸው ኩባንያዎች የተወሰነ ድርሻ ገዝተው ገበያው የሚፈልገውን እውቀትና ሃብት ማፍሰስ ማስቻል ከልማታዊ መንግሥት የሚጠበቅ ተግባር ነው” ብለዋል፡፡

ስለሆነም ይህ ውሳኔ ትልቅ ውሳኔ ስለሆነ ይህ አደረጃጀት የተገኘውን የኢኮኖሚ ድርጅት ውሳኔ በአገራችን የተንሰራፋውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቀነስ፣ ያለውን የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ለመቀነስ ከፍተኛ ዕድል የሚሰጥ መልካም ዕድል ነው፡፡ ስለሆነም ይህንን መልካም አጋጣሚ በየደረጃው ያሉ አካላት ተገንዝበው በጋራ በመረባረብ ሁሉም ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ጥንቃቄ ይደረግበት እንጂ መልካም እርምጃ መሆኑን የካፒታል ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ የሆኑት አቶ ሙሉቀን ወንዶሰንና የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያው አቶ ጌታቸው አስፋው ለፋና ቴሌቨዥን እንዲህ ሲሉ  ተናግረዋል፡፡ “ይህ በአሁኑ ሰዓት እየታየ ያለው የኢኮኖሚ እድገት ማለትም ለባለሃብቶች አክሲዮን ማጋራት የዘርፉን ኢኮኖሚ እንደሚያሳድገው ምንም ጥርጥር የለውም የአየር መንገዱም እየሰፋ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ንብረትነቱ መንግስትም በጥንቃቄ ሊመለከት ይገባዋል፡፡  አክለውም መንግሥት ወጭ እንዲቆጥብ የውጭ ጉዞን ጨምሮ ብዙ ወጭዎች ገደብ እንዲጣልባቸው ተደርጓል፡፡ ይህ ተግባር ይሁን ሚያሰኝ ስለሆነ በትኩረት ቢሰራበት ጥሩ ነው” ብለዋል፡፡ ስለሆነም ሁሉም ተግባራት በጥንቃቄ ይያዙ እንጂ የመቶ ቀናቱ የኢኮኖሚ እርምጃ ለአገሪቱ ተስፋ ሰጭ መሆናቸው የብዙዎች ምስክርነትን አገኝቷል፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ “በአገር ውስጥ የተገኘን ሀብት ወደ ውጭ ማሸሽ አደገኛ ነው” ሲሉ የማሳሰቢያ መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም ይህን ሀብት ከአገር ማስወጣት የሚያስከትለው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ በመሆኑም ከእናት አገር እጅ ላይ አውጥቶ ለማን ለመስጠት እንደሆነ ሁሉም ዜጋ ቆም ብሎ ሊያስብ ይገባል፡፡ ስለሆነም ከአገር ውስጥ የተገኘን ሀብት ወደ ውጭ አገር ማሸሽ ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑን ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ዶክተር ዘላለም እጅጉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሁኔታውን አስከፊነት እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

“ በአገር ውስጥ የተገኘን ሀብት ከአገር ማሸሽ አንዱ የሙስና መገለጫ ሲሆን፣ በአገር ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ ያደርሳል” ይላሉ፡፡ ከዚህ ጋር አያይዘውም የአገሪቱን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ወደ ኋላ የሚጎትት በመሆኑም በመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ ከፍተኛ እንቅፋት ይፈጥራል፡፡ የጤና፣ የትምህርት ሥራ እንዲሁም መንግስት የቀረጻቸው ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ካፒታል እንደሚፈልጉ ዶክተር ዘላለም ይጠቅሱና ገንዘቡ ወደ ውጭ እንዲፈልስ ከተደረገ መንግስት ኢንቨስትመንት ለማካሄድ ይቸገራል፡፡

ይህ ደገሞ አገር ላይ ትለቅ አደጋ ይደቅናል፡፡ ምክንያቱም ለማምረቻ አገልግሎት የሚውሉና ከውጭ የሚገቡ በርካታ ግባቶችን ለማስገባት የግድ ካፒታል ይጠይቃል፡፡ ዶክተር ዘላለም እንዲህ ይላሉ “በገንዘብ ማሸሽ ሳቢያ ይህ ካፒታል እንደማይኖር በዚህ የተነሳም የአገልግሎት ዘርፉ እንደሚጓተት ይገልጻሉ፤ የመድሃኒት እጥረት እንደሚከሰትም በአብነት በመጥቀስ፣ ይህም ትልቅ ፈተና መሆኑን” ያብራራሉ፡፡ ይህ የዶክተር ዘላም ገለጻ በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን ሀበት ከአገር ማሸሽ ያለውን አደገኛነት በጉልህ የገለፁበት ሁኔታ ሀብት ለአንድ አገር ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው መረዳት ይቻላል፡፡

ብር በጆንያ ተሸክመው ወደ በዕዳን አገር የሚያደርጉት ጉዞ በአጭሩ እንዲገታ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ገንዘብ እንዲሸሽ የሚደረገው በህገ ወጥ መንገድ ነው፣ በተለይም ፍተሻው ጠንካራ ባልሆነባቸው የድንበር አካባቢዎች የማሸሹ ተግባር በስፋት ይፈፀማል፡፡ ከአውሮፕላን ማረፊያዎች ሳይቀር የማሸሽ ሙከራ ሲደረግ የሚያዝበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ይህን ገንዘብ የሚያሸሹትም አንዳንድ ባለስልጣናት ከነጋዴዎች ጋር በመወዳጀት ጭምር መሆኑ የችግሩን አሳሳቢነት ከፍ አንዲል አድርጎታል፡፡ ሆኖም ግን መንግስት ባደረገው የተቀናጀ የፍተሻ ስርዓት በርካታ ገንዘቦችና የጦር መሳሪያዎች ከአገር ሲወጡና ሲገቡ  በቁጥጥር ስር ለማዋል ችሏል፡፡

ከዚህ ህገ ወጥ ድርጊት ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህር የሆኑት አቶ ታምሩ ባልቻ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የችግሩን አሳሳቢነት እንዲህ ገልፀዋል፡፡ “ገንዘብ ማሸሽ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ምክንያቱም የውጭ ምንዛሬ በመጥፋቱ መድሃኒተ እንኳ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት እስከሚሳን ድረስ ፈተና ይሆናል፤ በዚህም የጤናውን ዘርፍ ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ያደናቅፋል፡፡ ለኮንስትራክሽን ግንባታ የሚሆኑ ግብዓቶች ባለመኖራቸው ምክንያት የቀን ስራ በመስራት ኑሯቸውን የሚገፉ ወንድሞችቻችንና እህቶቻችን ከስራ ውጭ በማድረግ የችግሩ ግዝፈት እስከ ግለሰብ ድረስ ዘልቆ ይሰማል” ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ይህ ሁኔታ ምን ያህል አሳሳቢ ችግር እንደሆነ በግልፅ ይስተዋላል፡፡ ምክንያቱም ይህ ገንዘብ ከአገር የማሸሽ ተግባር ኢኮኖሚውን በማዳከም ማንኛውንም ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ቁሳቁሶችን በመገደብ አገራዊ ኪሳራ ያስከትላል፡፡ ስለሆነም ባለሃብቱም ሆነ መንግስት የውጭ ምንዛሬ ካጣ ማንኛውንም ለጤናው፣ ለኢንቨስትመንትም ሆነ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የሆኑትን ቁሳቁሶችን ማስገባት አይቻልም፡፡

ይህ ደገሞ ማንኛውንም የህብረተሰብ ክፍል የሚጎዳ እኩይ ተግባር ስለሆነ እያንዳንዱ ዜጋ ሊታገለውና ገንዘብ የማሸሽ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት ለህግ አካላት በመጠቆም ከፍተኛ ቁጥጥር ለሚያደርገው መንገስት የበኩሉን ድርሻ መወጣት መቻል አለበት፡፡ ምክንያቱም ይህ ጉዳይ ለማንም የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ርብርብ የሚሻ ነው፡፡ ስለሆነም በእኔ ባይነት ስሜት አገራችን ለምታከናውነው ሁለንተናዊ የእድገት እንቅስቃሴ እቅፋት እንዳይፈጥርባት ኢትዮጵያ ለልጆቿ ድምጿን ከፍ ድርጋ ጥሪዋን አስተላልፋለች፡፡