ዲያስፖራው እያሳየ ያለው በጎ ምላሽ

ኢትዮጵያ የለውጥ ባንዲራን ማውለብለብ ከጀመረች ወራትን አስቆጥራለች:: በእነዚህ ወራትም በአገራችን በጣም ብዙ የለውጥ ሥራዎች እየተከወኑ ይገኛሉ። እነዚህ ለውጦች መምጣት የቻሉት መንግሥትና ህብረተሰቡ አብረው መስራት ስለቻሉ ነው። አሁንም እነዚህን  ያየናቸውን መልካም የለውጥ አቅጣጫዎች ለማስቀጠል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የየበኩሉን ግዴታ መወጣት ይኖርበታል።

ባሳለፍነው ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በ2011 ዓ.ም ረቂቅ በጀት ዙሪያ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ላይ አገራችን የጀመረችው የለውጥ ጅማሮ እንዲቀጥልና የተሻለች ኢትዮጵያን ማየት እንድንችል በውጪ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባስተላለፉት መልዕክት አብዛኞቹ ዲስፖራዎች ወደ አገር ቤት የሚልኩትን ዶላር በህጋዊ መንገድ በባንክ በኩል እንዲልኩ አበክረው አሳስበዋል። ይህን ያሉበት ምክንያት ለተለያዩ አገልግሎቶች ማለትም ለመድኃኒት፣ ለዘይትና ለመሳሰሉት ነገሮች መግዣ ዶላርን መመንዘር አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ 

ዲያስፖራዎች የሚልኩትን ዶላር በህጋዊ መንገድ በባንክ መላክ ከቻሉ በአገራችን የህገ ወጥ ተግባር ይቀንሳል። በተጨማሪም የታቀዱ ሥራዎችን በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ እንድናከናውን ያደርገናል ሲሉ በውጪ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸው ይታወቃል።

ኢትዮጵያ በጀመረችው ለውጥ እንድትቀጥልና በሁሉም አቅጣጫ የተሻለች አገር ተፈጥራ ለማየት፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩትን የመሰረተ ልማት ችግሮች ለመቅረፍ  ሁሉም በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በቀን ለማኪያቶ ከሚያወጡት ወጪ ላይ በመቀነስ አንድ ዶላር ለአገራቸው ማበርከት ቢችሉ ታላቅ አስተዋዕኦ ይኖረዋል። እንዲሁም ይህ ገንዘብ ተሰባስቦ  የህብረተሰቡን ችግሮች በመቅረፍ ሥራ ላይ ቢውል ትልቅ አገራዊ ውለታ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች በቀን አንድ ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ከተቻለ በወር 30 ሚሊዮን ዶላር ይገኛል ማለት ነው ብለዋል። ይህ ከሆነ አሁን በአገሪቱ ለብዙ ጊዜያት መፍታት ያልቻለውን የመሰረተ ልማት ችግሮች መቅረፍ ይቻላል ብለዋል።

ይህ ከዲያስፖራው ላይ የሚሰባሰበው ገንዘብ ትረስት ፈንድ በሚል የሂሳብ ቁጥር ተከፍቶ በመሰብሰብ ለንፁህ ውሃ አቅርቦትና ትምህርት መማር ላልቻሉ አካል ጉዳተኞች  እንደሚውል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ ዲያስፖራውም ይህንን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበለትን መልካም ጥሪ ተቀብሎ መልካም ምላሽ እየሰጠ ይገኛል። አሁን ላይ ይህንን ጉዳይ የሚያስፈፅሙ ኮሚቴዎችም ተዋቅረው ወደ ሥራ ገብተዋል።  

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የswift አድራሻ CBETETAA በመጠቀም በመላው አለም የሚገኙ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉትን ድጋፍ ወደ ትረስት ፈንዱ ገቢ ማድረግ እንዲችሉ ሁኔታዎችን አመቻችቷል። ይህ ተግባር  በአለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ ማህበራት አባላት በማሳተፍ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የታለመ ነው፡፡ 

የታቀደውን ገንዘብ ለማሰባሰብ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል 1000255726725 የሂሳብ ቁጥር ተከፍቶ  በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን  በቀን አንድ ዶላር ማስገባት ጀምረዋል። አንዳንዶችም የዓመቱን 365 ዶላር ማስገባታቸው እየተነገረ ነው። ይህ የሚያሳየውም በውጭ የሚኖሩ ዜጎቻችን አገራቸውን ለመርዳት ያላቸውን ቁርጠኝነትና ቀናነት ነው፡፡

በእርግጥም ዲያስፖራው ለአገሩ ያለውን ፍቅር በተለያዩ የድጋፍ ሰልፎች በመግለጽ በመሪው የቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ በመመለስ ታዛዥነቱን እያሳየ ይገኛል። ይህ ደግሞ አገሪቱ ለጀመረችው ለውጥ መፋጠን በእጅጉ ይጠቅማል። በዚህም በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተጣለባቸውን አገራዊ አደራ በመወጣት በአዲሲቷ ኢትዮጵያ መጪ ተስፋ ላይ አሻራቸውን ለማስቀመጥ ከወዲሁ መትጋት ይጠበቅባቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባሰለፍነው ሳምንት ወደ አሜሪካ ማቅናታቸው ይታወቃል። በዚያም ከበርካታ ኢትዮጵያውያን ጋር የመገናኘት ዕድል አግኝተዋል። በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያም ምክክር አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዲሲ በነበራቸው ቆይታ ከአክቲቪስት ታማኝ በቀለ  በጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዲያስፖራው  የቀረበውን በቀን አንድ ዶላር የአበርክቱልን ጥያቄ ተቀብሎ ይህንን መልካም ተግባር ወደ አሥር ዶላር በማሳደግ የማስተባበር ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ቃል ገብቷል።  

ይህ ከሆነ ሁሉም በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በቀን አስር ዶላር ለአገራቸው ማበርከት ከቻሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላር ለአገራችን ማስገኘት ይቻላል። ይህም ገንዘብ ለታቀደለት አላማ ሲውል አገራችን ከዚህ ቀደም ከምትታወቅበት ኋላ ቀርነት ተላቃ ለሌሎች ተምሳሌት የምትሆን  አገር ትሆናለች።

የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ባወጠው መግለጫ ላይ ሁሉም በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ይህንን መልካም ዕቅድ ስኬታማ ለማድረግ እንደሚረባረቡ ያለውን እምነት ገልጿል። በሁሉም የአለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን በማጠናከር የተሻለች ኢትዮጵያን በመገንባት የተጀመረውን መልካም የለውጥ አቅጣጫ ማስቀጠል ይገባቸዋል።