የበጎነት አርአያ

የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለአገርና ለህዝብ ያለው ፋይዳ የጎላ ነው። በዚህ አገልግሎት በጎ ፈቃድ የሚያበረክቱት ወገኖች በደን ልማትና በአካባቢ ጥበቃ፣ በአንጓዴ ልማትና በጽዳት በመሳሰሉት ተግባሮች በመሳተፍ አገራቸውንንና ህዝባቸውን ማገልገል ይችላሉ።

አገልግሎቱን የሚሰጡት ተማሪዎችና በማንኛውም የሙያ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ አካላት ናቸው። አገልግሎቱ ለአንድ ለተወሰነ ክፍል የተተወ አይደለም። በመሳተፍ ላይ ያለ ግለሰብ ላልተሳተፈው አቻው አርአያ መሆን ይኖርበታል። የአገልግሎቱ ድምር ውጤትም እያንዳንዱ ዜጋ ባለው አቅም አገሩንና ህዝቡን መደገፍ ነው።

ከዚህ ፅሁፍ አኳያ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሊሸፈኑ የሚችሉ ደን ልማትና አካባቢ ጥበቃን እንዲሁም አረንጓዴ ልማትን በአገራችን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ እንመለከታቸዋለን።

እንደሚታወቀው ሁሉ የአገራችንን የተጎዱ መሬቶች መልሶ እንዲያገግሙ ለማድረግ የተለያዩ ሀገር በቀል ዛፎችን መትከል ዋነኛው አማራጭ ነው። ለዚህም በርካታ የችግኝ ማፍያ ጣቢዎችን በብዛት መጠቀም ያስፈልጋል።

እዚህ ላይ የአካበቢ ጥበቃን የተሻለ ለማድረግ የተፈጥሮን ሥነ- ምህዳር ለመጠበቅ ከሚደረገው ርብርብ ባሻገር፤ የዕለት ተዕለት ኑሮአችን የምንጠቀምባቸውን መሣሪያዎች መመልከት ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም አገራችን ከፍተኛ የሆነ የጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ከፀሃይ ኃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጭ ቴክኖሎጂዎችን በአማራጭነት እየተጠቀመች በመሆኑ ነው፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ የፀሃይ ሃይልን በመሰብሰብ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት የሚያስችል ነው፡፡ ከዚህ ቴክኖሎጂ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ሃይል ታዳሽ በመሆኑ በዘላቂነት መጠቀም ይቻላል፡፡ በየትኛውም መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና በቂ ፀሃይ ጨረር በሚገኝባቸው አካባቢዎች ሁሉ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ቴክኖሎጂ ስለሆነም በሀገራችን ተመራጭ ሆኗል፡፡

በአገሪቱ የሚኖረው ሰፊው ህብረተሰብ አርሶ አደር በመሆኑ የኤሌክትሪክ መስመር ባልተዘረጋባቸው አካባቢዎች ተደራሽ በመሆን ከፍተኛ የሃይል አማራጭ ሆኖ ይገኛል፡፡ በባህላዊ የማገዶ አጠቃቀም ምክንያት ወደ አካባቢ አየር የሚለቀቁትን አማቂ ጋዞችን የሚቀንስ ስለሆነም ለአካባቢ ብክለት መቀነስ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው። የአካባቢ ሙቀት ሳቢ ጋዞችን ልቀት በመቀነስ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የእንስሳትና የሰብል ምርታማትን በማሳደግ፣ የአርሶና አርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ላይ ናት።

በተጨማሪም የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ደንን በመጠበቅና በማልማት፣ ከታዳሽ ኃይል ምንጭ የኤሌክትሪክ ኃይል በሰፊው በማመንጨትና ዘመናዊና ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን በትራንስፖርት፣ በኢንዱስትሪና በህንፃ ኮንስትራክሽን ዘርፎች በመጠቀም ረገድ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው፡፡ ይህን ትኩረት ለማሳለጥ በሚደረገው ጥረት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊዎች በቀላሉ ደንን ለማልማት በሚደረገው ሂደት ውስጥ ጉልህ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡

ዛሬ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን መከተል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካዊያን አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆኗል። በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ካሉት ሀገራት ውስጥ ቻይናን እና ህንድን ብቻ ብንወስድ፤ እያንዳንዳቸው ከዚህ በፊት የዓለም ፍጆታን በሞኖፖል ከያዘው ክፍል በእጥፍ የሚበልጥ ህዝብ ያላቸው ናቸው። እነዚህ ሀገሮች በፍጥነት እያደጉ በሄዱ ቁጥር የተፈጥሮ ሃብት ምርቶች ፍላጎታቸው በዚያው ፍጥነት አድጓል።

እርግጥ በየትኛውም የዓለም ክፍል ውስጥ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ተኪ የሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን ማፍራት የሚቻል ቢሆንም፤ የተፈጥሮ ሃብትን ሙሉ በሙሉ መተካትና ህዝቦች ያላቸውን ፍላጎት በፍጥነት መቀነስ ግን አይቻልም።

በአሁኑ ሰዓት የተፈጥሮ ሃብት ተፈላጊነቱ እየጨመረ መጥቷል። ይህ ሁኔታም የተፈጥሮ ሃብት እጥረት እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑ አያጠያይቅም። የዓለም የተፈጥሮ ሚዛን ክፉኛ ሊናጋም ይችላል። እናም የተፈጥሮ ሃብትን በከፍተኛ መጠን ለመቆጠብ የሚያስችሉ እንደ የታዳሽ ሃየል ምንጮችን መፍጠር የግድ ይላል።

ታዳሽ ሃይልን መጠቀም በአየር ጠባይ ለውጥ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ አለው። ምዕራብ አውሮፓና አሜሪካ የሚከተሉት የዕድገት አቅጣጫ ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅስ ኢነርጂ አላቂ ከሆኑት የካርቦን ኬሚካሎች በማመንጨት ላይ የተመሰረተ ነው። እነዚህ የሃይል አማራጮች አላቂ ከመሆናቸውም በላይ የሚለቁት ካርቦንዳይአክሳይድ መጠን አየር ላይ እየተከማቸ የመሬትን ሙቀት ይጨምራል።

በአሁኑ ሰዓት በአገራችን መሻሻሎች ቢኖሩም የአየር ንብረቱን ለመቀጣጠርና ሚዛናዊ ለማድረግ የሚጠቅሙትን ደኖች በመጨፍጨፍ ለተለያዩ ሃይል መጠቀሚያነት እንዲውሉ ማድረግ አህጉሪቱን በድርቅ አደጋ ዋጋ እንድትከፍል እያደረጋት ነው።

በአሁኑ ሰዓት የድርቅን አደጋ ለመከላከል ደኖችን በመትከል መከላከል ይቻላል። በዚህ ተግባር ላይ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በክረምቱ ወራት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የፈሉ ችግኞችን በመትከል ሊሳተፉ ይችላሉ። ይህም ቢያንስ ድርቅን ሊቋቋም የሚችል ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር የሚያስችል ነው።  

አገራችን በአረንጓዴው ልማት ለታዳሽ ሃይል ትኩረት ሰጥታለች። የኃይል ልማት ፖሊሲው ከነባሩ ወይም ባህላዊ መንገንድን ተከትሎ ከሚደረገው የሃይል ማመንጨት ስራ ቀስ በቀስ ዘመናዊ የሃይል አጠቃቀምን መከተል እና መሸጋገር እንዳለባት በማመን እየሰራች ነው።

ይህ መንገድ አስተማማኝ የሃይል አቅርቦትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሁሉም የማዳረስና ለኢኮኖሚውም ዕድገት በቂ ሃይል የማቅረብ ሃሳብም ያለው ነው። ለአገር ውስጥ የሃይል ምንጭ ቅድሚያ በመስጠት ራስን መቻልን የሚያልምም ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም ንፁህ ኃይልን ቆጥቦ በብቃት በመጠቀም የአካባቢ የአየር ሁኔታ ጤናማነትን ለማስቀጠል ያግዛል። ኢትዮጵያ ይህን ታሳቢ ያደረገ የታዳሽ ሃይል ፍላጎትና አቅርቦትን የተከተለ የኢኮኖሚ ስርዓት ገንብታ እየሰራች ነው።

ስለሆነም ይህን መሰሉን ኢኮኖሚ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማገዝ አገርንና ህዝብን በድርቅና በተፈጥሮ ሃብት መራቆት ሳቢያ ከሚከሰት ችግር መከላከል ስለሆነ ለአገግሎቱ መትጋት እጅግ ወሳኝ ነው። ስለሆነም በበጎነት አርአያ ሆኖ በመሰለፍ አቻዎችን ወደ አገልግሎቱ መሳብ ይገባል።