ቀጣዩ ተስፋችን

በአገራችን እየተካሄደ ያለው ለውጥ በኢኮኖሚው ላይ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው። ለውጡ ኢኮኖሚውን በማነቃቃት ኢንቨስትመንትን መሳብ ችሏል። በለውጡ የተገኙት ውጤቶች ዘለቄታዊነት እንዲኖራቸው መንግስት ከፍተኛ ጥረቶችን እያደረገ ነው። ቀጣዩ ብሩህ ተስፋችን እውን ይሆን ዘንድ ህብረተሰቡ ለውጡን አጠንክሮ በመያዝ ፀረ ለውጥ ተግባር ፈፃሚዎችን ሊታገላቸው የሚገባ ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ፣ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለ ሃብቶችን ለመሳብ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማመቻቸት በሩን ከፍት በማድረግና በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ተጨባጭ ሁኔታውን በማስረዳት በአጭር ጊዜ ውስጥ አመኔታን አትርፎ በርካታ ባለሃብቶችን እየሳበ ነው።

በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለ ሃብቶች ቁጥር ከፍ እያለ ነው። አንፃራዊ ሰላማችንና አንድነታችን የፈጠረው ምቹ ሁኔታ የተገነዘቡ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ነው።

አዲሲቷ ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥም ይሁን የውጭ ባለሃብቶችን የሚሰማሩባቸውን ዘርፎች በመለየት እንዲሁም በመንግስት ስር ያሉ የልማት ተቋሞችን ወደ ግል በከፊልም ይሁን ሙሉ ለሙሉ ለማዞር እየተደረገ ያለው ጥረት ኢከኖሚውን እያበረታታው ነው። ይህም ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ የበኩሉን ሚና ይጫወታል።

የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገቱ አንቀሳቃሽ ሞተር በመሆኑ በመንግሥት ታምኖበት የአገር ውስጥም ይሁን ባለ ሃብቶች በዓለም የገበያ ውድድር ውስጥ ጠንካራ አቅም እንዲኖራቸው ቀጣይነት ያላቸው ድጋፎች ይደረግላቸዋል። ባለ ሃብቶቹ የሃብት ባለቤት እንዲሆኑና ለዜጎች የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸው በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ለማድረድ መንግስት እየሰራ ነው።

የአገር ውስጥን ባለሃብቶች ከውጭ ባለሃብቶች ጋር በማቀናጀት ለመፍጠር የተቻለው የገበያ ትስስርም ምቹ የኢንቨስትመንት መሰረትን ጥሏል ማለት ይቻላል። ከእነዚህ ውስጥ የቦንድ ዋጋ ከፍ ማለት፣ የወጪ ንግድ የብድር ዋስትና ስርዓት መተግበር፣ የውጪ ምንዛሪ ተመን ማስተካከልና የምንዛሪ ዋጋው ከንግድ ባንክ እኩል እንዲሆን ማድረግ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ተግባሮች ናቸው።

አገራችን የትምህርት፣ የጤና፣ የመንገድና የንፁህ መጠጥ ውሃ መሰረተ-ልማቶች ሙሉ ለሙሉ ያልተሟሉባት በመሆኗ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ከሀገራዊው ዕድገት ጋር የሚመጣጠን ግንባታዎች ለማካሄድ በመንግስት በኩል እንደሚካሄደው በተመሳሳይ ሁኔታ የግሉ ባለሃብት ሊከናወን አለመቻሉ ነው።

የግሉ ዘርፍ የኦኮኖሚ ዕድገቱ አንቀሳቃሽ ሞተር ስለሆነ ሃገራዊም ይሁን የውጭ ባለሃብቶች እንዲፈጠሩ እየተደረገ ነው። መንግስት የሚከተለው የኢንቨስትመንት ፖሊሲ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን ያሳደገና የስራ ዕድል የፈጠረ ብቻ አይደለም። ይልቁንም የአገራችንን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት እንደ የሀገር ውስጥ ባለ ሃብቶች ሁሉ ተመጣጣኝ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማምጣት የሚችሉ የውጭ ባለሃብቶችም ወደ አገራችን እንዲገቡ እየተደረገ ነው። ይህ ሁሉ ተግባር ኢኮኖሚው እንደያንሰራራ ያደረገ ነው።

መንግስት ለአገራችንም ይሁን ለውጭ ኢንቨስተሮች ሙሉ ዋስተና ይሰጣል። ማንኛውም ባለሃብት እዚህ ሀገር ውስጥ ለሚያፈሰው መውዓለ ነዋይ መንግስት ኃላፊነት ወስዶ የሚሰራ ይሰራል። በአሁኑ ሰዓት በአገራችን ከተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ጋር ተዳምሮ መንግስት በየደረጃው የሚወስዳቸው ህግና ስርዓትን የማስከበር ተግባር አመኔታን ማግኘት ችሏል። ይህም ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ እንዲሆን ያስቻለ ነው።

ታዲያ ይህ ሁሉ የመንግስት ጥረት ኢኮኖሚው በተያዘው ዕቅድ መሰረት እንዲከናወን የሚያስችል ይመስለኛል። በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፉን የሚያነቃቃ ነው።

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት አሁን ካለው ድርሻ በአራት እጥፍ እንዲጨምር በማድረግ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የተመራ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማረጋገጥ ታቅዷል። በዚህም መሠረት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በ2007 ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የነበረውን የ4 ነጥብ 5 በመቶ ገደማ ድርሻ በአራት እጥፍ በማሳደግ በ2017 ዓ.ም ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል ለማድረግ ታቅዷል፡፡

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው በላቀ ፍጥነት የሚያድግ ቢሆንም መነሻ መሠረቱ በጣም ጠባብ በመሆኑ በትራንስፎርሜሽንና ዘላቂ ልማት ስራው የመጨረሻ ዓመት (በ2012 ዓ.ም) ከአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት የሚኖረው ድርሻ ስምነት በመቶ አካባቢ ይሆናል። ስለሆነም በሚቀጥሉት 10 ዓመታት የምናረጋግጠው የ11 በመቶ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የተመራ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር በጉልህ እንደሚመጣ የሚያደርግ ጭምር መሆን ይጠበቅበታል።

ይህም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ካለው ጠባብ የኢኮኖሚ መሠረት አንፃር በተለይም በሁለቱም የአምስት ዓመታት ዕቅዶች ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት እንዲይዝ ከሚጠበቀው ድርሻ አኳያ የተቀመጠውን ግብ በተወሰነ መልኩ ማሳካት ይቻላል።

በተያዘው ዕቅድ መሰረት የኢኮኖሚው ማገር የሆነው የግብርና ዘርፍ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት የ36 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ማለት የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከሁሉም ክፍላተ-ኢኮኖሚ ዘርፎች በላቀ ፍጥነት እንዲያድግ ዕድል ይሰጣል።

ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የሚኖረው ድርሻ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማብቂያ ዓመት በ2012 ወደ 23 በመቶና በ2017 ደግሞ ወደ 28 በመቶ ከፍ እንደሚል ታቅዷል። የአገልግሎቱ ዘርፍ ድርሻ ከግብርና እና ከኢንዱስትሪ ቀሪው መቶኛ ድርሻ ይኖረዋል።

በእኔ እምነት መንግስት በአሁኑ ወቅት እያደረጋቸው ያሉት ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅሱ ተጨባጭ እርምጃዎች እነዚህን ሁኔታዎች መፈፀም ይችላል። ታዲያ ሁሉም ዜጋ በኢኮኖሚው ላይ የሚደረጉትን አሻጥሮች በመከታተለ የተያዘውን መንግስታዊ የኢኮኖሚ ማነቃቃት ስራ መደገፍ አለበት።