መላ እናብጅለት…

በአገራችን ውስጥ ሊቀረፍ ያልቻለው ህገ ወጥ ስደት አሁንም አጀንዳ ሆኖ አሳዛኝ ክስተቶችን እየፈጠረ ቀጥሏል። የስደቱ መነሻ ምንም ይሁን ምን፣ ህገ ወጥ ዝውውሩ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚያሳጣ ነው። ክስተቶቹ በጥቂት ወራት ውስጥ ብቻ የታደሰ ስም ይዛ ተቀባይነት እያገኘት ያለችውን አገራችንን ገጽታ ግንባታ ጥላሸት ሊቀቡ የሚችሉ ናቸው።

በመሆኑም መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ እያከናወነ ካለው ዘላቂ ስራዎች ባሻገር፣ ህብረተሰቡም የችግሩ ቀጥተኛ ሰለባ ስለሆነ መላ ሊያበጅለት የሚገባ ይመስለኛል። በየደረጃው የሚገኙ አስፈፃሚ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት የችግሩ እልባት ሰጪ አካል መሆን ይኖርበታል።  

ህገ ወጥ ስደት የዜጎችንና የአገርንና ክብር ይነካል። ክብረ ነክ ነው። በመሆኑም ዜጎች ሰብዓዊ መብታቸውና ክብራቸው ሳይነካ መንገስት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ መጠቀም ይኖርባቸዋል።

ዛሬ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት ህገ መንግስታዊ እውቅና እና ጥበቃ አለው። ማንኛውም ዜጋ በፈለገው ጊዜና ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራትና ሃብት የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብት ይዟል። ይህን መብት መቃወም ህገ መንግስቱን መፃረር ነው።

ህገ መንግስታዊ መብትን በአግባቡና ህጋዊ በሆነ ሁኔታ መጠቀም ይገባል። አንድ ዜጋ ባሻው ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ስላለው ብቻ ራሱን ለአደጋ ቤተሰቡን ደግሞ ለችግርና ለስጋት አጋልጦ ህገ ወጥ መንገድን መጠቀም የለበትም። መዘዙ እርሱንም ይሁን ቤተሰቡን የሚጎዳ ስለሆነ ነው።

ህጋዊነትን ተቀብሎ በህግ አግባብ ማንኛውንም ነገር ማከናወን ራስን ከአደጋና ከውርደት በመጠበቅ የሀገርን ክብርም ማስጠበቅ ነው። መንግስት ህጋዊ መንገዶችን በመፍጠር ዜጎች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ እያጠና ነው። ችግሩን ለመቅረፍ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ስራቸውን እየከወኑ ነው። ህብረተሰቡም የነኩሉን እገዛ ማድረግ አለበት።

በተለይ በክልሎች ውስጥ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት ብርቱ ጥረት መደረግ ይኖርበታል። እርግጥ ለህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መፍትሔው በመንግስት ላይ ብቻ የተጣለ ሊሆን አይችልም። ህብረተሰቡ የህገ ወጥ ዝውውሩ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት ህገ ወጥ ደላሎችን ያውቃቸዋል።

ህብረተሰቡ በየቀየው የህገ ወጥ ዝውውሩ አቀናባሪና ስደተኞችን ወደ ሞት የሚገፉ እነማን ማንም አይነግረውም። እንደ እጆቹ ጣቶች በሚገባ የሚያውቃቸው ናቸው። በመሆኑም ለችግሩ መፍትሔ ህብረተሰቡ ወሳኝ አካል ነው። ህብረተሰቡ ችግሩን ለመፍታት ቁርጠኛ እስከሆነ ድረስ የመንግስት ህጋዊ አሰራር ግቡን የማይመታበት ምክንያት አይኖርም።

እርግጥ ችግሩን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከስደት የተመለሱ አንዳንድ ወገኖች የሚፈጥሯቸው አሉታዊ ተጽዕኖዎች በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም። ከዚህ አኳያ እነዚህ ወገኖች የሚያሳድሩት ጫና በቤተሰባቸው ጭምር የሚደገፍ ሆኖ እናገኘዋለን።

ቤተሰቦቻቸው ልጆቻቸው ውጪ ሀገር ሄደው የሚያመጡት ገንዘብ በምን ሁኔታ የተገኘ መሆኑን ስለማይገነዘቡ ከስደት የተመለሱት ልጆቻቸው በስደት ሄደው ያመጡትን ጥቅም በመዘርዘር የህገ ወጥ ስደቱ ሂደት ተካፋይ የሚሆኑበት ሁኔታ ቀላል አይደለም። ይህም ቤተሰቦች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በደላልነት ተሰልፈው የዜጎቻቸውን ህይወት ለአደጋ አሳልፈው እንዲሰጡ ያደርጋል።

በየቀየው በህገ ወጥ ደላላነት የተሰለፉ አካላት የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨትና በሌሎች ዘዴዎች ለህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር አመቺ ሁኔታ የመፍጠር እንዲሁም ተጋላጭ ግለሰቦችን የመለየት ስራን ከሌሎች ጋር በመሆን ያከናውናሉ። ከሀገር የሚያስኮበልሉ ድንበር አሻጋሪዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን እያዘዋወሩ ይጠቀማሉ።

አዘዋዋሪዎቹ ሰዎችን በቡድን ከአካባቢ ደላሎች ተቀብለው ለሌሎች ተመሳሳይ አዘዋዋሪዎች የማስተላለፍ ስራዎችን እያከናወኑ ቢጠቀሙም ተጎጂው ግን ገንዘቡን አውጥቶና እነርሱን አምኖ የሚጓዘው ተዘዋዋሪ ነው። ምክንያቱም በየሄደበት ቦታ ሳይደርስ መንገድ ላይ በኮንቴይነር ታፍኖ የሚሞተውና በሌላ አገር ፖሊስ በቁጥጥር ስር የሚውለው እርሱው ስለሆነ ነው።

ወጣቶች የህብረተሰቡ አንድ አካል ናቸው። ይህን አስከፊ ክስተት አውቀው መሸሽ አለባቸው። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ወጣቶች ራሳቸው በፈጠሩት ለውጥ የእኔ የሚሉት መንግሥት  አላቸው። ለውጡ በአገራቸው ውስጥ ሰርተው ማደግና መለወጥ ብቻ ሳይሆን፣ ሃብት ማፍራትና ጥሪት መቋጠርም እንዲችሉ የሚያደርጋቸው ነው። ስለሆነም ስደትንና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን እንደ አማራጭ መውሰድ አይኖርባቸውም።

እናም ወጣቶች ውጭውን ብቻ ሳይሆን ውስጣቸውን በቅጡ ማማተር ይኖርባቸዋል። በሁሉም አገር ውስጥ ቢሆን በመስራት እንጂ ገንዘብ እንደ ሰማይ መና ከሰማይ አይወርድም። ውጭ የሚከናወን ስራ አገር ውስጥ ሊተገበር ይችላል።

እዚህም ይሁን እዚያ ማግኘት የሚፈለገው ገንዘብ እስከሆነ ድረስ ቁልፉ ነገር በርትቶ መስራት ነው። ስራን ሳንነቅ መስራት እስከቻልን ድረስ መለወጥ የማንችልበት ምክንያት የለም።

ምክንም እንኳን ዜጎች ድህነትን ለመቅረፍ የሚሄዱባቸው መንገዶች ሊኮነን የማይችል ቢሆንም፤ በህገ ወጥ ደላሎችና አፈ ቅቤዎች ተታልለው ራሳቸውን ለአደጋ ማጋለጥ የለባቸውም። በተለይ ሁሉም ነገር ህግን የተከተለ አካሄድ ተጠቅሞ ማደግና መለወጥ እየተቻለ፣ ህይወት ጭምር የሚያሳጣን ህገ ወጥ አካሄድን በመያዝ ራሰን ለአደጋ ማጋለጥ ተገቢ አይደለም። በመሆኑም ማህበረሰቡ በዚህ ረገድ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን በመፈተሽ ህገ ወጥነትን መላ ሊያበጅለት ይገባል።