እርቀ ሰላሞቹ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንና በእስልምና ኃይማኖቶች ውስጥ ለዓመታት የዘለቀውን ቅራኔ ለመፍታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነት በተደረገው ጥረት ውጤታማ ሆኗል። የተፈጠረው እርቀ ሰላም በአገራችን ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር መጠናከር ላይ የሚኖረው እንድምታ ከፍተኛ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረት በስደት ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ወደ አገር እንዲመለስ ያደረገና ለሁለት ተከፍላ የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን ወደ አንድነት ያመጣ ነው። ይህ ሁኔታ በአገራችን እየመጣ ካለው ዘላቂ ሰላም አኳያ ትርጉሙ የላቀ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ በ1983 ዓ.ም ከተደረገው የመንግሥት ለውጥ በኋላ አራተኛው ፓትርያርክ የነበሩት አቡነ መርቆሬዎስ መንበራቸውን ለቀው ከተወሰኑ አባቶች ጋር ከአገር በመውጣትና በስደት ሲኖዶስ አቋቁመዋል።

ኢትዮጵያና አሜሪካ በሚገኙ ሲኖዶሶች መካከል እርቀ ሰላም ለማውረድ የተደረገው ተደጋጋሚ ጥረት እልባት እንዲያገኝ ከሁለቱ ሲኖዶሶች አባቶች እንዲሁም ከካህናትና ምዕመናን በተውጣጣው የሰላም ኮሚቴ አማካይነት ከሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ባካሄደው ውይይት ስምምነት ላይ በመድረሱ ነው።

ይህ ተግባር እንዲፈጸም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አመድ ጉልህ ድርሻ ነበራቸው። በቅርቡ ዋሽንግተን ዲሲ በተደረገው ስምምነት ዶክተር አብይ በስፍራው ተገኝተው ሁለቱም ፓትርያርኮች በእኩል ክብር ቤተ ክርስቲያኒቱን እንዲያገለግሉ ማድረግ ተችሏል።

በአሁኑ ሰዓት የአገር ቤትና የውጭ አገር ሲኖዶስ የሚለው ስም ቀርቶ አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ እንዲሆን ተወስኗል። በሁለቱም ሲኖዶሶች የተላለፈው ቃለ ውግዘት በጋራ ምልዓተ ጉባኤ እንዲፈታ ተደርጓል።

ዶክተር አብይ የውጭውን ሲኖዶስ ሲመሩ የቆዩትን አራተኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ  አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አዲስ አበባ  ይዘው ተመልሰዋል። ፓትርያርኩ ጸሎትና ቡራኬ በማድረግ ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ ተወስኗል። ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስና ስድስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በአስተዳደር ሥራ ቤተ ክርስቲያንን በመምራት ጸሎትና ቡራኬ በማድረግም  ቤተ ክርስቲያንን እንዶያገለግሉ ተደርጓል።

ቀደም ሲል የተሾሙ ነባር ሊቃነ ጳጳሳትን በተመለከተም በሁለቱ ሲኖዶስ የተላለፈው ቃለ ውግዘት በጋራ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በመፈታቱ ስማቸውና ክብራቸው ተጠብቆ በውጭም ሆነ በአገር ቤት በሀገረ ስብከት እንዲመደቡና እንዲያገለግሉ ይደረጋል። ከዚያም  በኋላ በሁለቱም ወገኖች የተሾሙትም ስማቸውን እንደያዙ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀበላቸውና በውጭም ሆነ በአገር ቤት ተመድበው ምዕመናንንና ቤተ ክርስቲያኒቱን እንዲያገለግሉ ይደረጋል።

ይህን ታላቅ ስራ የከወኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሁለቱ ሲኖዶሶች አባላት በመስማማታቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። የአንድነትን መንፈስ “ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አንድ ስትሆን እኛም አንድ እንሆናለን” በማለት ገልፀውታል። ይህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አንድ ስትሆን ምዕመናን ከልዩነት ተላቅቀው ለአምላካቸው ብሎም ለአገራቸው እንዲያስቡ የሚያደርጋቸው ይሆናል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ስድስተኛውን ፓትሪያርክ ይዘው በመምጣታቸው የአንድነትና ትውወቅ ስነ ስርዓት ተካሂዷል። በዚህ ወቅትም አቡነ ማቲያስ፣ ሁለቱ ሲኖዶሶች እርቅ ፈፅመው ከ26 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለጉባኤ በጋራ መገናኘታቸው ደስታ እንደፈጠረባቸው አስታውቀዋል። ባለፉት ዓመታት በሁለቱ ሲኖዶሶች መለያየት የተነሳ ሀገሪቱ ያጣችውን አንድነትና ፍቅር በጋራ ፀሎት እና ስራ ህዝቡንና ቤተ ክርስቲያኗን መካስ እንደሚገባ አስረድተዋል። ይህ ሁሉ የሆነው ዶክተር አብይ በፈጠሩት የእርቅ ምህዳር መሆኑ ግልፅ ነው። እርግጥ ሃይማኖቶች እርቅና ይቅርታን በመለዋወጥ የሰላም ሃዋሪያ መሆን ይኖርባቸዋል።

የትኛውም ሃይማኖት በውስ ሰላምን ከፈጠረ የግጭት ምክንያቶች ሊወገዱ ይችላሉ። ግጭቶች ከተወገዱ ደግሞ አገራዊ አንድነት መፈጠሩ አይቀርም። አንድነት ከተፈጠረ ሰላም እውን ይሆናል። ሃይማኖቶች አማኞቻቸው ለሰላም እንዲተጉ፣ የተቸገረን እንዲረዱና ጭካኔና ግጭትን እዲያስወግዱ ያስተምራሉ።

በዴሞክራሲያዊ አገራት  ውስጥ ሁሉም ዜጎች እኩል ናቸው። አይበላለጡም። የሚፈጽሟቸው ማናቸውም ጉዳዩች አይበላለጡም። አንድ ዜጋ የሚከተለው እምነት ከሌላው ሊበልጥም ሆነ ሊያንስ አይችልም። ይህም እንደ እኛ ባለው ዴሞክራሲያዊ የለውጥ አገር ውስጥ ሁሉም እምነቶች እኩል ስለ መሆናቸው አስረጅ ነው። አንዱ ሃይማኖት ያለው መብት ሌሎችም አላቸው። 

አገራችን ውስጥ ማናቸውም ሃይማኖቶች የበላይ ወይም የበታች ሊሆኑ አይችሉም። የእከኩልነታቸው መሰረት የሚመነጨው ኢትዮጵያ ከምትከተለው የዴሞክራሲ ስርዓት የእኩልነት መርህን በጥብቅ ስለሚያምን ነው። እኩልነት የዴሞክራሲ አንዱ መርህ በመሆኑ ይህን መርህ መሸራረፍ አይቻልም። መሰረታዊውን የዴሞክራሲ አሰራር ሊያናጋው ይችላልና።

መንግስትና ሃይማኖት አገራችን ውስጥ የተለያዩ ቢሆኑም፤ የአንድን ሀገር ህዝብ በተለያየ መንገድ የሚያገለግሉት መንግስትና ሃይማኖት ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም ማለት አይቻልም። ሁለቱም አካላት በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በየራሳቸው የነጻነት ማዕቀፍ በመንቀሳቀሳቸው ብቻ ፈፅሞ የማይገናኙ ናቸው ብሎ መውሰድ አይቻልም። ሁለቱም አካላት ከሀገራቸው ዜጎች ጋር አብረው እስከሰሩ ድረስ አንደኛው ከሌላኛው ጋር መገናኘታቸው አይቀሬ ነው። የአገርን ሰላም ለመፍጠር በጋራ ሊሰሩ ይችላሉ።

በዚህ መሰረትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ልክ እንደ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሁሉ በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ የተፈጠረውን መከፋፈል ለመቅረፍ ተንቀሳቅሰዋል። በእርሳቸው ጥረት በእስልምና ሃይማኖት ውስጥም የነበረው መከፋፈል ወደ አንድነት እያመራ ነው።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተግባር አገራችን የተያያዘችው የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር ጉዞ የደረሰበት ሂደት እና የወደፊቱን ተስፋችንን የሚያመላክት ነው። ስለሆነም ህዝቡ ለለውጡ እየሰጠ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ በመቀጠል የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥረት ማገዝ አለበት።