የአቢይ ዐቢይ መንገድ ክፍል አንድ

ሰሞኑን ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ አህመድ በአሜሪካ ያደረጉት ውይይት ለእኛ ለኢትዮጵያውን ብቻ ሣይሆን ለሌሎችም ህዝቦች የተለየ ስሜት የፈጠረ ገብኝት ነበር፡፡ ኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ እና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በተለያዩ የአሜሪካ ስቴቶች በተዘጋጁ ጉባዔዎች ለታደሙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን ባደረጓቸው ንግግሮች የዳያስፖራውን ፍቅር እና አክብሮት አትርፈዋል፡፡ ብዙዎቹን በእንባ አራጭተው እነሱም የፍቅር እንባ አፍስሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል፡፡ በርካቶች ‹‹ለመጀመሪያ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሬ ብዬ የምቀበለው መሪ አገኘሁ›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በአርባ ዓመታት ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ኤምባሲን ደጅ የረገጡ ሰዎችም ታይተዋል፡፡ አንድ ላይ ለመቀመጥ ቀርቶ፤ በዓይን ለመተያየት እንኳን የማይፈቅዱ ኢትዮጵያውያን በአንድ ስፍራ ታድመዋል፡፡ ስለ አንዲት ሐገር እና ሕዝብ ጥቅም በጋራ ለመስራት ቃል ገብተው እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ ይህ ይሆናል ብለው አስበው የማያውቁ አንዳንድ ሰዎች፤ ሆኖ በተመለከቱት ተደምመዋል፡፡ ነገሩ ህልም ይሁን እውን መለየቱ ቸግሯቸው ዓይናቸውን ተጠራጥረዋል፡፡ የጥላቻ ግንብ ተንዶ፤ የመራራቅ ሸለቆን በፍቅር ድልድይ ተሻግረው ተቃቅፈዋል፡፡

ኢትዮጵያ፤ ከሃያ ሰባት ዓመታት በፊት የልማት ሳይሆን የጦርነት ዕቅድ የሚነደፍባት እና የሚተገበርባት ምድር ነበረች፡፡ የጥይት አረር የሚያፏጭባት፣ የመድፍ ቅንቡላ የሚጨፍሩባት፣ ፀረ- ሰው እና ፀረ- ታንክ ፈንጅዎችን ጎርሳ ሞትን የምትተፋ ምድር ነበረች፡፡ ከሰማይ እና ከምድር ሞት የሚዘራባት፤ ጦርነት የሚያስከትለው ሰቆቃ እና እሪታ የገነነባት ምድር ነበረች፡፡ የአንድ ሀገር ልጆች በእርስ በእርስ ጦርነት ደም የሚፋሰሱባት ሐገር ነበረች፡፡ ይህች ሐገር የዛሬ ሃያ ሰባት ዓመት ከእርስ በእርስ ጦርነት ብትላቀቅም፤ ጦርነት ለሰላም ቦታ ቢለቅም፤ አምባገነን ስርዓት ስርዓት ተገርስሶ፤ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር  ለማጽናት ቢሞከርም፤ እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ፤ ህዝብን የሚያስከፋ እና የሚያስቀይም ነገር ተበራክቶ፤ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ሐገራችን በውጥረት ቆይታለች፡፡ ይህን ችግር ለማስወገድ መሪው ድርጅት ኢህአዴግ የጥልቅ ተሐድሶ መድረክ በተደጋጋሚ እየዘረጋ ውጤት ማምጣት ተስኖት ከቆየ በኋላ፤ በመጨረሻ እንደ ብረት ፍርግርግ አስሮ የያዘውን  ውስጣዊ ችግር ጥሶ ማለፍ በቻለ የለውጥ ኃይል አማካኝነት አደጋው ተቀልብሶ፤ ያ ተስፋ ማጣት፤ በተስፋ ተተክቶ፤ ጨለማው በብርሐን ተለውጦ፤ ጥላቻም ለፍቅር፣ ለይቅርታ እና ለመደመር ቦታ ለቅቆ፤ አዲስ የተስፋ ፀሐይ ደምቆ ማየት ችለናል፡፡

አሁን አዲስ ተስፋ ሲንጸባረቅ ያየነው፤ ባለፉት አርባ ዓመታት አንድም የተስፋ ጨረር ካልነበረው የህብረተሰብ ክፍል ጭምር ነው፡፡ ለዚህ አንድ ትልቅ ምሣሌ ተደርጎ ሊነሳ የሚችለው፤ ለዘመናት የሰላ ትችት በመሰንዘር የሚታወቁ ምሁራን የሚሰጡት አስተያየት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም እና የዶ/ር ጌታቸው ኃይሌ አስተያየት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌ ከቀናት በፊት  ‹‹ክቡር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንኳን ደኅና መጣህ›› በሚል ርዕስ በጻፉት ጽሁፍ ለውጡን በምን ስሜት እንደተቀበሉት የሚያመለክት ነው፡፡

‹‹ክቡር ዶክተር ዐቢይ፤ ክቡር አቶ ለማ፤ በልባችሁ ያለውን ትሕትና ሰሞኑን ሳነብ፥ “አንተ” እያልኩ ሳማችሁ እንደነበረው እንድቀጥል እንደፈቀዳችሁልኝ አይቻለሁና፥ በአሜሪካ በድዮስጶራ ደረጃ ያለነውን ኢትዮጵያውያን ስላልረሳችሁን እያመሰገንኩ፥ እንኳን ደኅና መጣችሁ እላለሁ›› በማለት ጽሁፋቸውን ይጀምራሉ።

‹‹ 'እነሱ በሰላም ይኖራሉ̀ ብላችሁ ሳታስቡ እኛን ፍለጋ ስለመጣችሁ፥ መጠን-አልባ ደስታየን እገልጽላችኋለሁ። እርግጥ ነው፥ ባለንበት አገር ከፖሊስ ጋር እስካልተፋጠጥን ድረስ በሰላም እየወጣንና በሰላም እየገባን በሰላም እንኖራለን። ግን ሰላም ማለት በሰላም ወጥቶ ከመግባት ያልፋል። ከወገናችን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ያለን ግንኙነት የመንፈስ ብቻ ሳይሆን የአካልም ስለሆነ፥ በማንኛውም ኢትዮጵያዊ ላይ የሚደርሰው ደስታ ያስደስተናል፤ የጨቋኝ ገዢ ጥቃት እናንተን ያምማችሁ እንደነበረ እኛንም ያመን ነበረ›› በማለት አትተዋል።

ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌ አክለውም፤ ‹‹ምዕራባውያን ከማህላቸው አንድ ስም ያወጣ ሰው (celebrity) ሲያዩ፥ ሊነኩትና ሊጨብጡት ሲጋፉ ሳይ፥ በመገረም እታዘባቸው ነበረ። አሁን ገባኝ፤ የታሪክ ሰዎቼን በአካል በማየቴ ዕድለኛ ነኝ። አምላኬ ስለ ሀገራችን ላየውና ልሰማው የምመኘው ታሪክ እስከሚፈጸም እስከ ዛሬ ድረስ ስላቆየኝ፥ እንደ ሽማግሌው ስምዖን፥ “እስመ ርእያ አዕይንትየ አድኅኖትከ” (ዐይኖቼ ማዳንህን አይተዋልና) እለዋለሁ።››

ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌ ይቀጥላሉ፡፡

‹‹ግንቦት 24 ቀን ኢትዮጵያውያን ከታሰሩባቸው ሁለት እግር ብረቶች አንዱ፥ ጭቆና የተባለው እግር ብረት፥ የተፈቱበት ቀን ነው። ስለዚህም ሳንፈራ እንጽፋለን፥ ሳንሰጋ እንናገራለን፥ ሳንገላመጥ እንሰበሰባለን። ከፍርሃት ነፃ ወጥተናል። ሁለተኛው እግር ብረት ሲፈታልን፥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግንቦት  24  ቀንን በየዓመቱ የለማ መገርሳንና የዐቢይ አሕመድን ስም እየጠራ ሲያከብረው ይኖራል። በአንተም አመራር ሁላችንም በይቅርታና በፍቅር በሰላም ልንኖር ነው። ኢትዮጵያን ከጭቆና ነፃ ስላወጣሃትና በቀል የእግዚአብሔር መሆኑን ስላስታወስከን ከተቀመጥኩበት ተነሥቼ እጅ እነሣሃለሁ። በድዮስጶራ ያለነው ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሰላም ያገኘነውና “እፎይ” ብለን ያደርነው፥ ልዑል እግዚአብሔር የሕዝቡን ሥቃይ አይቶ፥ “ሕዝቤን ልጆቿን ከምትበላ ድመት እንድታድን ጠርቼሃለሁ” ብሎ ዐቢይን የላከው ዕለት ነው። ያን ሌሊት እንቅልፍ ያልወሰደው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ካለ፥ ታሪኩ ወደ ቅዠት እንዳይለወጥበት በመፍራት ያልተኛ መሆን አለበት። በሽተኛ ድመት፥ ሜዳው ሁሉ አይጥ በአይጥ ሆኖላት ሳለ፥ የምትበላው የራሷን ልጆች ነው። አርባ ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያ በገዛ ልጆቿ ከተበላች በኋላ፥ አንተና ፈር ቃዳጁ አቶ ለማ መገርሳ ቁጭታችሁን ይዛችሁ ብቅ ስትሉ፥ “በውኑ ከኢሕአዴግ ደግ ሰው ሊወጣ ይችላልን?” ያልን ጥቂቶች አልነበርንም። አትፈርዱብንም። ሳናስበው፥ የተፈጥሮ ጓደኛቸውን ሳጥናኤልን ሊመቱ የተላኩትን ሚካኤልንና ገብርኤልን መሰላችሁን።

‹‹ቅዱስ አምላካችን የሂትለርንና የስታሊንን ጀግንነት የሚኰንን፥ የማሀትማ ጋንዲን እና የኔልሰን ማንዴላን ጀብዱነት የሚያደንቅ መሪ ስላስነሣልን እናመሰግነዋለን። አንተንም፥ “ፈላስፋው መሪያችን ዐቢይ አሕመድ” ብየ ልጠራህ አስቤ ነበር፤ ግን ሕዝባችን እኔ የማውቀውን ፍልስፍናህን ሲያውቅ ራሱ ይጀምረዋል ብየ ተውኩት›› እያሉ ጥልቅ ስሜታቸውን ይገልጻሉ።

ብዕር ማንሳት የቻሉ ጥቂቶች እንዲህ ሲሉ፤ ብዙዎች ቃላትን ከንቱ በሚያደርግ ጩኸት እና የእንባ ቀለም ስሜታቸውን ተርከዋል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ‹‹ለእኛ የሚያስፈልገን አብዮት ሳይሆን ሪፎርም ነው›› ሲሉ የሚናገሩት የኢፌዴሪ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ የማሀትማ ጋንዲ እና የኔልሰን ማንዴላን ጎዳና የሚደንቁ መሪ መሆናቸውን ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌ ጠቅሰዋል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ‹‹ኪሳራ እንጂ ትርፍ አላገኘንበትም›› ከሚሉት ጎዳና ሐገራችንን ለማውጣት የሚከተሉት ጎዳና የፍቅር፣ የይቅርታ እና የአንድነት ጎዳና መሆኑን ደጋግመው ገልፀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈ ታሪክ በማተኮር ጊዜ ከማባከን ይልቅ፤ ያለንን ሐብት እና ጉልበት የወደፊቱን በማቃናት ተግባር ማዋል እንደሚገባን በአጽንዖት ይናገራሉ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መኖራቸውን፣ የኢኮኖሚ ወንጀሎች እና ምዝበራዎች መፈጸማቸውን ባለማወቃቸው ሳይሆን የሽግግር ሂደቱን ቀና በማድረግ፤ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት የሚሳለጥበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በማሰብ ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ከጋንዲ እና ከማንዴላ ጋር የተዛመደ እና ያልተለመደ ‹‹የሽግግር ፍትሕ›› የሚከተሉ መሪ ናቸው፡፡   

ብዙውን ጊዜ፤ የስርዓት ለውጥ ከተደረገ በኋላ በወደቀው አገዛዝ ሹማምንት የተፈፀመ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ የሚወሰዱ እርምጃዎች ‹‹የሽግግር ፍትሕ›› በሚል ይጠቀሳል፡፡ ዛሬ ‹‹የሽግግር ፍትሕ›› (Transitional Justice) ራሱን የቻለ አንድ የጥናት መስክ ሆኗል፡፡ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም ወዲህ ልዩ ትኩረት አግኝቷል፡፡ እንዲሁም በ1995 ዓ.ም ከተመሠረተው የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ተቋም ጋር ተያይዞ የሽግግር ፍትሕን የማረጋገጥ ፍላጎት እየተጠናከረ መጥቷል፡፡ ፖለቲካዊ ሽግግር በሚካሄድባቸው ሀገራት የሚገኙ የተለያዩ ማህበራዊ ኃይሎች በተደጋጋሚ የሚያነሱት ጥያቄ ሆኗል፡፡ በመሆኑም በይነ-ድስፕሊናዊ የሆነ የጥናት መስክ ሆኖ ወጥቷል፡፡ በዚህ የተነሳ፤ የተለያዩ ምሁራን የሽግግር ፍትሕህን አካሄድ በተመለከተ የተለያዩ አቋሞችን ሲያራምዱ ይታያል፡፡ ታዲያ እነዚህ ምሁራን የሽግግር ፍትሕ አፈፃፀም የተለያየ ስልት እና ሞዳሊቲ እንዲኖረው ይሻሉ፡፡

ሐገራት የፖለቲካ ሽብር እና የኃይል እርምጃ አፈፃፀምን፣ የታሪክ ውርሳቸውን (ሌጋሲ)፣ ፍትሕን፣ እርቅን እና የፖለቲካ መረጋጋት የመፍጠር ዓላማቸውን የሚያሳካው የትኛውን የሽግግር ፍትሕ ሞዳሊቲ እንደሆነ ፈትሸው ምርጫ ያደርጋሉ፡፡ በመንግስት የተቀነባበረ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ያስተናገዱ ሀገራት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሽግግር ሲያደርጉ፤ ከትናንት ታሪካቸው ጋር ለመታረቅ የሚወስዱት አማራጭ የተለያየ ነው፡፡

በዚህም መሠረት፤ አንዳንዶች የታሪክ እርቅን፤ የወንጀል ክስ በማቅረብ (Criminal Prosecution)፤ ሌሎች Lustration ወይም ካሣ እና ማቋቋሚያ በመስጠት (Compensation and Restitution)፤ እንዲሁም አንዳንዶች የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን በመሰየም የሽግግር ፍትሕን ለማስፈን ይሞክራሉ፡፡ እያንዳንዱ ህብረተሰብ ከነዚህ አማራጮች ውስጥ ከየራሱ የፖለቲካ አውድ እና ተጨባጭ ምክንያት በመነሳት የሽግግር ፍትሕ አፈፃፀሙን ይወስናል፡፡

ስም ያወጣ ሰው (celebrity) ሲያዩ ለመንካት እና ለመጨበጥ የሚጋፉ ሰዎችን በመገረም ይታዘቡ የነበሩት ዶ/ር ጌታቸው፤ ‹‹ያልደረሰበት ግልግል ያውቃል›› እንዲሉ፤ እሳቸውም እንደ ሌሎቹ ለመጋፋት የሚችሉ መሆናቸውን እንደተረዱ በመጠቆም፤ ‹‹የታሪክ ሰዎቼን በአካል በማየቴ ዕድለኛ ነኝ›› በማለት ለጠ/ሚኒስትሩ ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል፡፡ የአድናቆታቸው መነሻም የዶ/ር ዐቢይ ልበ ሰፊ ሰብእና መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ከ1983 ዓ.ም በኋላ የመንግስት ሥልጣን የያዘው ኢህአዴግ የሽግግር ፍትሕ አማራጭ አድርጎ የወሰደው የወንጀል ክስ ማቅረብን ነበር፡፡ የቀይ ሽብር ተከሳሾች አያያዝ እና የክስ ሂደት በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት መሠረታዊ እምነት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እና በኢህአዴግ ዘመን የታየው የሽግግር ፍትሕ በኢትዮጵያ ታሪክ ከተከሰቱ የስርዓት ለውጥ አጋጣሚዎች በልዩነት ሊጠቀስ የሚችል መሆኑን ምሁራን ይናገራሉ፡፡

እነዚህ ምሁራን፤ ‹‹በኢትዮጵያ የተለመደው የሽግግር ፍትሕ ሳይሆን Restorative Justice ነው›› ይላሉ፡፡ በመሆኑም፤ ኢህአዴግ በ1983 ዓ.ም የተከተለው ፖለቲካዊ የሽግግር ሂደት የህግ ተጠያቂነት ማስፈን ነበር፡፡ አሁን በሐገራችን የተመለከትነው የሽግግር ፍትሕ ደግሞ በእነ ጋንዲ እና ማንዴላ መስመር የሚሰለፍ እንደሆነ ዶ/ር ጌታቸው ጠቁመዋል፡፡