ተዓምር የታየባት አሜሪካ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ የአሜሪካ ጉብኝት ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ሲሆን በዲፕሎማሲው መስክም አዲስ ምእራፍ ከፍቶአል፡፡ ታላቅ የሆነ የገዘፈ ዲፕሎማሲያዊ ድልም አስገኝቶአል፡፡አሜሪካ  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ይዛ የምትኖር ሀገር ነች፡፡ በተለያዩ የአሜሪካ ስቴቶች ውስጥ እልፍ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ፤ይሰራሉ፤ይማራሉ፤ያስተምራሉ፡፡ እዚያው አሜሪካን ሀገር የተወለዱ ትወልደ ኢትዮጵያውያንም በብዙ ሺህዎች እንደሚሆኑ ይታመናል፡፡በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ የአሜሪካ ጉብኝት ባልተለመደ ሁኔታ ተአምር ታይቶአል ማለት ይቻላል፡፡መንግስትንና በስደት የሚኖሩ ዜጎችን በጥልቅ ያቀራረበ ድንቅ ትእይንት ሆኖ አልፎአል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ውጭ እጅግ ከፍተኛ በሆነ ቁጥር የሚኖሩባት ብቸኛዋ ሀገር አሜሪካን ነች፡፡ ቀድሞ በንጉሠ ነገስቱ በኋላም በደርግና በኢሕአዴግ ዘመን ወደ አሜሪካን ሀገር በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ገብተዋል፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን በዲቪ ሎተሪው እድል ኢትዮጵያውያን ወደ አሜሪካ ተጉዘዋል፡፡ በቀላል አገላለጽ አሜሪካ ለኢትዮጵያውያን ሁለተኛዋ ሀገራቸው ነች ነች ማለቱ ይቀላል፡፡

ሀገረ አሜሪካ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካካት ያላቸው ጎምቱ ፖለቲከኞች የሚገኙባት ሀገር ነች፡፡ ወግ አጥባቂ፣ አክራሪና ጽንፈኛ ፣ ለዘብተኛ፣ ሶሻል ዲሞክራትና የቀደመው የኮምኒስት አመለካከት አራማጆችም ከትመው የሚገኙት እዛው አሜሪካ ነው፡፡ ከአንድነት ኃይል እስከ መገንጠል ፖለቲካ የሚያራምደው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከሀገሩ በስደት ከወጣ በኋላ መኖሪያ ሀገሩ ያደረጋት አሜሪካንን ነው፡፡ስልጣን

በየሥርዓተ መንግሥስቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ የሲቪልና ወታደራዊ ከፍተኛ መሪዎች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተሰደው ቢኖሩም አብዛኛዎቹ የሚገኙት በአሜሪካን ነው፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከሀገር ቤት ውጭ ንዝረቱ ጎልቶ የሚሰማው በሀገረ አሜሪካ ነው፡፡

የሀገር ውስጥ ፖለቲካን ከውጭ መምራትና ውጤታማ ማድረግ ይቻላል ወይ ለሚለው ጥያቄ የየራሳችንን መልስ መስጠት እንችላለን፡፡ በዋናነት ግን ሕዝቡ በራሱ ተነሳሽነት ያደረገው የመብቴ ይከበርልኝ ጥያቄ፣ በኦሮሚያና በአማራው ክልል የተቀሰቀሰው ትግል ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩና ኢሕአዴግም ወስኖ በቁርጠኝነት መነሳቱ ነው ዛሬ የታየውን ለውጥ ያመጣው፡፡ የሀገር ቤት ፖለቲካ የሚመራው በሀገር ቤት በራሱ በሕዝቡ ለመሆኑም መልስ የሰጠ ይመስላል፡፡

በሀገር ቤት ሕዝቡ ያደረገው ትግል በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ በሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አልተመራም፡፡ ዛሬ የመጣው ለውጥ የተመራው በሕዝቡና በራሱ በኢሕአዴግ ለውጥ ፈላጊ አካላት ነው፡፡ ነገር ግን  በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የዲያስፖራው ሚና ቀላል ነበር ማለት አይቻልም ፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳይ በሀገር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ብቻ ሳይሆን በውጭ የሚገኙትንም ዜጎቻችንን ያለያያቸውና ያወካቸው እንደነበር የሚታመን ነው፡፡

የሀገር ውስጥ ፖለቲካ በፈጠረባቸው ብዥታ ምክንያትም የአንድ ሀገር ሰዎች በመጠላላት እርስ በእርሳቸው መወያየትና መነጋገር ተስኗቸው እንደነበር ለማየት ተችሏል፡፡ ስለ ሀገራቸው ያላቸውም አመለካከት የተለያና አንዱ የአንዱን ጉዳይ ጉዳዬ ነው የማይልበት ደረጃ ተፈጥሮ አይተናል፡፡  ያንን የጥላቻና በክፉ ዓይን የመተያየት መንፈስ ያፈረሱት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ ናቸው፡፡ ዜጎች  ከተዘበራረቀና ሺህ ቦታ ከተበታተነ አስተሳሰብ ወጥተው ስለአንዲት ጠንካራ ዲሞክራሲዊት ሀገር መፈጠርና  መጎልበት በስክነት ማሰብ የሚገባቸው ወሳኝ ወቅት ላይ እንዲደርሱ ተድጓል፡፡

እንደ ከዚህ በፊቱ መናቆሩ እርስ በእርስ መፋጀቱ ሀገሪቱን ለከፋ አደጋ የከተተበት ሁኔታ ዳግም ሊመለስ አይገባውም፡፡ በይቅርታና በፍቅር መደመር ማለት ከቂም በቀል ከጥላቻ ፖለቲካ መውጣት ከመናቆር መራቅ በሰለጠነ ፖለቲካ ልዩነትን ልዩነትን ይዞ ለጋራ ሀገር በጋራ ቆሞ ማለት ነው፡፡ ሀገሪቷን ለዘመናት ከገደላት ኃላቀር ፖለቲካ መላቀቅ ግድ ይላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አቢይ አሕመድ ይሄንን በተመለከተ ሁሉም በዲያስፖራ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ልዩነቱን አቻችሎ እርስ በእርስ መጠላለፉን አቁሞ ስለኢትዮጵያ ሲል በጋራ መስራት እንዳለበት የሰለጠነ የፖለቲካ ባሕል እየገነቡ መሄድ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ በአሜሪካን ሀገር ያደረጉት ጉብኝት እጅግ የተሳካ ከመሆኑም በላይ ለረዥም ግዜ በጥላቻ ፖለቲካ ይተያዩ የነበሩ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ሁሉ በአንድነት እንዲቆሙ ያደረገና የጥላቻውን ግንብም ያፈረሰ ነው፡፡

የመጀመሪው የጠቅላይ ሚኒስትር ጉብኝት በዋሽንግተን የነበረ ሲሆን ቀጥሎ በሎስ አንጀለስ የመጨረሻው ደግሞ በሚኒሶታ ነበር፡፡ የሆነውን ሁሉ ለማመን በሚያስቸግር መልኩ አዲስ ታሪክ የተሰራበት ኢትዮጵያውያን በፍቅርና በአንድነት የቆሙበት በጋራ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለአቶ ለማ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ ድጋፋቸውን ያሰሙበት መድረክ ነበር፡፡ ዝግጅቱና የዲያስፖራው አቀባበል የነበረው የጠለቀ የድጋፍ ስሜት ሕዝቡን በእንባ ያራጨ ያስፈነደቀም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ አንድ መሪ በውጭ ሀገራት ጉብኝት ያውም በአሜሪካ ከዚህ ቀደም የጋለ ተቃውሞዎች በሚሰሙበት ምድር ይህን የመሰለ ታላቅ  ድጋፍና አድናቆትን አግኝቶ በከፍተኛ ተቀባይነት የተስተናገደበት ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ  በአሜሪካ ሀገር ያደረጉት ጉብኝት በአይነቱ የተለየ ከመሆኑም በላይ ለሀገራችን በተለይም ለመንግስት ከፍተኛ ዲፕሎማሲዊ ድሎችን ያስገኘ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በአሜሪካን ተገናኝተው የተወያዩበት ቀን በከተሞቹ የኢትዮጵያውያን ቀን ሆኖ እንዲከበር በዋሽንግተን ከንቲባዋ መወሰናቸውና ይህንንም ይፋ ማድረጋቸው ስኬታማ ዲፕሎማሲን ያረጋገጠ ነው፡፡ በቅርቡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውን ከአሜሪካም ሆነ ከሌሎች ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ይጠበቃል፡፡ ለበርካታ አመታት የዘለቀ የሀገርና የቤተሰብ የወዳጅ ናፍቆት በውስጣቸው ሲመላለስ የኖረ እንደነበር የሚታወቅ እውነት ነው፡፡

ወገኖቻችን ወደ ሀገራቸው ተመልሰው የመሥራት ፍላጎትና ጉጉቱ አላቸው፡፡የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአሜሪካ ጉብኘት ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት የተገኘበት የሻከሩ የብዙ ዜጎች ልቦች በፍቅር በምሕረት በወንድማማችነት ስሜት የተሞሉበት ሳይነጋገሩ ለአመታት ተራርቀው በጥላቻ መንፈስ ሲተያዩ የነበሩት  የጠላትነት ስሜታቸውን አስወግደው በአንድ የተደመሩበት በፍቅርና በልዩ ስሜት የታደሙበት ነበር፡፡

በአሜሪካ በርካታ አመታትን አስር ሀያ ሰላሳና አርባ አመታት የኖሩ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ሀገራቸውን በአላቸው አቅም ሁሉ ለመርዳት ቃል ገብተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዲያስፖራ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን በቀን እንኳን ለሚኪያቶ ከሚያወጡት ወጪ አንድ ዶላር ወደ ሀገርቤት ቢልኩ ብለው ጠይቀው ነበር፡፡ በተደረገው ጥሪ መሰረትም እያንዳንዱ ዲያስፖራ በቀን እስከ አስር ዶላር ድረስ ሊያዋጣ እንደሚችል በተወካዩ አማካኝነት ምላሹን ሰጥቷል ማስተባበር፡፡

በአሜሪካን ሀገር በተለያየ የሙያ ዘርፍ ተሰማርተው የሚሰሩ አንቱ የተባሉ ምሁራን አሉ፡፡እነዚህ ሁሉ ለሀገራቸው ሀብት ናቸው፡፡ በብዙ መልኩ ለእናት ምድራቸው ከድህነት መውጣት የገዘፈ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ፤ አቅሙም አላቸው፡፡ የነዚህ ሁሉ አስተዋጽዖና የተፈጠረው የሰላምና የመግባባት መንፈስ ሀገራችንን ወደተሻለ ምእራፍ እንደሚያሸጋግራት ይታመናል፡፡

አሁን ባላቸው ሙያና ኢኮኖሚያዊ አቅም አገራቸውን ለማሳደግ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸዋል፡፡  ይህን ወርቃማ አጋጣሚ ተጠቅመው በሀገራቸው ላይ በብዙ መስክ ኢንቨስት ማድረግ ይችላሉ፡፡ አዳዲስ ቴኬኒዮሎጂዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት፤የትምህርት ጥራትን የበለጠ ለማሻሻል ተግተው በመስራት ብቁ ትውልድ የመቅረጽ ስራና ኃላፊነትን የመወጣት፤ በጤናው፤ በምርምሩ በግብርናው በአቪየሽኑ በከተሞች ልማት በብዙ መስኮች የሚሰሩበት እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ጊዜው የፍቅር የመግባባት የእርቅና የምሕረት ሀገርንም በጋራ የማሳደግ  በመሆኑ ከጥላቻና ከቂም በቀል ፖለቲካ በመውጣት አንዱ ሌላውን በጠላትነት ከመፈረጅ በሽታ በመላቀቅ በአዲስ አስተሳሰብ የትላንቱን ውደቀትና ያስከተለውን አካሄድ በመቀየር በአዲስ መንፈስ ለሀገር መቆምና መስራት ያለብን ግዜ ዛሬ ነው፡፡

ያለፉት ታሪኮቻችን በመናቆርና እርስ በእርስ በመባላት የተሞሉ በመሆናቸው ያተረፉልን መዋረድን ስደትን  ወንድም ወንድሙን ማጥፋትን በመሆኑ ሊደገሙ አይገባም፡፡ ከዚህም በላይ እኔ ብቻ ነኝ ትክክል የሌላው ሀሳብ ትክክል አይደለም፤እኔ ብቻ ነኝ የሀገር ተቆርቋሪና አሳቢ ከእኔ ከእኛ በላይ ለሀገር አሳቢና ተሟጋች የለም የሚለው እጅግ ኋላቀር አስተሳሰብ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ እንደማያስብ አድርጎ የመሳልና የመውሰድ እሳቤ ብዙ ጉዳት አስከትሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአሜሪካ  ከሚገኘው ዜጋችን ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ የዲያስፖራው አመለካከት በብዙ መልኩ እየተለወጠ በመምጣት በሀገራዊ ጉዳዮቻችን ዙሪያ ከመንግሥት ጋር በጋራ እየመከረ የሀሳብ፣ የሙያና የፋይናንስ ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡