የጥላቻ ምዕራፍ ተዘግቶ የፍቅርና የመደመር ዘመን መጥቷል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያን የመምራት ኃላፊነት በይፋ ከተረከቡበት ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ በሦስት ወራት ቆይታቸው በየአገሪቱ ክልሎች በመዘዋወር ባደረጓቸው ንግግሮች ከአገሪቱ ህዝብ ውስጥ ቂምና ቁርሾ እንዲጠፋ የበኩላቸውን ተወጥተዋል፡፡ እስረኞችን በማስፈታት፣ ነፍጥ ያነገቡ ኃይሎች ወደ ሠላማዊ ትግል እንዲመለሱ በማድረግም የሚያሰመሰግን ሥራ ሰርተዋል፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለዓመታት የቆየው ጥላቻና ቂም በቀል ወደ ሠላም እንዲቀየር የጀመሩት ጥረትና እያስገኘ ያለው ውጤት መልካም መሆኑ ለማንም ግልፅ ሆኖ የሚታይ ነው፡፡

የኤርትራ ልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ሠላም ለመውረዱ አመላካች እርምጃወች መታየታቸው ከሳቸው የጎመራ ፍሬ ነው፡፡ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ነፃነት እንዲሰማቸው ባደረጉት ማነቃቃት የታየው ተስፋ ሰጪ ብርሐን ከየትም የመጣ አይደለም፡፡

መላ የአገሪቱ ዜጎች በይቅርታና በፍቅር እንጂ በፀብ እንዳይፈላለጉ በሰጡት የማይታክት ማሳሳቢያ፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውን አገራቸው ገብተው በነጻነት እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረባቸው፣ መንግሥት ሲፈጽማቸው የኖሩትን በደሎችና ህገ-ወጥ ተግባራት በአደባባይ በማጋለጥ ይቅርታ መጠየቃቸው፣ ወዘተ የህዝብ ፍቅርና አክብሮትን አስገኝቶላቸዋል፡፡ ከዚህ በፊት ፍጹም ሊታሰብ የማይችል ለውጥ በአገሪቱ በሠላማዊና በሰለጠነ መንገድ እውን እንዲሆን ላደረጉት አስተዋጽዖም፣ በመላ አገሪቱ ሕዝብ በድጋፍ ሰልፍ እውቅና እየሰጣቸው ይገኛል፡፡ ይህ ዕውቅናም የበለጠ እንዲሰሩና የህዝብ ድጋፍ እንደማይለያቸው ማሳሰቢያ ሆኖ ይቆጠራል፡፡ የሠራ ሲሞገስ እጅግ በጣም ደስ ይላል፡፡ ሌሎችም ትምህርት ወስደው በሚሰሯቸው መልካም ሥራዎች የህዝብ ድጋፍ እንደማይለያቸው እንዲገነዘቡ ያደርጋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በተለያዩ ስፍራዎች ተገኝተው ባደረጓቸው ንግግሮች አጽንኦት የሰጡት ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንደሚያስፈልጋት ነው፡፡ ይህ ምኞት ዕውን የሚሆነው ደግሞ ኢትዮጵያውያን ከበቀልና ከጥላቻ ነጻ ሆነው በአንድነት ሲቆሙ ወይም በእርሳቸው አባባል ሲደመሩ ነው፡፡ ይህ አንድነት በብሄር፣ በእምነት፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካዊ አቋምና በመሳሰሉት ልዩነቶች ችግር እንዳይገጥመው በተደጋጋሚ አሳስበዋል፡፡ በተለይ በደቡብ ክልል በሀዋሳ፣ በወላይታና በወልቂጤ ከተሞች ከህዝብ ጋር መሰንበቻውን ባደረጓቸው ውይይቶች ኢትዮጵያውያን የሚያምርባቸው በአንድነት ሲቆሙ እንጂ ተለያይተው ሲጠፉ እንዳልሆነ አስረግጠው አስገንዝበዋል፡፡ ከሀገር ውስጥ አልፎ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ እያመጡት ባሉት ለውጥ በተለያዩ የሀገር መሪዎች እንዲሁም የአለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀር ሙገሳና ክብር ተችሯቸዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ የጎረቤት ኬኒያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ አንዱ ናቸው፡፡ ፕሬዝዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሀገሪቱን ስልጣን ከያዙ ወዲህ በዚህ አጭር ጊዜ በአገሪቱ መተማመንና አንድነትን ያመጡ መሪ በመሆናቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል ሲሉ መስክረውላቸዋል፡፡ የኡጋንዳና የሩዋንዳ ፕሬዝዳንቶች በተመሳሳይ የጠቅላይ ሚኒስቴሩ የይቅርታና የአንድነት መርህ በአገሪቱ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን አመላካች ነው ሲሉ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሀላፊ ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ በምስራቅ አፍሪካ በመተሳሰብና በመቻቻል በአንድ ልብ ለሰላምና ለልማት የሚያስቡበትን መንፈስ የዘሩ መሪ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ታዋቂነት ያላቸው ትልልቅ ሚዲያዎችም ስለጠቅላይ ሚኒስትራችን የለውጥ እንቅስቃሴ በስፋት እየዘገቡ ይገኛሉ፡፡ ለአብነትም የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ እየወሰዷቸው ባሉ አውንታዊ እርምጃዎች በእጅጉ ተበረታተናል ሲሉ በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ማይክ ሬነር ማስታወቃቸውን ዘግቧል። ኢትዮጵያ አሳሳቢ ለሆኑ ጉዳዮች ምላሽ ለመስጠት እና እያደረገች ያለችውን ጥረት ለመደገፍ፣ ሀገራቸው የምትችለውን ሁሉ እንደምታደርግም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል ያለውዘገባው "ሁሌም የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት አቋም የነበረው እና አሁንም የቀጠለው ለአጋርነታችን ይበልጡንም ደግሞ ለሕዝቧ ጥቅም ሲባል፣ ኢትዮጵያ ጠንካራ፣ የተረጋጋች እና የበለፀገች እና ስኬታማ አጋራቸን እንድትሆን ፍላጎታቸን ነው" ማለታቸውንአስደምጧል።       

Reuters Xinhuaን ጨምሮ በርካታ መገናኛ ብዙሃን የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ መሪዎች በኢትዮጵያ መንግስት አደራዳሪነት በአዲስ አበባ ፊት ለፊት ተገናኝተው መምከራቸውን የተመለከተ ዘገባን አቅርበዋል። የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር እና የቀድሞ ምክትላቸውን እና ተቀናቃኙ ዶ/ር ሪክ ማቻር በአዲስ አበባ ተገናኝተው መምከራቸው የኢትዮጵያው ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጥረት ከፍተኛ እንደነበር መገናኛ ብዙሃኑ በዘገባዎቻቸው አስታውቀዋል።            

ርዮተርስ የቀድሞው የብሄራዊ ፕላንኮሚሽን ሃላፊ ዶ/ር ይናገር ደሴ የብሄራዊ ባንክ መሪ ሆነው መሾማቸውን ዘግቧል። የቀድሞ የባንኩ ፕሬዝዳንት በምን ምክንያት ከሃላፊነታቸው እንደተነሱ አልተገለጸም ያለው ዘገባው ይህ የስልጣን ለውጥ ባለፉት ወራት እየተካሄደ የነበረው የመተካካት ሂዳት አንድ አካል ነው መባሉን ጠቁሟል።        የአገር መሪ ህዝቡን መስሎ መኖር የሚችለው ህዝቡን በሚገባ ሲያውቀው ነው፡፡ ይህ እውቀት የተገኘው ደግሞ በባልስጣናት በሚቀርብ ሪፖርት ሳይሆን ከበፊት ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች ከህዝብ ጋር በነበራቸው ጥልቅ ግንኙነት እንደሆነም አጠቃላዩ ሁኔታ ያስገነዝባል፡፡ ህዝቡን በዚህ ደረጃ የሚያውቅ መሪ ሲገኝ ተመስገን ማለት ብቻ ሳይሆን እውቅና ሰጥቶ ማሞገስ ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለዥም ዘመናት ያጣችው ይህንን የመሰለ ጸጋ ነበር፡፡

በመጨረሻም አገራችን መልካም አጋጣሚዎች እጇ ውስጥገብቷል፡፡ በዚህች ታሪካዊት አገር ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከመገንባት ታልፎ ምስራቅ አፍሪካን ከጦርነት፣ ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት ማላቀቅ የሚያስችል ታላቅ እምቅ ሃይል አለ፡፡ ኢትዮጵያውያን ስንከበር፣ ስንፈላለግና ለአገራችን እድገትና ብልፅግና አንድ ላይ መቆም ስንችል ተዓምር መፍጠር እንደምንችል ታላቁ የአድዋድል ምስክር ነው፡፡

ስለሆነም ኢትዮጵያውያን አንድ ላይ ስንቆም እንዲህ አይነቱን አንጸባራቂ ድል በዚህ ዘመንም ማስመዝገብ እንደምንችል ማንም መጠራጠር የለበትም፡፡ ስለዚህ ጊዜው የመደመርና የመተሳሰብ በመሆኑ እኛ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ጥላቻን፣ ቂምን፣ በቀልን፣ ሴራንና አሻጥርን በማስወገድ ለታሪካዊቷ አገራችን ወደ ተሻለ የሰላምና የልማት ምዕራፍ ለማሻጋገር በፍቅርና በአንድነት ጠንክርን መስራት ይኖርብናል፡፡