ወደ ተግባር እንቀይረው…

የሚነገር ነገር ሁሉ እውነት ላይሆን የሚችልበት አጋጣሚ በርካታ ነው። ፍሬውን ከእንክርዳዱ በሰከነ መንገድ መለየት ይገባል። አሊያ ስህተት ላይ መውደቅ ሊመጣ ይችላል። በተለይ ህብረተሰቡ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የሚናፈሱ ውዥንብሮችን ከትክክለኛው ምንጭ ካልሆነ በስተቀር መስማት የለበትም። ግድቡ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን በተግባር ያሳየበት፣ እያንዳንዱ ዜጋ አሻራውን ያሳረፈበት አገራዊ ፕሮጀክት በመሆኑ ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው። የሚስተጓጎልበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም።

በቅርቡ በግድቡ ግንባታ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ላይ የተፈጸመው አሳዛኝ ግድያ መላው ህዝባችን ግድቡን ከፍፃሜ ለማድረስ በአንድ ቃል ቁጭቱን በአደባባይ ሲገልጽ ተስተውሏል። የግድያውን ሁኔታ ፖሊስ አጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል። እስከዚያው ድረስ ግን እየተስተዋለ የሚገኘው ህዝባዊ እልህ እና ቁጭት ወደ ተግባር መለወጥ ይኖርበታል። በመሆኑም ይህን እልህ እና ቁጭት ወደ ተግባር ለመቀየር ህብረተሰቡ ለግድቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ ከምንግዜውም በላይ አጠናክሮ መቀጠል የሚኖርበት ይመስለኛል።

የግድቡ ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። የሚሰራውም እርሱው ነው። ለፍጻሜ እንዲበቃ የሚያደርገውም እርሱ ነው። ሌላ ማንም አይደለም። የኢንጅነር ስመኘው አሳዛኝ ሞት ልብ የሚነካ ቢሆንም፣ ግድቡ አሁን ከሚገኝበት ቦታ ከፍ ለማድረግ የተያዘው እልህና ቁጭት ለላቀ ድጋፍና ስራ የሚያነሳሳን ነው።

ቁጭታችንን የምንወጣው ግድቡን ከምንግዜውም በላይ በአንድነት መንፈስ ውስጥ ሆነን ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት ነው። በለውጥ ሂደት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ማድረግ የሚሳነው አይደለም። ምክንያቱም የፈጠረው ለውጥ ልማትን ለማምጣትና ድህነትን ለመቀነስ እየሰራ የሚገኝ በመሆኑ ነው።

በግድቡ ላይ የምናደርገው ርብርብ እኛም ሆንን ጎረቤቶቻችን ከግድቡ የምናገኛቸውን ጥቅሞች የሚያረጋግጡ ናቸው። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ግድቡ በሚገባ ተሰርቶ ሲጠናቀቅ በሙሉ ሃይሉ ስድስት ሺህ አራት መቶ ሃምሳ ሜጋ ዋት ያመነጫል። ይህም ለበርካታ ዓመታት ያህል በቀን ሁለት ሚሊዮን ዮሮ እንድናገኝ የሚያደርገን ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪካዊነቱ ያስቀመጠውን ሁለንተናዊ አሻራ ተመልሶ የታሪካዊ ዕድገት ተጠቃሚ እንዲሆን የማድረግ ሚና ያለው ነው፤ ግድቡ።

የህዳሴው ግድብ በመገንባት ላይ የሚገኘው በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ላይ ተመስርቶ መሆኑ ይታወቃል። ግድቡ በአገር ውስጥ ድህነትን ለመቀልበስ በአዲስ ኢትዮጵያዊ አንድነትና ለውጥ ለተነሳው ህዝብ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ነው።

ግድቡ የማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ሰርተን ልንለወጥ እንችላለን የሚል ፍላጎት ያናረ ነው። ከራሳችን አልፈን ለጎረቤቶቻችን እንድንተርፍም የሚያደርገን ነው። እናም እነዚህ ሁኔታዎች ብቻ የአገራችንን ፍትሐዊ አመለካከት የሚያንጸባርቁ ናቸው።

አዲሲቷ ኢትዮጵያ ሐብትን በጋራና በፍትሐዊ ሁኔታ የመጠቀም መርህን ተከትላ የህዳሴውን ግድብ እየገነባች ነው። የምትገነባው የሌሎችን መብትና ተጠቃሚነት ለመንካት አይደለም።

በተለይ ግድቡም ወንድም የሆነውን የግብፅ ህዝብ እንደማይጎዳ፣ ይልቁንም ኢትዮጵያ ከግድቡ ግንባታ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ እንደምትቀይስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለግብፅ ህዝብ አስረድተዋል።

ይህም ከዚህ በፊት በግብፅ በኩል የነበረውን ያለመተማመንና የጥርጣሬ መንፈስን ብእጅጉ የቀየረ ነው። መተማመንና በጋራ መስራት የሚያስችልን አዲስ አስተሳሰብ በግልፆች በኩል የፈጠረ ነው። ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊመሰገኑ ይገባል።

እርግጥ አገራችን የትኛውንም ወገን ያለመጉዳት መርህዋን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት መንግስታትና ህዝቦች አስረድታለች። የኢትዮጵያ ህዝቦች የትኛውንም ሀገር የመጉዳት ዓላማ እንደሌላቸው የምስራቅ አፍሪካና የተፋሰሱ አገራት ተገንዝበውታል።

አሁን በተፈጠረው ቁጭት እንደ ህዝብ ስራችንን መስራት ይኖርብናል። እኛ ኢትዮጵያዊያን በታሪካችን የየትኛውንም ሀገር መብት የማንጋፋ ከህዝቦች ጋር ተባብረን የምንኖር ነን። ይህ ህዝባዊ እምነታችን በመንግስታችን ፍትሐዊነትን ዕውን በሚያደርገው ህዝባዊ ለውጥ የታጀበ ነው። ዋነኛው ጠላታችን ድህነት በመሆኑ ይህን ጠላት መቅረፍ በሚችሉ ፕሮጀክቶች ላይ ሁሉ ልንረባረብ ይገባል።

ግድቡን የምንገነባው ይህን ጠላታችንን ድል ለመንሳት እንጂ የትኛውንም ወገን ለመጉዳት እያሰብን አይደለም። ግድቡ ህዳሴያችንን የምናረጋግጥበት አንድ ማሳያ ስለሆነ እንጂ በየትኛውም ወገን ላይ ችግር ለመፍጠር አይደለም።

እርግጥ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ለአፍሪካ ቀንድም ሆነ ለመላው አፍሪካ ህዝቦች ሰላም፣ መረጋጋትና ብልፅግና የሚጨነቁና ለዚህም ተግባራዊነት የህይወት መስዕዋትነት ጭምር እየሰጡ የሚተጉ እንዲሁም የዓባይን ወንዝ በተመለከተ የተፋሰሱ አገራት ፍትሃዊነትና እኩል ተጠቃሚነት በፅናት የሚቆሙና ሃላፊነት የሚሰማቸው ናቸው።

ይህን እውነታም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ግብፅን በጎበኙበት ወቅት ደግመው ደጋገመው ለግብፅ ህዝብ አስገንዝበዋል። የሚፈለገው መግባባትም ላይ ተደርሷል። ከዚህ በፊት የነበረውን ጥርጣሬን ተወግዶ አብሮ ተያይዞ የማደግ መንገድ ተቀይሷል።

እርግጥ ኢትዮጵያዊያን የአንዱ ማደግ የጎረቤታችንም አብሮ መመንደግ ብለው የሚያስቡ ናቸው። የአንዱ መውደቅም የሌላው አብሮ የቁልቁለት ጉዞ መያያዝ መሆኑም እንዲሁ ይገነዘባሉ። እናም እንኳንስ ከጎረቤቶቻችን ጋር ቀርቶ በሩቅ ሆነው ከእኛ ጋር አብረው ለማደግ ለሚሹ አገራትም ቢሆኑ የእኛ ብልፅግና ለእነርሱ ጉዳያቸው መሆኑ አያጠያይቅም።

ይህን ሃቅ የሚገነዘቡት የኢፌዴሪ መንግስትና ህዝቡም የሀገራቸው መፃዒ ዕድል ከሌሎች ጋር የተቆራኘ መሆኑን ያምናሉ። እናም በሀገር ውስጥ ለማደግ የሚያደርጉት ጥረት ምን ያህል ፍትሃዊ፣ ምን ያህል ሌሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በማጤን ተግባራቸውን እየከናወኑ ይገኛሉ።

በመሆኑም አሁን በምንገኝበት የለውጥ ሂደት ውስጥ የተፈጠረው ቁጭትና እልህ ግድቡን በሚፈለገው ፍጥነት ለመፈጸም የሚያስችለን ነው። ስለሆነም እልሁንና ቁጭቱን ወደ ተግባር በመቀየር የግድቡን ግንባታ ልናፋጥንበት ይገባል።