ስርአተ አልበኝነት ሀገር ያጠፋል

ሕግ ስርአትና መንግስት ባለበት ሀገር ከሕግ ውጭ የሆኑ ሕግን የሚያፈርሱ ድርጊቶች በስፋት እየታዩ ይገኛሉ፡፡የተጀመረውን በሕዝብ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ የኢሕአዴግ የተሀድሶ የለውጥ ሂደት (ሪፎርም) በቅጡ ካለመረዳት የተነሳ የተመሰቃቃሉ ሁኔታዎች እየተከሰቱ ማየት የተለመደ ሆኖአል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ የመደመር ለውጥ እሳቤ የትላንቶቹ ሀገራዊ የፖለቲካ ታሪኮቻችን በሙሉ አልበጁንም ስለዚህ ያለፈውን ምእራፍ ዘግተን በይቅርታ በምሕረት በፍቅር በመቻቻል ለሀገራችን የሚበጅ አዲስ ለውጥ እናምጣ ነው መሰረታው አላማው፡፡ የኃላ ታሪኮቻችን በሙሉ እርስ በእርስ የመናቆር የመባላት የመጠፋፋት የመገዳደል አስከፊ ታሪኮች ስለነበሩ ለሀገር ያስገኙት ለውጥና ትሩፋት የለም፡፡

በዚህ አይነቱ ጎራ ለይቶ የመባላት ትንቅንቅ ለሀገራችን የተሻለ ስራ መስራት ይችሉ የነበሩ አዋቂዎች ጠፍተዋል፡፡ከዚህ አስከፊ ታረክ እንደ ሀገር እንደ ሕዝብ እንውጣ፤ ነገን የተሻለ ለማድረግ ልዩነቶቻችንን በልዩነት ይዘን የጋራ በሚያደርገን ሀገራዊ ጉዳይ ላይ እንስራ የተሻለች ሀገር እንፍጠር ነው ዋናው መልእክቱ፡፡

አሁን በሚታየው ተጨባጭ ሁኔታ የተገኘው ለውጥ ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተደረጉት የመብት ጥያቄዎች በከፍተኛ ደረጃ እያደጉ ሄደው ገዢው ፓርቲ እራሱን በጥልቀት እንዲፈትሽ ከፍተኛ ግፊትና ጫና አሳድረዋል፡፡  ኢሕአዴግ ረዥም ግዜ በፈጀ ስብሰባና ግምገማ ተወያይቶ ስሕተቶቹን ተቀብሎ በአደባባይም ለሕዝብ የተሰሩትንና የተፈጸሙትን ስሕተቶች ሁሉ ወደራሱ ወስዶ  ይቅርታ ጠይቆአል፡፡ሕዝቡን ለመካስ እሰራለሁ ብሎ በአደባባይ ካወጀ በኃላ አቶ ኃይለማርያም ለቀው ዶ/ር አቢይ አሕመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተመረጡ በኃላ እስከዛሬ ባሉት የሶስት ወራት ግዜዎች ውስጥ እጅግ ስርነቀል የተባሉ የሚታዩ የሚጨበጡ ለውጦችን መርተዋል፡፡

በድርጅታቸው ውሳኔ መሰረት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ እስረኞች ተፈተዋል፡፡ፖለቲከኞች ታዋቂ ሰዎች ጋዜጠኞች ወዘተ፡፡ይህም ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ታስቦ የተሰራ ስራ ነው፡፡በሀገር ውስጥም በውጭ ያስፖራው ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘ አድናቆትም ያተረፈ ተግባር ነው፡፡በሁሉም ክልሎች ሕዝቡን ተዘዋውረው አነጋግረዋል፡፡በጎረቤትና በአረብ ሀገራት ጉብኝት አድርገዋል፡፡አሜሪካም በመሄድ በዲያስፖራ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን አነጋግረዋል፡፡

በአሜሪካው ጉብኝታቸው ለረዥም ዘመናት የዘለቀው የጥላቻ ግንብ እንዲፈርስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በመግባባት በውንድማማችነት ስሜት ተቀራርቦ ከጥላቻ ወጥቶ በጋራ ለሀገሩ እንዲያስብ እንዲሰራ በሩን ከፍተዋል፡፡የዲያስፖራ ፈንድ አሰባሳቢ ኮሚቴ ታዋቂ የሆኑ የፖለቲካ ሰዎች ምሁራን አክቲቪስቶች ያሉበት ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቶአል፡፡ ከኤርትራ ጋር የነበረውን ሰላምም ጦርነትም የለም በሚባለው የድንበር ፍጥጫ ተጎጂዎቹ ሕዘቡና ሀገራቱ መሆናቸውን በማመን ችግሩ በሰላም እንዲፈታ በማድረግ ከኤርትራ ጋር ስምምነት ላይ ተደርሶአል፡፡

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርትራን ከጎበኙ በኃላ የኤርትራው ፕሬዚደንት ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል፡፡የነበረው ውጥረት እንዲረግብ ተደርጎ ሰላማዊ ግንኙነት ተጀምሮአል፡፡በስደት የነበሩት ጳጳስ እርቅ ተደርጎ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡በውጭ ሀገር በፖለቲካ ምክንያት ተሰደው ይኖሩ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎቻቸው በእርቅና በምሕረት አዋጁ መሰረት ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ተደርጎአል፡፡የገቡ አሉ፡፡  እየገቡም ነው፡፡በውጭ የሚገኙ የተቃዋሚ ሚዲያዎች ወደ ሀገራቸው እንዲገቡና እንዲሰሩ በተፈቀደው መሰረት የገቡ አሉ፡፡የሚገቡም ይኖራሉ፡፡እነዚህ ሁሉ ግዙፍ ታላላቅ ለውጦች የተመዘገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ ስልጣን ከያዙ ሶስት ወራት ባልተቆጠረ ግዜ ውስጥ ነው፡፡

ቀደም ሲል በነበረው ልምድና ተሞክሮ የማይቻሉ የማይታሰቡ የማይገመቱና ይሆናሉ ተብለው የማይታመኑ ምናልባትም ረዥም አመታትን ወስደውም የማይሳኩ ሳይሳኩም የኖሩ ሕልም የሚመስሉ ስራዎች በአጭር ግዜ ተከውነዋል፡፡ይህንን ድንቅ የሆነ የለውጥ ድል ጠብቆ መራመድ የሕዝብና የሁሉም ዜጋ የጋራና የተናጠል ኃላፊነትም ጭምር ነው፡፡ ይህንን ለውጥ ጠብቆ አለመጓዝ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ሕዝብ እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል፡፡

በአሁኑ ሰአት የተሀድሶ ለውጡን ለማደናቀፍ በተለያዩ አካባቢዎች እየታዩ ያሉት  ግጭቶች በሶማሊያ ጅጅጋ የታየው አሳፋሪ ክስተት፤በጉጂ ዞን የደረሰው ግዙፍ መፈናቀል፤ በሻሸመኔ በቅርቡ በመንጋ ፍርድ በአደባባይ እንዲሰቀል የተደረገው ሳልቫጅ ሸጦ የሚኖር ወጣት አሳዛኝ ሞት፤ቀደም ሲልም ሕዝብ በሚዘዋወርበት አደባባይ መኪናው ውስጥ ተገድሎ የተገኘው የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት፤ በቴፒ ሰሞኑን የተካሄደው ግጭትና የደረሰው መፈናቀል፤ከውጭ ወደ አዲስ አበባ ሊገቡ ሲሉ በሕዝብ ጥቆማ በየግዜው የተያዙት የጦር መሳሪያዎች ቁጥር መጨመር ፤ሰሞኑን 2000 ሽጉጦችና ጥይቶቻቸው በቦቴ ተጭነው አዲስ አበባ ሊገቡ ሲሉ መያዛቸው ስርአተ አልበኛነት በሀገር ደረጃ በእጅጉ እየሰፋ ለመሆኑ ተጨባጭ ማስረጃዎች ናቸው፡፡

ከውጭ እንዲገቡ የተደረጉት ወይንም በመምጣት ላይ ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአክቲቪስቶቻቸው አማካኝነት የጀመሩት የማሕበራዊ ሚዲያ ጦርነት መወነጃጀል መነቃቀፍ ዛቻና ስደብ ከብዙው በጥቂቱ ሲታይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎና ቅን አመለካካት ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም ካላቸው ጽኑ ፍቅርና ምኞት ከመደመር ለውጡ ጋር ሙሉ በሙሉ የማይሄድ እንዲያውም የኃሊት ጉዞና ጨለማ ውስጥ እንዳንገባ የሚያስጠነቅቅ ክስተት ነው፡፡

የዲሞክራሲ ባሕልን በመገንባት ረገድ ገና ነን፡፡ብዙ ይቀረናል፡፡ነጻነት ማለት የራስንም የሌላውንም ነጻነትና መብት ማክበር ነው፡፡የተገኘውን አንጻራዊ ነጻነት በአግባቡ ለመጠበቅ የማንችል መሆናችንን በአደባባይ እያሳየን ነው፡፡ከሕግና ከስርአት ውጪ በሆነ መንገድ በጎበዝ አለቆች ፍርድና ውሳኔ ንጹኅን ዜጎች እየተገደሉ ነው፡፡በመንጋ እሳቤና ፍርድ በስሜታዊነትና በጀብደኝነት ሕግና ስርአትን ሕገመንግስቱን እየናዱ በመሄድ ሕግና ስርአት እንዲፈርስ ስርአተ አልበኝነት እንዲነግስ እየተደረገ ነው፡፡ዲሞክራሲ ለእኛ አይመጥነንም እያልን ነው፡፡እንደ ሀገር ያሳፍራል፡፡ያሳዝናልም፡፡

በቅርቡ ታዋቂው ጸሀፊ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ነጻነትን በአግባቡ መጠቀም ካልቻልን ባርነት ለዘለአለም ይኑር ሲል ጽፎአል፡፡ ወዶ አይደለም፡፡ሕዘብ ነው መሪዎችን እየገፋ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ የሚወስዳቸው፡፡አምባገነን እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው፡፡ነጻነቴና የዜግነት መብቴ ተገፎአል ብሎ ሲታገል የነበረ ሕዝብ የለውጥ መንገድ ሲጀመር ነጻነትን  የሚያጠፉ ስራዎች ውስጥ ከተሰማራ መንግስት ለሀገርና ለሕዝብ ሰላምና ደሕንነት ሲል  የመንጋ  አስተሳሰብና ድርጊት  የሚያስከትለውን  ውድመትና ጥፋት የዜጎችን ሕይወት ከአደጋ ለመከላከል የሀገርን ሀብትና ንብረት ለመጠበቅ ሲል በአለበት ሕገመንግስታዊ ኃላፊነት መሰረት የማያወላዳ እርምጃ ወደ መውሰዱ ይገባል፡፡

መንግስት ሀገር ስትጠፋና ስትወድም ንጹሀን ዜጎች በግፍና በገፍ  ሲፈናቀሉ ሲገደሉ ቤትና ንብረት ሲወድም በዝምታና በአርምሞ መመልከት አይችልም፡፡መንግስት ሕግና ስርአትን የማስከበር ቀዳሚ ተግባሩን ይወጣል፡፡በዚህ ሂደት የተሳተፉ መሪ ተዋናዮች ለሕግና ለፍትህ እንዲቀርቡ ያደርጋል፡፡በዚህ የሀገርን ሰላም የማስከበር ሂደት እንደገና ደግሞ ታሰርን ተንገላታን መብታችን ተነፈገ የሚል ጩሀት መሰማት ይጀምራል፡፡ ወንጀለኞች በሕግ አይጠየቁ፤ አይታሰሩ፤ አይመርመሩ፤ ለፈጸሙት ድርጊት ፍርድ አይሰጣቸው የሚል ሕግ በአለም ላይ የለም፡፡ማንም ከሕግና ከስርአት በላይ መሆን አይችልም፡፡ለዚህም መንግስት በትጋት ሕግና ስርአት ሕገመንግስቱ እንዲከበር ከሕዝቡ ጋር በመሆን ይሰራል፡፡

መንግስትም ሆነ ሕዝብ ስርአተ አልበኝነት ሲንሰራፋ ቆሞ መመልከት አይችልም፡፡  የጀማ ፍርድ ከጅምላ የመንጋ አስተሳሰብ የሚመነጭ በስሜታዊነት በጥላቻ የተሞላ ሕግና ስርአትን የጣሰ እርምጃ ነው፡፡እጅግ ኃላ ቀርና በጥንት ዘመን የቀረ አስተሳሰብ ነው፡፡ ግለሰብም ሆነ ግለሰቦች ጥፋት ከተገኘባቸው የሚጠየቁት የሚዳኙት በሕግና በሕግ ብቻ ነው፡፡

ሕብረተሰቡ በሰላሙ ላይ አደጋ የሚያደርሰውን ማንኛውንም ጉዳይ በጥብቅ በመከታተል ከነማስረጃው ይዞ ለሕግ አስከባሪ ፖሊሶች የመስጠት በዚህም በሕግ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራው እንዲጣራ ጉዳዩ በፍርድቤት እንዲታይ የሚያደርግ ሕግ አለን፡፡ሕገመንግስት አለን፡፡በየመንደሩ የተሰባሰቡ ወጣቶች ለውጡን እንደግፋለን በሚል ግርግር ቦምብ ይዞአል፤ተገኝቶበታል በሚል ዜጋን የመደብደብ፤ የመግደል በአደባባይ እንጨት ላይ የመስቀል መብት የላቸውም፡፡አይችሉም፡፡የወንጀልም ወንጀል ነው፡፡ለሕግ አስከባሪ አካላት ከነማስረጃው ማስረከብ ብቻ ነው የሚችሉት፡፡

ከኢትዮጵያዊነት ባሕልና ስነምግባር ጨዋነት ውጭ ያፈነገጠ እንደ ሀገር ሕዝብን አንገት  ያስደፋ ያስለቀሰ አረመኔያዊ ድርጊትና ወንጀል ነው የተሰራው፡፡ኢትዮጵያውያን አይሲሶች ተፈጥረዋል ውስጥ ለውስጥም አሉ ማለት ነው፡፡ይሄን ድርጊት ሕዝብና መንግስት በጋራ በመሆን ታግለው ያሸንፉታል፡፡ሀገር ከሕግና ከስርአት ውጭ ልትመራ አትችልም፡፡

ሕግና ስርአት ካልተከበረ ሀገር የለም፡፡የስርአተ አልበኞች የመንደር ጉልበተኞች በየከተሞቹ ያሉ ሽፍቶች መመፈንጪያ እንድትሆን የሚፈቅድ ዜጋ የለም፡፡በየቦታው የፖሊሶችን የሕግ ማስከበር ስራዎች፤የቀበሌ አመራሮችን፤የመንግስታዊ አስተዳደሩን ኃላፊዎች እየተጋፉ ወይንም ወደጎን እያደረጉ በነዋሪው ላይ ያሻቸውን የሚወስኑ የሚያስፈራሩ፤የሚደበድቡ፤ ገንዘብ የሚቀበሉ፤ሲያሻቸውም የሚያስሩ፤መኪና የሚያግቱ ቤት የሚዘርፉ ገንዘብ አስገድደው የሚቀበሉ የሀገርን ሕግና ስርአት የጣሱ ቀማኞች ስርአተ አልበኞች በየቦታው ተፈልፍለዋል፡፡ተፈጥረዋል፡፡

እኛ ነን ትግሉን የመራነው ወሳኞቹ እኛ  ነን ፤ፖሊስ ምን አገባው ፤የወረዳ አመራርና ቀበሌ ምንአገባው የሚሉ ልቅና መረን የወጣ ስርአተ አልበኝነት ሰፍኖአል ብቻ ሳይሆን ነግሶአል፡፡የመደመር ለውጡ አስተሳሰብ መነሻውም መድረሻውም ይሄ አልነበረም፡፡የለውጥ ጅምሩ በስርአተ አልበኞችና በለውጥ አደናቃፊ ኃይሎች እንዳይሰናከል ሕዝብ ከመንግስት ጎን ጸንቶ መቆም ይጠበቅበታል፡፡ስርአተ አልበኝነት የግድ ሊገታ ይገባል፡፡ሀገር ያጠፋልና፡፡