አዲሱ ዓመት

አዲስ ዓመት በዓል በኢትዮጰያዊያን ዘንድ ልዩ ስፍራ ያለው ነው። በዓሉ ‘‘አዲስ ዓመትን በአዲስ መንፈስ’’ በሚል እሳቤ ይከበራል። መጪው ጊዜ የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር ነው። እነዚህ አዲስ ኢትዮጵያዊ ሂደቶች የወደፊቷን ኢትዮጵያ ታላቅ ተስፋ አብሳሪዎች ናቸው።

በአዲሱ ዓመት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ሲመለሱ የዋጋ ቅናሽ ተደርጓል። ይህም ወገኖቻችን ወደ አገራቸው እንዲገቡ አገር ውስጥ ያለው ዜጋ የሚያሳያቸው ፍቅር አንዱ መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። እንዲሁም ተግባሩ አንድነትን የሚፈጥርና ኢዮጵያዊነትን የሚያጠናክር ነው።

አዲሱን ዓመት የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የመረዳዳት፣ የመቻቻልና የአንድነት እሴቶቻችን የሚጠናከሩበት ነው። በአዲሱን ዓመት ቀደም ሲል ያጋጠሙንን ችግሮች እየፈታን ለውጡን አጠናክረን የምንቀጥልበት ስለሆነ ዜጎች ለበዓሉ ድምቀት እጅ ለእጅ መያያዝ ይኖርባቸዋል።

በአዲሱ 2011 ዓ.ም የህዝባችን በተለይም የወጣቶች የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር ተስፋዎች የሚለመልሙበት ነው። የመጪው አዲስ ዓመት የወጣቱ ራዕይ ተጨባጭ መሆን አለበት።  “አዲስ ዓመት ጠባ…” ብለን 2011 ዓ.ምን ስንቀበል፤ በግለሰብ ደረጃ የምናቅደው አዲሱ ውጥናችን የሚደረስበት፣ ሰላማዊና ህጋዊ መሆን ይኖርበታል።

ሌሎችን ማክበር፣ ፍቅር መስጠትና መደመር ያላቸውን ዋጋ የምንገነዘብበት ዓመት ነው። የትላንት ችግሮቻችንን በልማትና በህጋዊነት የምንክስበት ዓመት ሊሆን ይገባል። የሰላምን ፀዳል የምንላበስበት በመሆኑም ስርዓት አልበኝነትን የምንታገልበት ዓመትም ነው።

በመሆኑም ወጣቱ ትውልድ ከምንም በላይ ለሰላማዊነት ትልቅ ቦታን በመስጠት አዲሱን ዓመቱን ሊጀምረው ይገባል። በዚህም ላም ያለውን የማይተካ ዋጋ ለጓደኞቹ በማስረዳት እንዲሁም ከሰላም ሊገኝ ስለሚችል ጥቅም በማስተማር ፍቅርን፣ አንድነትንና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ በማድረግ ዓመቱን መጀመር ይኖርበታል።

በተጠናቀቀው ዓመት ከነበረበት ቦታ ይበልጥ ወደ ላይ ከፍ ማለት ይኖርበታል። በትናንቱ ቦታ ፈፅሞ መገኘት አይኖርበትም። ከትናንቱ ጠንካራ ጎኖችን በመውሰድ ነገ ይበልጥ ሊያጎለብታቸው ይገባል።

አመለካከቱ በአዲሱ ዓመት በአዲስ ሰላማዊና በህጋዊ የተጠቃሚነት መንፈስ መቀየር አለበት። ለአብነት ያህል በ2010 ዓ.ም ሲታዩ የነበሩት የስርዓት አልበኝነትና ህግና ስርዓትን ያለማክበር ጉዳዩችን በመታገል ረገድ ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆን አለበት። ከለውጡ ጎዳናዎች የሚያስወጡትን የአደናቃፊዎችን አሉባልታ ባለመስማት አዲሱን ዓመት ራሱን በሚጠቅም በአዲስ የስራ መንፈስ መጀመር ይኖርበታል።

የአገራችን ወጣት በ2011 ዓ.ም መተግበር ያለበት በአሮጌው ዓመት የነበሩብንን ችግሮች የሚያቃልል፣ ጠንካራ ጎኖችን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል እንዲሁም በሰላማዊ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ እውነታን ነው። ለግጭት በር የሚከፍቱ ቀዳዳዎችን ለመፍጠር የሚፈልጉ ፀረ ለውጥ ሃይሎችንመ የሚታገልበትዓመት ነው። 

በሚጠባው መስከረም የህግ የበላይነትን በማክበር ችግሮችን በሀጋዊ መንገድ መፍታት አለበት። ወጣቱ በህግ ካለተደነገገ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር እንደማይችል ማወቅ ከፍ ሲልም ማስተማር ይኖርበታል። የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ሥርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም።

የመኖር ዋስትና በሌለበት ሀገር ውስጥ ደግሞ ሰላምና መረጋጋት ይጠፋና እንደ ሰው ለመንቀሳቀስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ የሚደረስ ይሆናል። ይህም የተጀመረውን ለውጥ እንደሚያደናቅፍ መገንዘብ አለበት።

ወጣቱ መንግስት ባለበት አገር ውስጥ ማንም ሰው ከህግ በላይ ሊሆን እንደማይችል መገንዘብ አለበት። በመሆኑም መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚያደርጋቸውን ተግባሮች በመደገፍ አዲሱን ዓመት መጀመር አለበት።

አሁን በምንገኝበት የለውጥ ሂደት ውስጥ አንድ አካል ከሳሽም ፈራጅም ራሱ ሊሆን እንደማይችል ወጣቱ መገንዘብ አለበት። የጅምላ ፍርድ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነም መገንዘብ ይኖርበታል።

በእንዲህ ዓይነት የህግ የበላይነትን በሚጻረሩ ወገኖች ላይ መንግስት አስተማሪ የሆነን እርምጃ በህጉ አግባብ መሰረት ሲወስድ ወጣቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተባባሪ በመሆን መስራት ይኖርበታል።

ይህ የመንግስት የህግን የበላይነትን የማረጋገጥ እርምጃ በወጣቶች ስቃይ ስልጣናቸውን ለማደላደል አሊያም ከተጠያቂነት ለማምለጥ የሚደረገውን የፀረ ለውጥ ሃይሎችን ፍላጎት በበቂ ሁኔታ የሚገታ በመሆኑ በአዲሱ ዓመት ለተግባራዊነቱ መሰለፍ ይኖርበታል።

አንዳንድ ለውጥ አደናቃፊ ሃይሎች የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዘቦች መቻቻልን ያጎለበቱ እንዲሁም ዴሞክራሲያቸውን ስር እንዲሰድ ለማድረግ የህግ የበላይነትን የሚያፀና ሥርዓትን ያላቸው መሆናቸውን ማስረዳት ከወጣቶች የሚጠበቅ ተግባር ነው፤ በአዲሱ ዓመት። የህግ የበላይነት በምንም ዓይነት መንገድ ለድርድር መቅረብ እንደሌለበት ለአቻዎቹ ማስረዳት ይኖርበታል።

ከዚህ በተጨማሪ ወጣቱ የለውጥ አደናቃፊዎችን አሉባልታ ሊያወግዝ ይገባል። የለውጥ አደናቃፊዎች ዓላማ በአሁኑ ወቅት ወጣቱ በለውጡ ምክንያት እያገኘ ያለውንና ወደፊትም ይበልጥ ሊያገኝ የሚችለውን ተጠቃሚነት የሚያስቀር ነው።

ለውጡን ለማደደናቅፍ የሚፈልጉ ሃይሎች በተቀናጀ ሁኔታ የራሳቸውን አሉባልታዎች በውሸት በመለወስ በተለያዮ ማህበራዊ ሚዲያዎች በማቅረብ ተመልሰን ወደ ግጭት ውስጥ እንድንገባ እንደሚፈልጉ መገንዘብ አለበት።

የእነዚህን ሃይሎች ተግባር ለመግታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ወሳኝ ሚናውን መወጣት አለበት። ይህን በማድረግ በአዲሱ ዓመት ፍቅርን፣ አንድነትንና መደመርን በአገራችን ውስጥ ለማስረጽ የሚደረገውን ርብርብ ያግዛል።

በአዲሱ ዓመት ስርዓት አልበኞችና የመንጋ ፍርደኞች እንዳይሰለጥኑብን በሚደረገው ህግን የማስከበር ሂደት ውስጥ ሁሉም በየቀየው ሃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል። ህግንና ስርዓትን ያለ ህዝቡ ተሳትፎ እውን ማድረግ ስለማይቻል፤ ያገኘነውን ነጻነት እንዳንጠቀምበት የሚያደርጉንን ሃይሎች መከላከል የኢትዮጵያዊያን ድርሻ ሊሆን ይገባዋል።