መደላድል ፈጣሪው

ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (ዕትዕ) ተተልሞ ወደ ስራ ከተገባ ሶስት ዓመት ሆነው። ከ2007 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ የተያዘው ይህ ዕቅድ፤ ሰፋፊ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን የሚጠይቅ ነው። በቅርቡ ይፋ የሆነው የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን የሁለት ዓመት ከመንፈቅ ወይም የአጋማሽ ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት፤ ከማክሮ ኢኮኖሚ፣ ከኢኮኖሚ ልማት፣ ከመሰረተ ልማት፣ ከሰው ሃብት ልማትና ከቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ እንዲሁም ከልማታዊ መልካም አስተዳደርና ከዴሞክራሲ ልማት ግንባታ ብሎም ከባለ ብዙ ዘርፎችን ከድርጊት ክዋኔያቸው አኳያ የሚያሳይ ነው።

በዕቅዱ የተከናወኑ ተግባራት፣ በአፈፃፀም ወቅት ያጋጠሙ ፈታኝ ሁኔታዎችና በቀጣይ መወሰድ ስላለባቸው ርምጃዎች በሪፖርቱ ላይ የተመለከቱ እውነታዎች ናቸው። ታዲያ በዚህ ፅሑፍ ላይ የማክሮ ኢኮኖሚን ከዕቅዱ አፈፃፀም አኳያ በመጠኑ ለመመልከት እንሞክራለን።

ሁለተኛው የልማት ዕቅድ በ2007 ዓ.ም ይፋ ሲሆን የማክሮ ኢኮኖሚ (የሀገር አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ) የሚከተሉትን ዓላማዎች ያነገበ ነበር። እነርሱም በመሰረታዊ የዕድገት አማራጭ ኢኮኖሚውን በአማካይ በ11 በመቶ ማሳደግ፣ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት፣ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ መፍጠር፣ የዋጋ ንረትን በነጠላ አሃዝ መገደብና የውጭ ምንዛሬ ተመንን ማረጋጋት ይገኙባቸዋል። እንዲሁም የበጀት ጉድለትን በየዓመቱ በአማካይ ከሶስት በመቶ እንዳይበልጥ ማድረግ፣ የሀገር ውስጥ ገቢን በየዓመቱ በአማካይ በ16 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ማሳደግ፣ የሀገር ውስጥ ቁጠባን ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻ 29 ነጥብ ስድስት በመቶ ማድረስና የኢንቨስትመንት ድርሻን በዕቅዱ ዘመን መጨረሻ 41 ነጥብ ሶስት በመቶ እንዲሆን ማስቻል ናቸው።

የዕቅዱ እነዚህ ዓላማዎች በሁለት ዓመት ከመንፈቅ ውስጥ ታዳጊ ሀገሮች በተለይ ዘላቂ ዕድገትን እንዲያስቀጥሉ ከሚፈለገው የሰባት በመቶ እድገት አኳያ ከፍ ያለ ነው። ይሁንና በ2008 እና በ2009 ዓ.ም በቅደም ተከተል የተመዘገበው የስምንት በመቶና የ10 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ዕድገት በበጀት ዓመቶቹ በተከታታይ ከተቀመጡት የ11 ነጥብ ሁለት በመቶ እና የ11 ነጥብ አንድ በመቶ ዒላማ ጋር ሲነፃፀር ዝቅ ያለ መሆኑን አፈፃፀሙ ያስረዳል። በምክንያትነትም በ2008 ዓ.ም ተከስቶ የነበረው ድርቅ ያስከተለው ተፅዕኖ እንዲሁም የወጪ ሸቀጦች ዋጋ በዓለም የገበያ ላይ መውረዱና በዚህም ሳቢያ በወጪ ንግድ ገቢ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ በዋነኛነት ከተጠቀሱት ጉዳዩች ውስጥ ይገኛሉ። እነዚህን ችግሮች ለመሻገር እጅግ ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል።

በአንፃሩ ደግሞ፤ በ2009 ዓ.ም ከተመዘገበው 10 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ተያይዞ የጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት መጠን በጊዜው የገበያ ዋጋ በ2007 ዓ.ም ከነበረበት አንድ ነጥብ ሁለት ትሪሊዮን ብር፤ በ2009 ዓ.ም ወደ አንድ ነጥብ ስምንት ትሪሊዮን ብር ማደጉን ሰነዱ ያስረዳል። ይህ ዕድገትም በ2007 ዓ.ም 693 የአሜሪካን ዶላር የነበረውን የዜጎችን የነፍስ ወከፍ ገቢ (Per Capita Income)፤ በ2008 ዓ.ም ወደ 801 የአሜሪካን ዶላር እንዲሁም በ2009 ዓ.ም ወደ 863 የአሜሪካን ዶላር እንዲያድግ አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህ እውነታም በችግር ላይ ባንሆን ኖሮ፤ ዕድገቱ የዜጎችን የነፍስ ወከፍ ገቢ ከዚህ በላይ ያሳድገው እንደነበር የሚያመላክት ይመስለኛል።

በ2010 የበጀት ዓመት በመሠረታዊ የዕድገት አማራጭ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርትን በ11 ነጥብ አንድ በመቶ፣ የግብርናውን ዘርፍ በሰባት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ፣ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በ20 በመቶ እና የአገልግሎት ዘርፉን በ10 ነጥብ አንድ በመቶ ለማሳደግ ግብ ያስቀመጠ ነው። በበጀት ዓመቱ የመኸር ወቅት የዝናብ መጠንና ስርጭት መልካም የነበረ ነው። ይህም ለግብርናው ዘርፍ የሰባት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ተጨማሪ እሴት ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችል ነው።

መንግስት በኢንዱስትሪ ዘርፉ ያስቀመጠውን የ20 በመቶ የዕድገት ግብ ለማሳካት ስራ እየተከናወነ ቢሆንም፤ ከውጭ ምንዛሬ ጋር የተያያዙ እና የዘርፉን ዕድገት ከሚያፋጥኑ ግብዓቶች አቅርቦት አንፃር ውስንነቶች በስፋት ይታያሉ። ይህም በዘርፉ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉ የሚቀር አይደለም።

የአገልግሎት ዘርፉ ዕድገት የግብርና እና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ዕድገት ነፀብራቅ በመሆኑ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ከሁለቱ ዘርፎች አፈፃፀም ጋር ተሳስሮ የሚታይ ነው። በ2008 እና በ2009 የበጀት ዓመታት የተመዘገበው አማካይ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት ዘጠን ነጥብ አምስት በመቶ ነው። ይህም በተከታታይ ዓመታቱ ይደረስበታል ተብሎ በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ከተቀመጠው ጋር ሲተያይ የአንድ ነጥብ አምስት መቶኛ ጉድለት እንዳለው መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚህ መሳ ለመሳም የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች አማካይ አፈፃፀም በቅደም ተከትል የአራት ነጠብ አምስት በመቶ፣ የ19 ነጥብ ሰባት በመቶ ሆኗል። ይህም በተከታታይ ዓመታት በአማካይ ይደረስበታል ተብሎ በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ከተቀመጠው ግብ በቅደም ተከተል ሲታይ፤ በግብርና ዘርፍ የሶስት ነጥብ አምስት መቶኛ፣ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የዜሮ ነጥብ ሶስት እና በአገልግሎት ዘርፍ የዜሮ ነጥብ አምስት መቶኛ ጉድለቶች ተፈጥረዋል።

ስለሆነም በቀጣይ በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የተቀመጠውን የዕድገት ግብ ለማሳካት በተለይ የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት የበለጠ ለማሳደግ እና የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንትን በተፋጠነ ሁኔታ ለማስፋፋት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል።

ግብርናው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዋነኛ ሞተር እንደመሆኑ መጠን በዘርፉ ላይ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መስራት ለነገ የሚተው ተግባር መሆን የለበትም። እንዲሁም መንግስት በተለይ ካለፉት አራት ወራት ወዲህ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን በማስፋፋትና በማስተዋወቅ እንዲሁም ኢንቬስተሮችን በማፈላለግ ሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ያከናወናቸው የገፅታ ግንባታ ስራዎች ችግሩን ይቀርፋሉ ተብለው ተስፋ የሚጣልባቸው ናቸው።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የ2008 ዓ.ም የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ የዋጋ ንረት ዘጠኝ ነጥብ ሰባት በመቶ ነበር። የ2009 በጀት ዓመትም በተመሳሳይ ሰባት ነጥብ ሁለት በመቶ ደርሶ ነበር። በ2010 የበጀት ዓመት የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት ረዘም ላለ ጊዜ የዋጋ ንረትን በሚያሳየው አገር አቀፍ የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ ጠቅላላ የዋጋ ንረት በታህሳስ ወር 2010 ዓ.ም ዘጠኝ ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።

ከዚህ ውስጥ የምግብ እንዲሁም ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ንረት በቅደም ተከተላቸው 12 ነጥብ ስድስት በመቶ እና ሰባት በመቶ ሆኗል። በጥቅሉ ከሐምሌ 2009 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 2010 ዓ.ም ድረስ በነበሩር ስድስት ወራቶች ውስጥ የዋጋ ንረቱ ሁለት አሃዝ ያለው ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፤ በተለይ በህዳር ወር 18 ነጥብ አንድ የዋጋ ንረት ምጣኔ ታይቷል።

ይህ የሆነውም በሀገራችን ውስጥ በተደረገው የብር የውጭ ምንዛሬ ለውጥና በአዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች የተፈጠረው አለመረጋጋት ሳቢያ መሆኑ ተመልክቷል። በአሁኑ ወቅት የብር ምንዛሬን በተለይም በጥቁር ገበያ የነበረውን እጅግ የናረ የዶላር ለውጥን መቆጣጠር በመቻሉና የዶላር ክምችታችን እየጨመረ በመሄዱ እንዲሁም ሰላማችን በአንፃራዊ ሁኔታ አስተማማኝ መሆኑ ቀደም ሲል የታየውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር ተስፋን በመፈንጠቅ ላይ ይገኛሉ። ይህም ምግብንና የምግብ ነክ ምርቶችን የዋጋ ንረት በነጠላ ዋጋ ለመገደብ የሚያስችል ይመስለኛል።

ከማክሮ ኢኮኖሚ አኳያ ሊነሳ የሚገባው ሌላ ጉዳይ የውጭ ብድር ፍሰትን የተመለከተ ጉዳይ ነው። በ2008 እና በ2009 በጀት ዓመቶች በቅደም ተከትል በድምሩ ሶስት ነጥብ አራት እና ሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ብድር ተገኝቷል። ብድሩ በ2007 ዓ.ም ከተመዘገበው የስድስት ነጥብ አራት የአሜሪካ ዶላር ጋር ሲነፃፀር፤ በቅደም ተከተሉ የ53 በመቶ እና የ56 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

 

ያም ሆኖ በ2009 በጀት ዓመት የሀገሪቱ ጠቅላላ የውጭ ብድር ክምችት 23 ነጥብ አምስት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የደረሰ ሲሆን፤ በ2010 ዓ.ም በነበሩት ስድስት ወራት መጨረሻ ብድሩ ወደ 24 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል። ይህ የውጭ ዕዳ ጫና ሀገራችን በምታከናውነው ዕድገት ላይ ጫና እንዳይፈጥር ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል።

 

በአሁኑ ወቅትም መንግስት ያለበትን የውጭ ዕዳ ለመክፈል እየሰራ ነው። በያዝነው ዓት ብቻ 22 ቢሊዮን ብር ለውጭ ዕዳ ክፍያ በጅቷል። ወደፊት በእጁ የሚገኙትን የልማት ድርጅቶች ሙሉ ለሙሉና በከፊል ለመሸጥ የያዘው ዕቅድም የውጭ ጫናው በኢኮኖሚው ዕድገት ላይ ጉልህ ጫና እንዳይፈጥር የሚያደርግ ነው። በአጠቃላይ በማክሮ ኢኮኖሚውን ሁኔታ ከነበረበት ለመቀየር መንግስት የሚያከናውናቸው ስራዎች ለውጥ የሚያመጡ በመሆናቸው ሊበረታቱ ይገባል እላለሁ።