የአብይ ዓብይ ወግ

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት ሲባል፣ የእያንዳንዱ ሰው ነፃነትም ክብር ሊነፈገው አይገባም ማለት ነው፡፡ ዴሞክራሲ የተለያዩ ሐሳቦች የሚስተናገዱበት መሆኑን ለደቂቃም ቢሆን መዘንጋት አይገባም ማለት ነው፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ የሕግ የበላይነት መከበር ያለበት መሆኑ ላይ ልዩነት ሊኖር አይገባም ማለት ነው፡፡የ አብይ ጉዳይም ይኸው ነው።

 

በአብይ ጉዳይ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ከስደት ወደ አገር ቤት እየተመለሱ ነው፡፡ የቀሩትም በቅርቡ ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአፈና ምክንያት የተሰደዱ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አገር ቤት ሲመለሱ፣ የመጀመርያ ተግባራቸው ለሐሳብ ነፃነት ዕውቅና መስጠት መሆን አለበት፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚታየው የሌሎችን ሐሳብ ማንቋሸሽ፣ በጠላትነት መፈረጅና ከዚያም አልፎ ተርፎ በዛቻ የተሞሉ ማስፈራራቶችን በአደባባይ ማውገዝ ይኖርባቸዋል፡፡ ብዙዎቹ ደጋፊዎቻቸውን ካለማወቃቸውም በላይ የትግሉን ስፋትና ጥልቀት የተረዱ እንዳልሆኑ፣ ከሚያወጡዋቸው መግለጫዎች መረዳት ይቻላል፡፡

 

አሁን ግን ሕዝብ ዘንድ እየደረሱ ስለሆነ ተጨባጭ ሁኔታዎችን መገንዘብ አለባቸው፡፡ ከዓመታት በፊት የተለዩት ደጋፊና አሁን የሚያገኙት አዲሱ ትውልድ በብዙ ነገሮች ይለያያሉ፡፡ የአሁኑ ትውልድ ትምህርት ላይ የሚገኝ፣ ሞጋች የሆኑ ጥያቄዎችን የሚያቀርብ፣ ዝም ብሎ በስሜት የማይነዳና መረጃ የታጠቀ በመሆኑ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ድጋፍና ተቃውሞ ከስሜት ይልቅ ምክንያታዊነት ላይ ስለሚመረኮዙ፣ የሐሳብ ገበያው ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደሚደራ መገንዘብ ይገባል፡፡ የሐሳብ ነፃነት እንዲከበር ደግሞ የሕግ የበላይነት መኖር አለበት፡፡የአብይ ጉዳይና የየመድረኮቹ ወግም ይኸው ነው።

 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን ውስጥ በሁሉም መስኮች መሰረታዊና ተስፋ ሰጪ ለውጦች እየተመዘገቡ ያሉበት ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ብንገኝም በተጀመረው ስፋትና ጥልቀት ለውጡን ለማስቀጠል የሚደረገውን ጥረት የሚያደነቅፉና የለውጡን አቅጣጫ የሚያስቱ ችግሮችም አብረው እየታዩ መጥተዋል። 

 

አገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት የቆየ ሥልጣኔ ባለቤት የሆነች፣ በዓመታት የጎለበተ የመንግሥት መዋቅርና ሥርዓት ያላት፣ የፍትህና ርትዕ ማህበረ ባህላዊ መረዳትም በህዝቦቿ ዘወትራዊ ህይወት ውስጥ የሰፈነባት እና ህዝቦቿም ለዘመናት ስለነጻነት ታሪካዊ ገድል የፈጸሙባት ታላቅ አገር ናት። አብሮነትና መቻቻል በመልካምም ሆነ በፈታኝ የታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ የአገራችን ህዝቦች አይነተኛ ዕሴት ሆኖ ቆይቷል፡፡  

በኢትዮጵያ ዘላቂ ዋስትና ያለው ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት እንዲፋጠን፤ በሕግ የበላይነት እና በህዝቡ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ መገንባት፣ ይህንንም ለማሳካት የግለሰብና የቡድን መሰረታዊ መብቶች ካለአንዳች ልዩነት እንዲከበሩ ማድረግ እና ለዚህም የሚያሥፈልገውን የፖለቲካ ምህዳር በህገ-መንግስቱ መሰረት ማደራጀት ያስፈልጋል።

 

ባለፉት አራት ወራት የተወሰዱት የእርምት እርምጃዎች የሕዝቡን ጥያቄ በተወሰነ ደረጃ በመመለስ ፋታ ያስገኙ ቢሆኑም መሠረታዊ የሆኑት የፍትህ፣ የዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት ጥያቄዎችን በመመለስ ረገድ ገና ብዙ የሚቀር መሆኑ አይተባበልም። ቀደም ባሉት ዓመታት ይስተዋል የነበረውን ሕግን እንደመሣሪያ ተጠቅሞ የመግዛት አካሄድ ያመጣቸውን መዘዞች ለማረም ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል አንዱ ያላግባብ ይወነጀሉ የነበሩ ዜጎችንና የፖለቲካ ቡድኖችን ጉዳይ በይቅርታና በምህረት ዕልባት እንዲያገኝ ማድረግ ነው። በዚህ ሂደት ላይ እያለን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አንዱ የተጋረጠብን ፈተና ነጻነትንና ሥርዓት አልበኝነትን ባለመለየት፤ መረን የለቀቀ፣ ሕግና ሥርዓትን የማያከብር እንቅስቃሴ እና ድርጊት መስፋፋት ነው።

 

አሁን በአገራችን እየታየ ያለውና ለሕግ የበላይነት ትልቅ ፈተና የሆነው ጉዳይ ለሕግ ተገዥነትን ወደ ጎን የማድረግ ትልቅ ዝንባሌ ብቻ ሳይሆን በስሜትና በጥላቻ የሚወሰዱ እርምጃዎች፣ ሕግን ወደ ራስ ፍላጎት እና ስሜት በመውስድ በመንጋ የሚሰጡ ስርአት አልባ ፍርዶች ጭምር ናቸው፡፡ ድርጊቶቹ በአንድ ክልል፣ ብሔር፣ ቋንቋ ወይም ሃይማኖት የተወሰኑ አይደሉም፡፡ እንዲህ ያሉት እንቅስቃሴዎች የዜጎችን ደህንነትና የአገሪቱን ሰላም በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተኑ ይገኛሉ። በመሆኑም እነዚህ ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመሩ የመጡ በመንጋ የሚሰጡ የፍትህ እርምጃዎች እንደ አገር ለመቀጠል አሳሳቢ እንደሆኑ እና በፍጥነትም መታረም እንዳለባቸው መንግስት በጥብቅ የሚያምን መሆኑን አብይ በወጋቸው አረጋግጠዋል።

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ  ወደ ሥልጣን ከመጡ ለመጀመርያ ጊዜ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ በሶማሌ ክልል ሰዎች ከአንበሳ፣ ከጅብና ከነብር ጋር ይታሰሩ እንደነበር ገልጸዋል:: በሶማሌ ክልል የነበረው ሰብዓዊ መብት ጥሰት በፊልም የሚታይ ልብ ወለድ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግ አይመስልም ብለው፣ ታሳሪዎች የሚጠበቅባቸውን ብቻ ሳይሆን ከሚጠበቅባቸው በላይ እንዲናዘዙ ለማስፈራራት ይህ ድርጊት ይፈጸምባቸው እንደነበር አውግተዋል።

 

በቅርቡ በክልል በነበረው ግጭት ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በዜጎች ላይ ሲደርስ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ለመግባት ለምን ዘገየ በሚል ተጠይቀው፣ በክልሉ የሚደረገው ጣልቃ ገብነት ከፍተኛ ጥንቃቄና ብስለት ካልተደረገበት በስተቀር ክልሉን ብቻ ሳይሆን ቀጣናው ሊታወክ ይችል እንደነበር ተናግረው፤ ለዚህም እንደ ማስረጃ ያነሱት ድሬዳዋ ላይ ሆን ተብሎ የጂቡቲ ዜጎች እየተመረጡ ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ይህም ግጭቱ ቀጣናዊ ይዘት እንዲኖረው ለማድረግ ታስቦ መሆኑን በወጋቸው ጠቁመዋል ። 

 

በአገሪቱ በቅርቡ የመጣውን ለውጥ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እንዴት ተቀብለውታል ተብለው የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለውጡን ሙሉ ለሙሉ የተቀበሉና ያልተቀበሉ ድርጅቶች እንደሌሉ እንዲህ አውግተዋል።“ኦሕዴድ ለውጡን ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ሕወሓትን ግን የዚያ ተቃራኒ አድርጎ መመልከት ስህተት ነው። በሕወሓት ውስጥ ለውጡን የሚደግፉና ከለውጡ ጋር የቆሙ አሉ።ለውጡን የማይቀበሉት ኃይሎችም አሉ፤”

 

ትግራይ ክልልን እየመሩ ያሉት አመራሮች ለውጡን ከልብ እንደሚደግፉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በጡረታ የተሰናበቱትና የቀድሞውን ሥርዓት እንዲቀጥል የሚፈልጉት ለውጡን ላይደግፉት ይችላሉ ብለዋል። ሁለቱን ቡድኖች ግን አንድ ላይ ጨፍልቆ ማየት ስህተት ነው ብለው፣ ሕወሓትን የለውጡ ተቃዋሚ አድርጎ መመልከት አያስፈልግም ሲሉም ጉዳዩ የእርሳቸውና የመንግስታቸው ዓብይ ጉዳይ መሆኑንም አውግተዋል።

 

ከለውጡ ጋር በተያያዘ ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ የሚመራበትን አይዲዮሎጂ ቀይሯል ወይ ለሚለው ጥያቄ፣ “ኢሕአዴግ በመጀመርያ ታድሷል:: በመቀጠልም በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ነው ያለው። ይህንን ማድረግ ያስፈለገው ኢሕአዴግ በማርጀቱና በመሻገቱ ነው:: ስለዚህ የዴሞክራሲ አውዱን አስፍቷል። ይህም ማለት አሸናፊ ሐሳብ እንዲገዛ ተደረገ እንጂ፣ የአይዲዮሎጂ ለውጥ አልተደረገም፤” ሲሉ ወጋቸውን ቀጥለዋል።

 

ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲኖር ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረው፣ የቀጣዩ ምርጫ ምዝገባ በዘመናዊ መንገድ እንዲከናወን ከተቻለም ሙሉ የምርጫ ሒደቱ ዘመናዊ አሠራርን እንደሚከተል በአብይ ወጋቸው ያረጋገጡት ዶክተር አብይ፤ “የምርጫ ኮሮጆ ጥርጣሬ ከኢትዮጵያ ውስጥ መጥፋት አለበት:: ሳይመረጡ ማገልገል አይቻልም” ሲሉም በወጋቸው አክለዋል። ይህንንም ለማድረግ የምርጫ ተቋሙን በኢሕአዴግም፣ በተቃዋሚዎችና በሕዝቡም ጭምር እንዲታመን አድርገን እንዲደራጅ እየሠራን ነው ብለዋል።

 

በአገር-አቀፍ ደረጃ ከተጀመረው የሪፎርም፣ የይቅርታ፣ የነፃነትና የፍትህ ፋና-ወጊ ሥራዎቻችን በተፃራሪ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በጥቂት ግለሰቦችና አካላት በዘፈቀደና በስሜት የሚፈፀሙ በአመዛኙ የብሔር ማንነትን መሰረት ያደረጉ አካላዊ ጥቃቶች፤ ግድያዎች፤ የንብረት ውድመቶችና መፈናቀሎች የሕዝቡን ሰላም፤ ነፃነትና የኑሮ ዋስትና ከመሰረቱ እያናጉ በመሆናቸው ከእንግዲህ መንግስት እንዲህ ያሉ ተግባራትን ፈፅሞ የማይታገስ መሆኑን ሁሉም አካል በውል ሊገነዘብ ይገባል። የሚለው የአብይ ወግ በለውጥ ሃይሎች ሊሰመርበትና ሊደገፍ ይገባል።

መንግስት የሚያራምደው ነፃነት፤ ሰላምና ማህበረሰባዊ ብልፅግናን የማረጋገጥ ራእይ፤ ሕግ- አልባነትንና አመፃን በሚታገስ ስርአት ወይም የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ተፈፃሚ ሊሆን እንደማይችል ሊታወቅ ይገባል፡፡ ስለሆነም በሀገራችን የዜጎቻችንን መብት እና ነፃነት ለማረጋገጥና የአካል፣ የህይወትና የኑሮ ዋስትናቸውን ለማስጠበቅ ብቸኛው መሳርያ ሕግና ሕገ-መንግስታዊ ስርአትን በሙሉ አቅም ማስከበር በመሆኑ፤ ማንም ሰው ህግ ሲተላለፍ ተጠያቂ የሚደረግበትን የአሰራር ስርአት መዘርጋት እና መተግበር እንደዜጋ ለእያንዳንዳችን፤ እንደ ሀገርም ለሁላችን የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ስለሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከመንግስት ጎን በመሆን ርብርብ እንዲያደርግ ክቡር ጠቅላያችን ያቀረቡት ጥሪም እንደ ተራ ነገር ሳይወሰድ በለውጥ ሃይሎች ሊደገፍ ይገባል፡፡

 

ከምንም በላይ የግልና የቡድን ጥቅሞቻችሁን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማስጠበቅ እየቻሉ በተለያዩ ወንጀሎችና ሰላምን የማደፍረስ እኩይ ተግባራት ላይ ለመሰማራት የሚያስቡ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በአብይ ወጋቸው ያሳሰቡት ዶክተር አብይ በማንኛውም የህዝብን ፀጥታ በሚያደፈርሱና ህዝብን ከህዝብ በሚያጋጩ ህገወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርቶ የተገኘ እንዲሁም ለእንደዚህ አይነት ህገወጥ ተግባራት በምንም መልኩ ትብብር ያደረገ አካል ላይ ህግን ተከትሎ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ መንግስት ቁርጠኛ እንደሆነ በጥብቅ አውግተዋልና ፤ የሚበጀውን እና በጎውን መምረጥ የምርጫ ጉዳይ ይሆናል፡፡