ወሰን ተሻጋሪው በጎ ተግባር

የበጎ ሥራ አገልግሎት ሰዎች በራሳቸው ተነሳሻነት ያለማንም ማስገደድ በራሳቸው ፍላጎት የሚያከናውኑት መልካም  ተግባር ነው።በእዚህም ተግባር ላይ ለመሳተፍ መስፈርት ያልተቀመጠለት በመሆኑ በሁሉም የዕድሜ ክልል ያለ ሁሉ በሚችለው መንገድ ሁሉ መሳተፍ ይችላል።የብሔር፣የሀይማኖትና የባህል ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳን እነዚህን ልዩነቶች ወደ ጎን በመተው አቅደውት የተነሱትን  መልካም ተግባር በቁርጠኝነት በመሥራት ውጤታማ መሆን ይገባል።በዚህ የበጎ ሥራ አገልግሎት ላይ የሚሳተፉ በጎ ሠራዊቶች የሚያገኙት ምንም ዓይነት ገቢ የለም የሚያገኙትም ትልቁ ነገር ከፍተኛ የሆነ የህሊና እርካታ ብቻ ነው።

ከዚህን ቀደም ወጣቶች ስለ በጎ ሥራ አገልግሎት የነበራቸው ግንዛቤ አነስተኛ ስለነበረ በሀገራችን ይህ  አገልግሎት ብዙም ባለመተግበሩ ያመጣውን ፋይዳ ያስገኘውን ጠቀሜታ ማየትና መረዳት አልቻልንም። አሁን ላይ መንግሥት ይህን አውቆ ግንዛቤ ከማስጨበጥ አንስቶ በትኩረት እየሰራበት ይገኛል። አብዛኛውን ጊዜ ይህ በጎ ተግባር የሚከናወነው በክረምት ወቅት ነው። ይህም የሆነው ብዙ ወጣቶች ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት የሚያርፉበትና ትምህርትም የሚዘጋበት ወቅት በመሆኑ ነው።ወጣቶቹም ይህን የዕረፍት ጊዜያቸውን መልካም ተግባራትን በማከናወን እንዲያሳልፉ በማሰብ መንግሥት የሠጠውን መግለጫ ወጣቶች በተለያዩ የበጎ ሥራ አገልግሎቶች ላይ ቀዳሚ ተሳታፊዎች በመሆን ላይ ናቸው።

መንግሥትም አሁን ላይ ለጀመረው የለውጥ አቅጣጫ መልካም ተሞክሮ ስለሚሆን ይህን የበጎ ሥራ አገልግሎትን ወሰን ተሸጋሪ ከማድረግ አኳያ ከወጣቶች ጋር አብሮ እየሠራና ግንዛቤን እያስጨበጠ ይገኛል።በተጨማሪም ይህ ተግባር ወጣቶች ለሀገራቸው  የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡና ለራሳቸውን የኃላፊነት ስሜት እንዲሰማቸው ከማድረግ አኳያ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል።

ባሳለፍነው ሣምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከተለያዩ ቦታዎች ከተወጣጡ አንድ ሺህ ከሚሆኑ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ለመሥራት ቆርጠው ከተነሱ በጎ  ወጣቶች ጋር በወሰን ተሸጋሪ የበጎ ሥራ አገልግሎቶች ላይ በስፋት መወያየታቸው ይታወሳል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጣቶቹን በዚህ መልካም ተግባር ላይ ለመሳተፍ በልበ ሙሉነት በመነሳታቸው በጣም ዕድለኛ መሆናቸውን ጠቁመው በዚህም ተግባር ላይ በቁርጠኝነት በመሥራት ለሀገራቸው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነትን መወጣት  እንደሚገባቸው ገልፀዋል። ወጣቶቹም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ከተወያዩ በኋላ ወደ ተለያዩ  የሀገሪቱ ክፍሎች በመሄድ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ።እነዚህ ወጣቶች ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ የሚሄዱበትን አካባቢ ባህል፣ቋንቋና የአኗኗር ዘይቤን በጥቂቱም ቢሆን እንዲያውቁና የራሳቸውን ባህል ለማስተዋወቅም ይጠቅማቸዋል።ይህ ዳግሞ ፍቅርና አንድነትን በህዝቦች መሃከል እንደሚፈጥር ይታመናል።

ወጣቶቹም በሄዱበት ስፍራዎች ሁሉ በተለያዩ የበጎ ፍቃድ ሥራዎች ላይ  በስፋት እየተሳተፉ ይገኛሉ።ለአብነት ያህል በደም ልገሳ፣በአካባቢ ፅዳትና የትራፊክ ሕግን በማስከበር ላይ ቀዳሚ በመሆን እየሠሩ ይገኛሉ።ይህ ወሰን ተሸጋሪ የበጎ ሥራ አገልግሎት ከአገልግሎቱ ባሻገር የሚኖረው ሀገራዊ ፋይዳን ስንመለከት ህዝቦችን በማቀራረብ፣የአንድነትን፣ የፍቅርና የመደመርን ዕሣቤን በማጉላት የሀገሪቱን የወደፊት ተስፋ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅዖም አለው። በተጨማሪም እነዚህ በዚህ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ሥራ ላይ የሚሳተፉ በጎ ሠራዊቶች ይህንን መልካም ተግባራቸውን እያከናወኑ ጎን ለጎን ሌሎች ወጣቶችን ማነሳሳትና ለተመሳሳይ ተግባርን እነዲያከናውኑ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።እነዚህ ወጣቶች አንግበውት የተነሱትን ይህን መልካም ተግባር ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ በሄዱበት አካባቢዎች ሁሉ የሚመለከታቸው አካላት እነሱን በመቀበል አስፈላጊውን ነገሮች ሁሉ በሟሟላትና ከአካባቢው ወጣቶች ጋር በመቀናጀት መልካም ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ።

የሀገርን ፀጥታና ሰላም ለማስጠበቅ የሚቻለው መንግሥት  ከሕዝብ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ሲሠራ ነው።  ስለዚህ ይህን ሀገራችን የጀመረችውን መልካም የለውጥ ጅማሮን ከማስቀጠል አንፃር እነዚህ ወሰን ተሸጋሪ የበጎ ሥራ ሠራዊቶችም በሚሄዱበት አካባቢዎች ላይ የጉልበት ሥራዎችን ብቻ ለመሥራት ሳይሆን ይልቁንም ፅንፈኝነትን በመታገል፣ ሰላምን በማስጠበቅ የሥራ ፍቅርን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ በማድረግ የሀገራችን ሰላም ሲከበር ከራሳችን አልፎ ይበልጥ ለሌሎች የጎረቤት ሀገራት መትረፍ እንደሚችል አንዱ ማሳያ ነው ።