የህዝቦች አንድነት

በአንድ አገር ለህዝቦች ብልፅግና እና መልካም አስተዳደር ሲባል የአስተሳሰብ ልዩነቶችና ሐቀኛ ክርክሮች አስፈላጊ ነገሮች ናቸው፡፡ አስፈላጊ የሚሆኑት ግን በሥነ አመክንዮ የተደገፉና ለሰፊው ህዝብ ወገንተኝነት ያላቸው እስከሆኑ ድረስ ብቻ ነው፡፡ አንድ ሐሳብ ወይም ተግባር በበቂ ምክንያት ካልተደገፈና ለህዝቡ ጥቅም ከሌለው ዋጋ አይኖረውም። ሊኖረውም አይችልም፡፡

 

የኢትዮጵያ ታሪክና የህዝቦቿ ግንኙነት በጎና መጥፎ ገፅታዎች አሉት፡፡ በጎ ገፅታዎች የአገራችን ዜጎች በጋራ ያዳበሯቸው እሴቶችና ገድሎች ናቸው፡፡ ህዝባችን በረዥም ጊዜ ሂደት የምንነትና የእምነት መወራረስ ፈጥረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች በተለያዩ ጊዜያት አገሪቱን ለመቆጣጠር ብሎም ለመቀራመት የመጡትን የውጭ ወራሪዎች በጋራ ተዋግቶ ድል በማድረግ አገራችንን ከባዕድ ገዥዎች ከመጠበቅ ባሻገር ከባዕድ ገዥዎች የማይሻሉ የውስጥ አምባገነኞችንም ታግለው አስወግደዋቸዋል፡፡

 

በሌላ በኩል የገዥ መደቡ በህዝቦች ግንኙነት ላይ መጥፎ አሻራ ጥሎ አልፏል። በህዝቦች ላይ ሲደርስ በኖረው ብሔራዊ ጭቆና ምክንያት ዛሬ ማስታወስ ባያስፈልግም መጠነ ሰፊ ጥፋቶች ደርሰዋል። ማስታወስና መተንተን ባያሻም የታሪክ ዋና ጥቅም የትናንትናን አውቀህ ጥፋቶቹን በማረም የዛሬና የነገ ህይወት ማስተካከል ስለሆነ ታሪካችንን ማወቁ ይበጃል፡፡

 

በአንድ የታሪክ አጋጣሚ በትረ ሥልጣን የጨበጠው ገዥ ኃይል የአገሪቱን ዜጎች እኩልነታቸውንና ማንነታቸውን ለማጎልበት ሲጠይቁና ሲታገሉ ከማስተናገድ ይልቅ በራስ መነፅር ብቻ እንዲያልፉ በርከት ያሉ ቅድመ ግዴታዎችን ሲያስተናግዱ ኖረዋል፡፡ ከዚህ አልፎ አንዳንድ ወገኖቻችን አፅመ ርስታቸው በሆነው አገር "መጤ" ወይም "ከወንዝ የወጣ" ሌሎች ደግሞ "በኢትዮጵያ የሚገኙ" እየተባሉ በአገራቸው ጉዳይ ያገባናል እንዳይሉ ተደርገው ኖረዋል። ገዥ መደብ ሥልጣኑን ዘለዓለማዊ ለማድረግ በማሰብ ሌሎች ዜጎችን  በራሱ አምሳል ብቻ ለመቅረፅ ያረቀቀውና ይታገልለት በነበረው ፖሊሲ ምክንያት ህዝብን እርስ በርስ በማጋጨት የጥርጣሬ መንፈስ ከፈጠረ በኋላ ከፋፍሎ ይገዛ ነበር፡፡

 

በአጠቃላይ ሲታይ የገዥ መደብ "እኛን ምሰል ፖሊሲና ስትራቴጂው" ለረዘም ያለ ጊዜ ብሔራዊ ጭቆናን መፈጠርና ማስቀጠል በመቻሉ፤ በህዝቦች መካከል ልዩነትና ጥርጣሬ እንዲኖር በማድረግ አገሪቱን ለከፍተኛ እልቂትና የመበታተን ጫፍ አድርሶ ነበር። በዚህም ፖሊሲው በከፊል ተሳክቷል። በዘመነ ገዥ መደብ ግዴታ እንጂ መብት የሚባል ጉዳይ አልነበረም፡፡ መብት ከሌለ ደግሞ እኩልነት አይኖርም፡፡ እኩልነት ከሌለ ደግሞ የጋራ ተጠቃሚነት አይታሰብም፡፡ እኩልነትና የጋራ ተጠቃሚነት በሌሉበት ሠላም ሆነ ልማት አይታሰብም። የዘመኑ ሀቅ የነበረው ተወልዶ ሌላን መምሰልና ሰርቶ ለገዥ ማስረከብን የተሰላቸ ህዝብ ለመብቱ ፍለጋ በ1960ዎች ጫፍ እስከ ጫፍ ተነስቷል፡፡ ጥያቄው ስለህዝብ ሉዓላዊነትና ስለሃብቱ እኩል ተጠቃሚነት የነበረ ቢሆንም የግብረ መልሱ ቋንቋ ኃይል ብቻ ስለነበር ሠላም ጠፍቶ ልማት አይታሰቤ ሆኖ ቆይቷል፡፡

 

በኃይል አንድነት አይመጣም፡፡ ሊመጣም አይችልም፡፡ አብሮነት የህዝብ ምርጫ እንጂ የገዥዎች ይሁኝታ አይደለም፡፡ በገዛ አገራቸው ሠላም፤ ልማትና ዴሞክራሲ ቀርቶ በየአካባቢያቸው አሰቃቂ ግፍ የደረሰባቸው ህዝቦች ነፃ አውጭ ግንባር ቢፈጥሩ ንቃተ መብታቸው ማደጉን እንጂ አብሮነት አለመፈለጋቸውን አያሳይም፡፡ ንቃተ መብታቸው አደገ ሲባል ያኔ የገዥ መደብ ዘመን ከነበረ አንድነት መለያየቱ እጅግ የተሻለ ስለነበር ነው፡፡ መለያየቱ የተሻለ ነበር ማለት ግን ከመለያየት የበለጠ አማራጭ አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ ገዥውን መደብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አስወግዶ በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተና ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ያለው የህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት አይደርስ ይመስል የነበረው ግን የተደረሰ የብልሂ አማራጭ ነው፡፡ ይባስ ብሎ ገዥው ኃይል መልሶ ቢነግስ እንኳ ራሱን ብቻ ይወክላል እንጂ ኢትዮጵያንም ሆነ ኢትዮጵያዊነትን አይወክልም።  

 

አንድ ህዝብ እንደ ህዝብ ራሱን መተካት አለበት፡፡ አንድ ህዝብ እንደ ህዝብ ራሱንና ህይወቱን ማጣት የለበትም፡፡ ለዚህም ነው ረገጣ የበዛባቸው የኢትዮጵያ ህዝቦች የየራሳቸውን ነፃ አውጭ ግንባር የመሠረቱት፡፡ ግንባሮቹ የተለያየ ዓላማ ነበራቸው፡፡ መገንጠልን የመረጡ ግንባሮችም ሆነ አብሮነትንና ኢትዮጵያዊነትን ሳይፈልጉ ቀርቶ ሳይሆን ለብዙ አሥርት ዓመታት መብታቸውን በሙሉ ስለተነፈጉ ነው፡፡ አንድ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር ስላልመሠረተ የተለየ የኢትዮጵያ አንድነት ፍቅር ነበረው ማለት አይደለም፡፡ ሊኖረውም አይችልም፡፡ ያ ነፃ አውጭ ግንባር ያልመሠረተ አካል ለጊዜው የነበረው ማኅበረ ፖለቲካዊ አደረጃጀት ግንባርን ለመመሥረት አላስቻለውም አሊያም በተነፃፃሪም ቢሆን መብቱን አላጣም ማለት ነው፡፡ ጭቆናን ለማስወገድ ነፃ አውጭ ግንባር ሳይመሠረት በራሱ መንገድ የታገለም አለ፡፡

 

ነፃ አውጭ ግንባሮች ሲመሠረቱ የተለያየ ዓላማ ነበራቸው፡፡ በብዙዎች ሲደገፍና ሲታገሉለት የነበረ ዓላማ የመገንጠል አማራጭ ሆኖ በአንዳንዶች ሲራመድ ኖሯል። ብሔራዊ ጭቆናን መገርሰስ እንጂ መገንጠል ህዝብ የሚመርጠው አማራጭ አልነበረም፡፡ ሁለተኛው አማራጭ ሁሉንም ጭቁን ህዝቦች ነፃ አውጥቶ ሠላምና ዴሞክራሲያዊ የህዝቦች አንድነት ማረጋገጥ እንዲሁም በየደረጃው ዜጎች የሚሳተፉበት ተመጣጣኝና ቀጣይነት ያለው የልማት ተጠቃሚነት የሚል ነው፡፡

 

የህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነትና እኩል ተጠቃሚነት ሲከበር በህዝብ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ለህዝቦች አንድነት ሲባል በኢትዮጵያ የዜጎች የበላይነትና የብሔር ጭቆና ታሪክ ከመሆናቸው ባሻገር አስተማማኝ ሠላም፣ ታዳጊ ዴሞክራሲና ህዝቡ በየደረጃው ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚሆንበት ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ምጣኔ ሃብት እየተገነባ ይገኛል። በዚህም መነሻ በተባበረ የህዝቦች ክንድ ህዳሴው እውን እየሆነ መጥቷል።