መደመር የህይወት ፍልስፍና ነው

እኔ የመደመር ፍልስፍና የሚያሳስበኝ ነገር ብዙ ነው፡፡ ‹‹መደመር›› ከጠቅላላ የሰው ልጆች አንጻር የሚገለጽ እውነት አለው፡፡ እንዲሁም ‹‹መደመር›› ከኢትዮጵያ አንጻር የሚታይ እውነት አለው፡፡ በአጭሩ መደመር የህይወት መሠረታዊ ህግ ነው፡፡ የሰው ልጅ ህልውና የሚጸናው በመደመር፡፡ እያንዳንዳችን የምንኖረው ለየግላችን ይመስለናል፡፡ አይደለም፡፡ ነገሩ በእውነት ከታየ፤  ለየግላችን መኖር የምንችለው፤ በመደመር ስኬታማ ከሆንን ብቻ ነው፡፡

 

የሰውን ልጅ የሚያጠቃ በሽታ ሲመጣ፤ በበሽታው በተያዘው በእያንዳንዱ ሰው ህመም፤ የሰው ልጅ በሽታውን ለመከላከል የሚያስችል ሥነ ህይወታዊ ብቃት ይገነባል፡፡ ይህ ከባለ አንድ ሴል ፍጥረት ጀምሮ በማንኛውም ህይወት ያለው ነገር ውስጥ የሚከናወን ነው፡፡ ይህ ህግ ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ ሥነ ህይወታዊ ብቃት በመገንባትም ይገለጣል፡፡ የወባ ትንኞችን ነገር ተመልከቱ፡፡ የወባ ትንኞች ዲዲቲን ለመከላከል የሚያስችል አቅም እስኪገነቡ ብዙ የወባ ትንኞች አልቀዋል፡፡ በእያንዳንዱ ትንኝ ሞት፤ የወባ ትንኝ ዘር ከምድር ሳይጠፋ መቀጠል የሚችልበትን ሥነ ህይወታዊ ብቃት ለማግኘት ችለዋል፡፡ ዲዲት የማይገድላቸው የወባ ትንኞች ተፈጥረዋል፡፡ ለመድኃኒቱ የማይበገር ሥነ ህይወታዊ ብቃት አዳብረዋል፡፡ ይህን ብቃት ያዳበሩት ብዙ የወባ ትንኞች አልቀው ነው፡፡ ስለዚህ በተናጠል የሚከሰተው የወባ ትንኞች ሞት፤ ለዘሩ መቀጠል ዋስትና ሆኗል ማለት ነው፡፡

 

የእኛም ነገር ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ነገር ግን የእያንዳንዳችን ህይወት ለራሳችን ብቻ ይመስለናል፡፡ ሁላችንም ለራሳችን ስንል የምንኖር ይመስለናል፡፡ ውሻው የሚጮኸው እኛን ለመጠበቅ አይደለም፡፡ ለራሱ ፈርቶ ነው፡፡ እኛም የምንኖረው ለራሳችን ይመስለናል፡፡ እኛ የምንኖረው ለሰው ልጅ ህይወት መቀጠል የበኩላችንን ጥረት ለማድረግ ነው፡፡ በርግጥ የግል ህይወታችን መቀጠሉ፤ ለእኛ ትልቁ ቁም ነገር ነው፡፡ ነገር ግን እኛ የግል ህይወታችንን ለማስቀጠል ስንጣጣር፤ በእኛ የግል ህይወታችንን የማስቀጠል ትግል ውስጥ የሚተገበረው ትልቁ ሥራ የሰው ልጅ ህይወት መቀጠል ነው፡፡ ህይወት ለሰው ልጅ ህልውና መቀጠል እንጂ ለግለሰብ ደንታ ያላት አትመስልም፡፡ ስለዚህ ሰው በግለሰባዊ ትግሉ ለሰው ዘር መቀጠል እየሰራ ያልፋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው የሚኖረው ለሰው ዘር ህልውና ነው፡፡ የሰው ዘርም ለእያንዳንዱ ግለሰብ መኖር እና አስደሳች ህይወት መምራት የሚያስችል የማህበራዊ ኑሮ ስርዓት ለመገንባት መስራት ይኖርበታል፡፡ ይህን በማድረግም የሰው ዘርን ህልውና ያቀጥላል፡፡ ይህ የመደመር ፍልስፍና ሊባል ይችላል፡፡ ይህን ፍልስፍና በአንድ ሐገር አውድ ልናየው እንችላለን፡፡

 

አንድ ወታደር ለሐገሩ ሲል ይሞታል፡፡ በእርሱ ሞት የሐገር ህልውና ይቀጥላል፡፡ ይህ ከላይ ካየነው ከተፈጥሮ ህግ ይለያል፡፡ ብንወድም ባንወድም እያንዳንዳችን ለሰው ዘር መቀጠል የሚያገለግሉ ሥነ ህይወታዊ ሥራዎችን እየሰራን እናልፋለን፡፡ ነገር ግን እንደ ወታደር ህብረተሰባዊ ሥራ ለመስራት ሲቪክ አስተሳሰብን ይጠይቃል፡፡ ሲቪክ አስተሳሰብ ካልገነባን፤ የየግል ህይወታችን ለማትረፍ ብቻ ካሰብን፤ የሐገር ህልውና ሊከበር አይችልም፡፡ የመደመር ፍልስፍና ለሲቪክ አስተሳሰብ ትኩረት እንድንሰጥ ጥሪ የሚያደርግ ፍልስፍና ነው፡፡ ‹‹ለእኔ›› ብቻ በሚል አስተሳሰብ ሳንታወር፤ ‹‹ለእኛ›› ብሎ የመስራት አመለካከትን ለመፍጠር የሚሞክር ፍልፍና ነው፡፡ ‹‹የእኔን›› ፍላጎት ‹‹በእኛ›› አስተሳሰብ ለማሳካት የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው፤ በግለሰብ ደረጃ ሲታይ የሰው ዘር አንድ ሴል ነው፡፡ ምክንያቱም፤ ብንወድም ባንወድም እያንዳንዳችን ለሰው ዘር መቀጠል የሚያገለግሉ ሥነ ህይወታዊ ሥራዎችን እንሰራለን፡፡ አካላችን ሲቆስል፤ አካላችንን ከጥቃት ለመከላከል ነጭ የደም ሴሎቻችን ይዘምታሉ፡፡ ታግለው እየሞቱ  ለአካላችን ህልውና ይሰራሉ፡፡ ግለሰቦችም ለሰው ዘር መቀጠል ወይም ለሐገር ህልውና መረጋገጥ እየታገሉ ይሞታሉ፡፡ ወታደርም ለሐገር ህልውና መቀጠል ይሞታል፡፡

 

በተጨማሪም፤ የህይወት ስርዓት እንዲህ ያለ መሆኑን የምናረጋግጠው፤ እናት እና አባት ለልጆቻቸው በሚያደርጉት እንክብካቤ ነው፡፡ በወላጆች ልብ ውስጥ ፍቅር መስሎ የምናገኘው ይህ የህይወት ‹‹ሰፍትዌር›› ነው፡፡ እናት ልጇን እንደ ወለደች የምትጥል ቢሆን የሰው ዘር ይከስም ነበር፡፡ ነገሩ ከግለሰብ አንጻር ብቻ ሲታይ፤ ሊፈጠር የሚችለውን ነገር በአንዳንድ የምዕራብ ሐገራት ህብረተሰብ ህይወት ውስጥ እያየነው ነው፡፡ ለግለሰባዊ ህልም መሳካት ብቻ የሚኖሩ አድርገው የሚቆጥሩት ምዕራባውን፤ ቤተሰብ መመስረት እና ልጆች መውለድ እየፈሩ፤ ሐገራቸውን የአዛውንቶች ሐገር ሲያደርጓት እየተመለከትን ነው፡፡ እግዚአብሔር በአንዳንዱ ሰው ህይወት ለጠቅላላው የሰው ልጅ መዳን የሚበጅ ነገር ለመስራት የሚፈልግ በመሆኑ፤ ለግለሰብ ህይወት ደንታ ቢስ መስሎ ይታያል፡፡ ይህም ለጊዜው እንጂ ለፍጻሜው አይደለም፡፡ ለፍጻሜው እያንዳንዱ ግለሰብ የተመቸ ህይወት እንዲኖር በማቀድ የተዘረጋ የህይወት መርሐ ግብር ነው፡፡  መደመር ይህን መሠረታዊ ህግ የሚያስረዳ ነው፡፡ የፍልስፍናው መነሻ፤ ሁሉም በእኔነት ወይም በጠባብ ብሔርተኝነት አስተሳሰብ ተለክፎ መሠረታዊ የተፈጥሮ እና የህብረተሰብ ህግን እየሳተ ፀረ-ህይወት እና ፀረ-ህብረተሰብ የሆነ አስተሳሰብ ውስጥ ሲዘፈቅ ከማየት የመነጨ ‹‹አገር – አድን›› ጥሪ ነው፡፡ ይህንም አስተሳሰብ በአንዳንድ የምዕራብ ሐገራት ህብረተሰብ ይታያል ካልኩት አስተሳሰብ ጋር የሚዛመድ ነው፡፡

 

ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ በህዝብ ተካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በአቀረቡ ጊዜ የተናገሩት አንድ ነገር ነበር፡፡ ፀረ-ህይወት እና ፀረ-ህብረተሰብ አካሄድ እየተከተልን ሳለ፤ ህይወትን መፍጠር መቀጠላችን ወይም ልጅ መውለዳችን፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር መጨመሩ ገርሟቸው፤ ልጆቻችን በሰላም ሊኖሩ የሚችሉበትን ሁኔታ ሳንፈጥር ልጅ መውለዳችን አስደንቋቸው፤ ፍቅርን ሳይሆን ጥላቻን እያወረስናቸው፤ እርስ በእርሳቸው ሊባሉ የሚችሉበትን ቤት እየሰራንላቸው ሳለ፤ በዚህ ዓይነት ሐገር ልጆች መውለዳችን አስደምሟቸው፤ ‹‹…እንዲህ እያደረግን ደግሞ ልጆች እንወልዳለን›› ብለው ነበር፡፡ የምንወልዳቸው ልጆች፤ ለእነርሱ ወደዚህ ምድር መምጣት መሠረት በሆነው የፍቅር ወይም የመደመር ህግ ካልታነጹ፤ በአንድ ቤት ሲኖሩ ይጠፋፋሉ፡፡  በፍቅር የመኖር ህግ በቤተሰብ ብቻ ሳይሆን በህብረተሰብ ደረጃም እንደሚያስፈልግ ሲያስረዱ ‹‹እንደመር›› አሉ፡፡

 

ህብረተሰብ ወይም መንግስት የብዙ ሰዎች ስብስብ ከሆነ፤ ከሁሉ አስቀድሞ ይህ ስብስብ ሊኖር የሚችለው፤ ተጋበተው ለመውለድ የሚችሉ አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ሲኖሩ ነው፡፡ ሁለቱን በአንድ የሚያስተሳስረውም ፍቅር ነው፡፡ ሴት እና ወንድ ሳይኖሩ ህብረተሰብ ሊኖር አይችልም፡፡ አንድ ወንድ እና አንዲት ሴትን የሚያስተሳስረው እና የሚያስተዳድረውም ፍቅር ነው፡፡ የሰው ዘር በምድር መኖሩን ይቀጥል ዘንድ፤ የአንድ ሴት እና ወንድ መኖር እና የእነሱም በፍቅር መተሳሰር ግድ ነው፡፡ ስለዚህ የህብረተሰብ መሠረት ፍቅር ነው፡፡ ፍቅር ‹‹የመደመር›› ወይም ‹‹መደመር›› የፍቅር ተለዋጭ ስም ነው፡፡ ይህ ሐይማኖታዊ እሳቤ አይደለም፡፡ የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡ 

 

የሴት እና የወንድ ጥምረት የሚፈጠረውም በሰዎች ብቻ ይመስላል፡፡ ነገር ግን አይደለም፡፡ ፍቅር ወይም ‹‹መደመር›› የተፈጥሮ መላ ነው፡፡ ፍቅር ወይም ‹‹መደመር›› የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡ የሰው ልጆች አምሳያቸውን ተክቶ በማለፍ የተፈጥሮ ዝንባሌ የሚገዙ ናቸው፡፡ ይህም ዝንባሌ ከማናቸውም ሌሎች እንስሳት ወይም ዕጽዋት ጋር የሚጋሩት የአጠቃላይ ተፈጥሮ መሻት እና ዝንባሌ ነው፡፡ በዚሁ አግባብ ወንድ እና ሴት የተፈጥሮ ግብራቸውን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ፤ አምሳያቸውን በመተካት ራሳቸውን ህያው ያደርጋሉ፡፡ ወይም ዘራቸው ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ያደርጋሉ፡፡ ካህሊል ጅብራን፤ ‹‹ልጆች በእናንተ በኩል መጡ እንጂ ከእናንተ አልመጡም›› ያለው ለዚህ ነው፡፡ በእኛ ፈቃድ በኩል የአጠቃላይ የተፈጥሮ መሻት እና ዝንባሌ እውን ሆኖ ልጆች ይወለዳሉ፡፡ በፍቅር ልጆች ወደዚህ ምድር ይመጣሉ፡፡ በዚህ ምድር ከሌሎች ሰዎች ጋር ይኖራሉ፡፡ ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚኖሩትም፤ ወደዚህ ምድር በመጡበት የፍቅር ወይም የ‹‹መደመር›› ህግ ነው፡፡ የፍቅር ወይም የ‹‹መደመር›› ህግ የሌሎችን ነጻነት በማክበር፣ ለሌሎች በማሰብ፣ ለፍትሕ በመቆም ወዘተ ይፀናል፡፡ ልጆቻችን በዚህ ህግ ካልታነፁ፤ ይጠፋፋሉ፡፡

 

አሪስጣጣሊስ፤ ፍጡር ከአዕምሮው ብቃት የተነሳ ጌታ ወይም አለቃ፤ ሌላው ደግሞ ተገዢ ወይም አሽከር ይሆናል፡፡ አንድ ፍጡር አዕምሮውን ተጠቅሞ መጪውን ነገር አስቀድሞ ለማየት ከቻለ፤ ተፈጥሮ ያን ፍጡር ጌታ እና አለቃ አድርጋ ልታኖረው መርጣዋለች ማለት ነው፡፡ በተቃራኒው፤ አንድ ነገር ሲደርስበት በአካሉ ምላሽ ከመስጠት በቀር፤ በህሊናው ኃይል አስቀድሞ መጪውን ለማየት የማይችለውን ፍጡር ተገዢ (ተመሪ) እንዲሆን ደንግጋለች ይላል፡፡ ሰው ሰው በጉልበት በሚበልጡት አንስሳት ላይ ሊሰለጥን የቻለው በአዕምሮው ብቃት ነው፡፡ ስለዚህ ሰው ከእንስሳት ይበልጣል፡፡

 

አሪስጣጣሊስ እንደሚለው፤ ሰው ገና ሲወለድ አዕምሮ የሚባል ልዩ ጸጋ ታጥቆ የሚወለድ ነው፡፡ ታዲያ ይህ መሣሪያ ለልማትም ሆነ ለጥፋት ሊውል ይችላል፡፡ ይህ የታጠቀው መሣሪያ በአስተዋይነት፣ በግብረ ገብነት እና በትክክለኛ የፖለቲካ መርህ ተገርቶ በጥቅም ላይ ካልዋለ፤ በአጭሩ ሰው ግብረ ገብነት የሌለው ፍጡር ከሆነ፤ በማዕረጉ ከእንስሳትም የወረደ ርኩስ፣ ጨካኝ ወይም አረመኔ ይሆናል፡፡ የ‹‹መደመር›› ህግ መገለጫ የሆኑትን (የሌሎችን ነጻነት ማክበርን፤ እንስሳት እና ዕጽዋትን ጨምሮ ለመሰሉ ለሌሎች ፍጡራን ማሰብን፤ ፍትሕን ማክበርን) ካላከበረ፤ ርኩስ፣ ጨካኝ ወይም አረመኔ ይሆናል፡፡ አሪስጣጣሊስ እንደሚለው፤ አዕምሮን የመሰለ ልዩ ጸጋ እና ከባድ መሣሪያን የታጠቀው የሰው ልጅ ኢ-ፍትሐዊ ከሆነ በጣም አደገኛ ጥፋት ሊያመጣ የሚችል ነው፡፡ በመልካም እሴት ያልታነጸ አዕምሮ፤ አደገኛ መሣሪያ የታጠቀ የኢ-ፍትሐዊነት መሣሪያ ነው፡፡ ለሌሎች ፍጡራን በማሰብ እና በፍቅር ስሜት ያልተገራ እውር ፍላጎት እና አልጠግብ ባይነትም፤ መጪውን ነገር አስቀድሞ በማየት የተፈጥሮ ጸጋው መጠቀም ያልቻለ እና በጥፋት ስሜት የተሞላ መንፈስ ነው፡፡ ስለዚህ ሌሎችን ያጠፋ እና ውሎ አድሮ እርሱም ይጠፋል፡፡ ጌታ ለመሆን ተወልዶ፤ የማይረቡ ነገሮች ባሪያ ይሆናል፡፡ የሚኖርበት ማህበረሰብም ሰላም ያጣል፡፡

 

ምክንያቱም፤ ሰዎችን እንደ አንድ አካል በሰላም አስተሳስሮ የሚይዝ ማህበራዊ ገመድ ፍትሕ ነው፡፡ የአንድ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ሰላም እና መረጋጋት የሚረጋገጠው በፍትሕ መስፈን ነው፡፡ ሆኖም ሰዎች በእውር ፍላጎት እና በአልጠግብ ባይነት እየተመሩ ሰዎችን በሰላም አስተሳስሮ የሚይዘውን ማህበራዊ ገመድ ወይም ፍትሕን በመጉዳት፤ የሰዎችን ሰላም እና ህብረትን ያጠፉታል፡፡ መደመር ይህን የተፈጥሮ መሠረት ያለው ማህበራዊ ህግን እንድናስታውስ ጥሪ የሚያቀርብ ፍልስፍና ነው፡፡

 

ዝቅተኛው የሰዎች ህብረት ቤተሰብ ነው፡፡ ይህ የሰዎች ህብረት መሠረቱ ፍቅር ወይም መደመር ነው፡፡ የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት ፍላጎት ለማሟላት የተመሠረተ ህብረት ነው፡፡ ‹‹ቤተሰብ›› በተፈጥሮ ህግ የተመሠረተ እና የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት ፍላጎት ለማሟላት የሚያግዝ፤ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ የሚፈጠርበት ህብረት ነው፡፡ ነገር ግን የሰዎች ህብረት በቤተሰብ ብቻ አይወሰንም፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ ከህብረተሰብ ማህጸን አንደገና ይወለዳል፡፡ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ በርካታ ቤተሰቦች የዕለት ተዕለት ፍላጎትን ከሟሟላት ከፍ ያለ ሌላ ዓላማን ለማሳካት ህብረት ይፈጥራሉ፡፡ በመሆኑም፤ በዚህ ሂደት በመጀመሪያ ሊፈጠር የሚችለው ህብረት መንደር ነው፡፡ የተፈጥሮ ጎዳናን ተከትሎ በተፈጠረው በዚህ ህብረት (መንደር) ልጆች እና የልጅ ልጆች ይኖራሉ፡፡ አንድ ጡት ጠብተው የሚያድጉት የአንድ ማህጸን ፍሬ ወገኖች በአንድ የሚኖሩበት መንደር ነው፡፡ ከመንደር ከፍ ያለ ህብረትም አለ፡፡ አሪስጣጣሊስ፤ በበርካታ ቤተሰቦች ስብስብ የሚፈጠረውን ህብረት፤ ‹‹ኮሎኒ›› ይለዋል፡፡ እነዚህ በደም፣ በባህል፣ በቋንቋ ወዘተ የተሳሰሩ ይሆናሉ፡፡ በደም፣ በባህል፣ በቋንቋ ከፍ ብሎ በሲቪክ አስተሳሰብ ትስስር የሚፈጠርበት ሐገር የሚባል ህብረትም አለ፡፡ ይህ ህብረት፤ ዜጎች በአንድ በኩል ገዢ፤ በሌላ በኩል ተገዢ የሚሆኑበት ህብረት ነው፡፡ ‹‹ሰው በተፈጥሮ ፖለቲካዊ እንስሳ ነው፡፡ በመሆኑም፤ የመንግስት ምስረታ የአጋጣሚ ሳይሆን ከተፈጥሮ ግዴታ የመነጨ ክስተት ነው›› የሚለው አሪስጣጣሊስ፤ ‹‹መንግስት (ስቴት) የሌለው ሰው፤ አንድም መጥፎ ሰው ነው፤ አለያም ከሰው የላቀ ማዕረግ ከመልዐክ የሚታሰብ ሌላ ዓይነት ፍጡር ነው›› ይላል፡፡ እስካሁን እንዳየነው፤ ይህ ህብረት መሠረቱ መደመር ወይም ፍቅር ነው፡፡ መሠረቱ፤ የሌሎችን ነጻነት ማክበር፣ ለመሰል ለሌሎች ፍጡራን ወይም ሰዎች (እንስሳት እና ዕጽዋትን ጨምሮ) ማሰብ እና ፍትሕን ማክበር ነው፡፡

 

ስለዚህ ጠ/ሚ ዐቢይ እንዳሉት፤ በፍቅር ህግ የፈጠርናቸውን ልጆቻችንን በጥላቻ ህግ ካሳደግናቸው፤ ውሎ አድሮ እርስ በእርስ የሚበላሉ እና የሚጠፋፉ በመሆናቸው፤ ለምን እንወልዳቸዋለን? ማንሳት አለብን፡፡ ስለዚህ ጠ/ሚ ዐቢይ ‹‹መደመር›› ሲሉ የህይወትን መሠረታዊ ህግ እያስታወሱን ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት የተጓዝንበት ጎዳና አንዳንድ አጥፊ የሆኑ ነገሮች እንዳሉት አይተው እና አስተውለው፤ ይህን ስህተት ለማረም ‹‹እንደመር›› አሉ፡፡ መደመር የፍቅር ህግ ማስታወሻ ቀላል ቃል ነው፡፡ የህይወት እና የህብረተሰብን ቋሚ እና ዘላለማዊ ህግን መዘከሪያ ቃል ነው፡፡ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች መድህን የሚሆን ፍልስፍና ነው፡፡

 

በአሁኑ ጊዜ የበለጸጉ ሐገራት መንግስታት ስደተኞችን እና ፍልሰተኞችን በተመለከተ ከመደመር ፍልስፍና የራቀ አመለካከት ሲያምደ እናያለን፡፡ ስደተኞችን እና ፍልሰተኞችን በተመለከተ የጋራ ስምምነት አጥተው ሲቸገሩ እናያለን፡፡ በዚህም የተነሳ በመንግስታቱ መካከል አለመግባባት እየተፈጠረ ይታያል፡፡ የስደተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እና ጉዳዩም ውስብስብ እየሆነ ቢመጣም፤ በበለጸጉት ሐገራት በመንግስታት ዘንድ የሚታየውም ድንበር የመክፈት ሳይሆን የመዝጋት አዝማሚያ በመሆኑ፤ በዘርፉ የተሰማሩን ሰዎችን ወይም ባለሙያዎችን የሚያሳስብ ችግር ሆኗል፡፡ በዚህ የተነሳ በዘርፉ የተሰማሩን ሰዎች የወደፊቱ ነገር ብሩህ ሆኖ አይታያቸውም፡፡ በመሆኑም፤ ትልቅ ትኩረት ሊሰጥ የሚገባው የስደት ምንጭ የሆኑ ምክንያቶችን የማስወገድ ሥራ ቢሆንም፤ ችግሩ በመደመር ፍልስፍናም መፍትሔ ማግኘት አለበት፡፡  

ኢትዮጵያ እንደ በለጸጉት ሐገራት ሐብት ባይኖራትም፤ ስደተኞችን በፍቅር ተቀብላ የምታስተናግድ ሐገር ነች፡፡ ከተለያዩ የጎረቤት ሐገራት መጥተው፤ እኤአ ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ እየኖሩ ያሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ እየኖሩ ያሉት ስደተኞች የሐገሪቱ አቅም ዝቅተኛ በመሆኑ እና ከውጭ የሚገኘውም ድጋፍ ያን ያህል በቂ የሚባል ባለመሆኑ ብዙ ምቹ ነገር ባይኖራቸውም፤ እነሱን ማስተናገድ በማስተናገድ በተፈጥሮ ሐብት ላይ ጫና የሚያሳድር ቢሆንም፤ ሐገራችን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኞች አቅፋ ደግፋ ይዛለች፡፡

የምንከተለው ፖሊሲም  ስደተኞች ከማህበረሰቡ ጋር ተዋህደው የሚኖሩበትን ሁኔታ በማመቻቸት እና የሥራ ዕድል አግኝተው ራሳቸውን መደገፍ የሚችሉ እንዲሆኑ በማድረግ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የስደተኞች ፕሮግራምም ከሰብአዊ እርዳታ ወደ ልማት ድጋፍ ይለወጣል፡፡ አሁን ያለው የኢትዮጵያ የስደተኞች ፖሊሲ፤ ስደተኞች ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ ማድረግን (ኢንተግሬሽንን) የሚደግፍ ነው፡፡ አሁን ባለው እቅድ ከ10 ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ ስደተኞች ካምፕ አይኖርም የሚል ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ስደተኞችን በተመለከተ የምታደርገው ጥረትም በሰብዐዊ መብት አያያዝ ረገድ በአንዳንድ ወገኖች የሚደርስባትን ወቀሳ እና የሥም ስብራት የሚጠግን ነው፡፡ ይህ የመደመር ፍልስፍና ዓለም አቀፍ ገጽታ ተደርጎ ሊሰወሰድ የሚችል ነው፡፡ መደመር የምሥራቅ አፍሪካን አየር በምን ፍጥነት እንደ ቀየረውም እያየን ነው፡፡