ማሸነፍ ሳይሆን ማክሸፍ…

የኢፌዴሪ ጠቅይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ የመከላከያ መኮንኖችን ሲያስመርቁ፣ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለው የመንጋ ፍትህ እና አላስፈላጊ ሁከት ተቀባይነት የሌለው እንዲሁም የህግ የበላይነትን አደጋ ውስጥ እንደሚጥል መናገራቸው ይታወሳል። ዶክተር አብይ ይህን ጉዳይ በወቅቱ ያነሱት በሀገራችን አልፎ አልፎ የሚታየው የመንጋ ፍትህ አሰጣጥ ሁኔታ በምንም ዓይነት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ለህብረተሰቡ ለማስገንዘብ ነው።

እርግጥ ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ የተሳሳተ መረጃን መሰረት በማድረግ ለህግ ቅድሚያ ሳይሰጥ የሚፈጽማቸው ድርጊቶች እየተገነባች ያለችን አገር ከማፍረስ ውጭ ዋጋ የለውም። እንዲሁም የማሸነፍ አቅም የሌላቸው የቅልበሳ ሃይሎች ዋነኛ ዓላማና ተልዕኮ ማሸነፍ ሳይሆን ማክሸፍ በመሆኑ ይህን እንዲፈፅሙ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል።

ስለሆነም እንዳይሆን ህግና ስርዓትን ያልተከተለው የመንጋ ፖለቲካ መቆም ይኖርበታል። መንግስት በአገራችን ውስጥ የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚወስዳቸው እርምጃዎች ይህን እውነታ ታሳቢ ያደረጉ በመሆናቸው ህዝቡም ለውጡ ሳይደናቀፍ እንዲቀጥል በዚህ ረገድ የተለመደውን ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል።  

በህግ ማስከበር ስራ ውስጥ የሚከናወኑ ጉዳዩች የሚጠቅሙት ህብረተሰቡን ነው። የህግ የበላይነት ለአንድ ሀገር ማህበረሰብ መጠበቅ መሰረት ነው። ከህግ በላይ የመሆን ዝንባሌ የትኛውንም ወገን አይጠቅምም። አሁን በምንገኝበት የዘመነው 21ኛው ክፍለ ዘመን ከህግና ከስርዓት ውጭ መሆን አይቻልም።

ለነገሩ ዘመናዊነት የህግ የበላይነትን ማክበር ነው። በዚህ ዘመን ለህግና ለስርዓት መገዛት የግድ ይላል። ምክንያቱም ለህግ የማይገዙ ዜጎች በህግ የሚገዙ አምባገነኖችን ሊፈጥሩ ስለሚችሉ ነው። ይህ እንዳይሆንም ህግንና ስርዓትን በማክበር ማናቸውንም ስራዎች በህግ አግባብ ማከናወን ያስፈልጋል። ህጋዊ ስርዓትን እያዳከሙ በመንጋ የሚሰጥ ፍትህን መከተል ሀገርንና ስርዓትን ወደ ማይገባ ተግባር እንዲሁም ሁሉንም ጉዳዩች በኪሳራ የሚጨርስ ነው። በአሁኑ ወቅት እንደመር እየተባለ በይቅርታ የሚከናወን ተግባር ትናንት ያጣነውን ነገር ለመመለስ እንጂ በለውጥ ጎዳና ላይ ያለችውን ሀገር ውጤቱ ለከፋ ቀውስ ለመዳረግ አይደለም። እናም ህግንና ስርዓትን አክብሮ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል።

በለውጡ እጅግ በተጠናከረ ሁኔታ የቀጠሉት የዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደቶች ስኬታማ እንዲሆኑ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነበት ምህዳርን መፍጠር ተገቢ ነው። ለዚህ ደግሞ የመንጋ ፍትህ መቆም አለበት። አገራችን ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት ትችል ዘንድ ማናቸውንም ጉዳዩች በህግ ልዕልና ስር ሆኖ መፈፀም ያስፈልጋል።

ለውጡ የህግ የበላይነትን የሚያከብር ነው። ዶክተር አብይ እንዳሉት መንግስት ህግንና ስርዓትን ተከትሎ ይሰራል። ስለሆነም የህግ የበላይነትን ተላልፎ የሚገኝ ማንኛውም ዜጋ ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም። በለውጥ ሂደት ላይ ያለችው አገራችን ውስጥ ማንኛውም ሰው  በህግ ፊት እኩል ቁመና አለው። ለውጡ እየተተገበረ ያለው አድልኦን ለማስቀረት በመሆኑ በማንም ላይ የሚፈፀም አድልኦአዊ አሰራር አይኖርም። የትኛውም ወገን ትልቅም ትንሽም አይደለም። በህግና በስርዓት የሚፈፀሙ የህግ ልዕልናን የማስከበር ተግባሮች ግለሰቦች በመረጃና በማስረጃ በተረጋገጠባቸው ጥፋት ልክ ተጠያቂ እንዲሆኑ ይደረጋል። ይህ አሰራር በሁሉም ዜጎች ላይ ገቢራዊ የሚሆን ነው። 

አዲሲቷ ኢትዮጵያ በለውጥ ስኬታማ ሂደት ላይ ናት። ለውጥ ደግሞ ሰላምን ይሻል። ስለሆነም ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ለብሔራዊ ደህንነቷ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከልና መቆጣጠር ይኖርባታል። ለዚህም ዘንድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ አለባት።

እርግጥ ህግና ስርዓት ባልተተገበረበት ሁኔታ ዜጎች በሰላም ስራቸውን አያከናውኑም። ይህም የአገራችን እድገት ይጎትታል። ከህግ ውጭ የመንጋ ፍርድ በመስጠት ራስ ከሳሽ ራስ ፈራጅ መሆን ከተጀመረ ስርዓት አልበኝነት እንዲገነግን ያደርጋል።

ስለሆነም ሁሉም ህግንና ስርዓትን በማስከበር የድርሻውን ተግባር መወጣት አለበት። ህግና ስርዓትን ይበልጥ አጠናክሮ የማስከበር ስራ የሁሉም ዜጋ ድርሻ መሆኑም ሊታወቅ ይገባል። አሊያ ግን አገር ወደማትወጣው መጥፎ ሁኔታ ውስጥ መግባቷ አይቀርም። ይህ እንዳይሆን በህገ መንግስቱ መሰረት ህግንና ስርዓትን ማስከበር ተገቢ ይሆናል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የእኩልነት መብት በሚለው የህገ መንግስቱ አንቀፅ 25 ላይ “ሁሉም ሰዎች በህግ ፊት እኩል ናቸው፤ በመካከላቸውም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በህግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል።…” በሚል የተደነገገው ጉዳይም ዜጎች መብቶቻቸው ሳይሸራረፉ በህግ የተጠበቁ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው።

ስለሆነም ዜጎች መብቶቻቸውን ሳይሸራረፉ ለመጠቀም እነርሱ ያላቸውን መብት ሌሎችም እንዳላቸው መገንዘብ ይኖርባቸዋል። የራስን መብት ለማስከበር የሌሎችን መብትን አለመጋፋት ዘመናዊነት ነው። ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል የመሆኑ እውነታ የሚመነጨውም ከዚህ መሰረታዊ ሃቅ በመነሳት ነው።

በህግ ፊት እኩል መሆን የተቃዋሚንም ይሁን የደጋፊን እንቅስቃሴ አይገድብም። ሁሉም ዜጋ በአንድ ዓይነት ሁናቴ እንዲታይ ያደርጋል። ምክንያቱም ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚመለከት ስለሆነ ነው።

ስለሆነም እዚህ ሀገር ውስጥ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ያለአንዳች ስጋት እንዲንቀሳቀስ የሚፈቅድ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ህግን ማክበር ይህን መሰሉን ጠቀሜታ ያስገኛል።

የህግ የበላይነት ልዕልና ካልተጠበቀ በሀገሪቱ የሚረቀቁ ማናቸውም ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ሊሆኑ አይችሉም። ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ካልሆኑና በቸልታ የሚታለፉ ከሆኑ የዜጎች መብቶች ሊሸራረፉ ይችላሉ። የመብት መሸራረፎች ደግሞ አንዱ እንዳሻው እንዲፈነጭ የሚያደርገው ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ህግና ስርዓትን አክብሮ እንዲንቀሳቀስ ያደርገዋል። እንዲህ ዓይነት የህግ እኩልነት የለም።

እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ህግና ስርዓትን የሚያከብረው ዜጋ ሌላውን በመመልከት ወደ ተሳሳተ መንገድ ሊያመራ ይችላል። በመሆኑም ይህን ችግር ለመቅረፍም የህግ የበላይነት ልዕልና ገቢራዊ መሆን አለበት። በመሆኑም ህግና ስርዓትን የማስከበር ተግባር በሀግ አስፈፃሚው አካል በሚፈፀምበት ወቅት የተለየ ትርጓሜ ሊሰጠው አይገባም። ስለሆነም መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስፈፀም የሚያከናውናቸው ተግባራት የሚጠቅመው ህዝቡንና አገርን በመሆኑ ህብረተሰቡ ከዚህ ህጋዊ አሰራር ጎን መቆም ይኖርበታል። ይህም የማሸነፍ አቅም የሌላቸውና ለውጡን ማክሸፍ ዓላማዬ ብለው የሚሰሩ ጥቂት ሃይሎችን የሚገታ ተግባር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።