የድንበሩ ጉዳይ

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ከድንበር ጋር በተያያዘ የኢትዮ-ሱዳን ሁኔታን አንስተዋል። በዚህም የሱዳን አጎራባች በሆኑ የአማራ ክልል አካባቢና በሱዳን በኩል ያለው የድንበር ወሰን መልክ ባለመያዙ ችግሮች እንደተከሰቱና በመሪዎች ደረጃ በቅርቡ በተካሄደ ውይይት በሁለቱም በኩል ታጣቂዎች ከድንበር እንዲርቁና ጥበቃውን በጋራ ለማካሄድ ስምምነት ተደርሷል።

ኢትዮጵያና ሱዳን በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል ወዳጅነት ያላቸው አገራት ከመሆናቸውም በላይ፣ ህዝቦቻቸውም በደም፣ በእምነት፣ በባህልና በወግ የተሳሰሩ ናቸው። ይህ ትስስራቸውም የሚፈጠሩ ማናቸውንም ችግሮች በመነጋገርና በመወያየት ለመፍታት ያስችላቸዋል።

ስለሆነም የድንበር ማካለሉ ጉዳይም በድርድር የሚፈታ ነው። ሁለቱ አገራት ከሚያለያያቸው ይልቅ የሚያስተሳስራቸው ጉዳዩች በርካታ በመሆናቸው የሚፈጠሩ ጊዜያዊ ችግሮችን በጋራ የመፍታት ባህልን ሲያዳብሩ የመጡ ናቸው። የድንበር ጉዳያቸውንም ከዚሁ አንፃር በመፍታት ለሌሎች አገራት አርአያነታቸውን ማረጋገጣቸው አይቀርም።

ሱዳን ለአገራችን ጠቃሚ የመሆኗን ያህል፣ ኢትዮጵያም ለሱዳን ጠቃሚ ናት። ዶክተር አብይ ወደ ሱዳን ባደረጉት ጉብኝት ይህን ማረጋገጥ የተቻለ ይመስለኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ኢትዮጵያ በፖርት ሱዳን ወደብን በጋራ ማልማት የምትችልበትን ሁኔታ እንድታገኝ በማድረግ ተስማምተዋል። ይህም ለሱዳንም ይሁን ለኢትዮጵያ እጅግ ጠቃሚ ነው።

የአገራችን ወጭና ገቢ ንግድ እየጨመረ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ፖርት ሱዳንን በጋራ የማልማት ስምምነት ተገቢነቱ አያጠያይቅም። ሱዳንም ቢሆን በጋራ ከሚለማው ወደብ ተጠቃሚ ትሆናለች። ኢኮኖሚያዊ ትስስሩም ይዳብራል።

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱም ይጠናከራል። ይህም በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ እንዲመጣ የሚፈለገውን የኢኮኖሚ ውህደት በማፋጠን የአገራቱን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ይሆናል። በሀገራቱ መካከል የተዘረጋው የየብስ ግንኙነት እየተጠናከረም የህዝቦችን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል።

እንዲህ ዓይነት በአጭር ጊዜ ውስጥ የተፈጠረ ጠንካራ ግንኙነት በድንበር ሳቢያ የሚላላበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሱዳን በአሁኑ ወቅት ያለውን የለውጥ አመራር የጋራ ተጠቃሚነት መርህን በሚገባ የምትገነዘብ አገር ናት።

እንደሚታወቀው ሁሉ አገራችን በምትከተለው ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መርህ በሱዳንም ተቀባይነት አላት። በዚህ አስተሳሰቧም የአባይ ውኃ አጠቃቀም ፍትሃዊ በሆነ መልኩ መጠቀም አስፈላጊነቱን አምናም እየሰራች ነው።

የናይል የላይኛው ተፋሰስ ሀገሮች የጋራ ማዕቀፍ ፈርማ ወደ ማጽደቅ ሂደት በመግባት ላይ ነች። ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባት ማለት ስድስት ሺህ 450 ሜጋ ዋት በማመንጨት ዓላማዋ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ጎረቤት ሀገሮችንም መጥቀም ስለሆነ ነው። ይህን እውነታ የምትገነዘው ሱዳን በማንኛውም ሁለት አገራት መካከል ሊፈጠሩ የሚችሉ ጊዜያዊ ችግሮችን በቀላሉ በድርድር መፍታት የምትችል አገር ናት።

ሱዳን ለኢትዮጵያ ጠቃሚ የመሆኗን ያህል፣ ኢትዮጵያም ከሱዳን ጋር በአብሮነት ብዙ ተግባራትን ከውናለች። እርግጥ በጐረቤት አገር ሱዳን የተቀሰቀሰውን አለመረጋጋት እልባት ከመስጠት አኳያ የአንበሳውን ድርሻ ከተወጡት የአፍሪካ ቀንድ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ናት።

ሱዳን በአፍሪካ ውስጥ በቆዳ ስፋቷ ቀዳሚ ሀገር ስትሆን ለጥ ያለና ውሃ ገብ የሆነው መልከዓ ምድሯ እንዲሁም ሰፊ የተፈጥሮ ሃብቷ ለታላቅ ዕድገት መብቃት የምትችል እንደሆነች ብዙዎቹን ያስማማ ሃቅ ቢሆንም ቅሉ፤ አገሪቱ ግን ለበርካታ ዓመታት በዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ቆይታ ነበር። በዚህም ለከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ቀውስ ልትዳረግ በመቻሏ ለተቀሰቀሰው አለመረጋጋት እልባት ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።  

እንደሚታወቀው ሁሉ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል የነበረውን አለመግባባት በመፍታት፣ በዳርፉርና በአብዬ የተከሰቱ ችግሮችን በመቅረፍና የሰላም አስከባሪ ሰራዊት በማሰማራት ኢትዮጵያ የተጫወተችው ሚና እጅግ የላቀ ነው።

መንግስት በጎረቤት ሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ያደረገው ጥረት የጐረቤቶቻችን ሰላም ለአገራችን የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታችን መፋጠን ካለው ፋይዳ አኳያ ነው። ምክንያቱም እኛ ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለመዋጋት የምናደርገው ትግል ሊሳካ የሚችለው ጐረቤቶቻችን ሰላም ከሆኑ ነው።

እርግጥም የጎረቤቶቻችን ሰላም መሆን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለእኛ ሰላም መጐልበት ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። በአገራችን ሰላም ላይ የቅርብ ተጽዕኖ ያላት የሱዳንን ችግር ለመቅረፍ በመንግስታችን የተካሄደው ጥረት ምንጩ አገራዊ ህልውናን የማረጋገጥና የጋራ ተጠቃሚነትን እውን ለማድረግ ነው።

ከዚህ በመነሳትም የሱዳንና የኢትዮጵያ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ያተኮረ ሆኗል። ይህም በንግድ፣ በመሰረተ ልማት፣ በኢንቨስትመንትና በፀጥታ ጉዳዩች ላይ ያተኩራል። በአሁኑ ሰዓት አገራችን ከሱዳን ጋር ያላት መልካም ግንኙነት ቀጣናውን በልማት ለማስተሳሰር የምታደርገውን ጥረት እንደሚያጎለብት ተስፋ ተጥሎበታል። ይህም አንዱ የዲፕሎማሲ ድል ነው።

ሱዳን ቀደም ባሉት ዓመታት በውስጧ የተፈጠረውን የእርስ በርስ ግጭት የኢፌዴሪ መንግስት ከኢጋድ ጋር በመሆን ችግሩን ለመፍታት ጥረት አድርጓል። በዚህም ውጤቶች ተገኝተዋል። ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ለረጅም ጊዜያት ሲያካሂዱት የነበረውን ጦርነት በሪፈነደም መፍታት እንዲችሉ ኢትዮጵያ ጠንካራ ሚና ነበራት።

የመንግስታችን ከጐረቤት ሃገሮች ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት የመፍጠር ጥረት በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሀገሪቱ ለጀመረችው የፈጣን ልማት ቀጣይነት መረጋገጥ ብቸኛው አማራጭ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ይህን መነሻ ታሳቢ ባደረገ መልኩም መንግስታችን ለሰላም ካለው ጽኑ አቋም በመነሳት ለዘመናት የእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ለቆየችው ጐረቤት ሀገር ሱዳን፣ ሰላም መስፈን ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ይህ ሁኔታም በሁለተ አገራት ህዝቦች መካካል ጠንካራ ትስስርን የፈጠረ ነው። ስለሆነም እንዲህ ዓይነት ለዘመናት የዘለቀ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ያላቸውና በቅርብ ጊዜ ውስጥም በጋራ ተጠቃሚነት እየሰሩ ያሉ አገሮች በጊዜያዊ የድንበር ጉዳይ ሊወዛገቡ አይችሉም። መግባባቱና መደማመጡ ከፍተኛ ስለሆነ ማናቸውንም ችግሮች በድርድር የመፍታት አቅም ያላቸው አገሮች ናቸው።