የስበት ማዕከል

በአሁን ሰዓት አዲሲቷ ኢትዮጵያ በማካሄድ ላይ ያለችው ለውጥ እየደገፉ ያሉ የዓለም አገራት ቁጥር እንደተበራከተ ነው። በመሆኑም ይህን አዎንታዊ የዲፕሎማሲ ገፅታ ማጠናከር ያስፈልጋለ። በአሁን ሰዓት ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስበት ማዕከልነቷ ጨምሯል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና መንግስታቸው በፈጠሩት ፈጣን የዲፕሎማሲ አውድ በወራቶች ውስጥ ብቻ በርካታ እንግዶችን አስተናግደዋል። እያስተናገዱም ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ የዓለም አገራት የሚመጡ እንግዶችን እየተቀበሉ ነው። የመሪዎችን መልዕክተኞች ደብዳቤ እየተቀበሉ ይወያያሉ፤ አዎንታዊ ምላሽም ይሰጣሉ። ሰሞኑን ወደ አገራችን የመጡትን የአሜሪካ ኮንግረንስ አባላትን፣ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑካንን፣ የማሌዥያ ፕሬዝዳንት ጉብኝትን ማንሳት ይቻላል።

ምን ይህ ብቻ። ዶክተር አብይ በ“ዋን ሮድ ዋን ቤልት” ለመገኘት ወደ ቻይና በመጓዝ ያደረጓቸው ጠቃሚ ስምምነቶች የዚሁ አካል ናቸው። ታዲያ እነዚህ የጥቂት ሳምንታት ዲፕሎማሲያዊ ክንዋኔዎች የሚያሳዩን ነገር ቢኖር፤ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሰሚነቷ እየጨመረና የዲፕሎማሲ የስበት ማዕከል እየሆነች መምጣቷን ነው።

ዶክተር አብይ የተከተሏቸው የዲፕሎማሲ አቅጣጫዎች ለተሰሚነታችን የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱ ናቸው። የዲፕለማሲ ግንኙነታቸው የአካባቢውንና ጎረቤት ሀገሮችን ለጋራ ጥቅምና ሠላም እንዲሰሩ የሚጋብዝና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ነው። ብሔራዊ ጥቅማችንን የሚያስጠብቅና አገራዊ ህልውናችንንም የሚያረጋግጥ ነው።

እርግጥ ኢትዮጵያ ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖራት ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የአገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን በከፍተኛ ደረጃ በሚቀንስ ደረጃ የተተለመ ነው። በተለይ አገራችን ከቀጠናው አገራት ጋር የምታደርገው ግንኙነት የህዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው።

የአገራቱ የዲፕሎማሲ ትስስር የቀጠናውን ህዝቦች ጥቅም ያማከለ ነው። የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ በባህል፣ በታሪክ፣ በአብሮ መኖር፣ በመዋለድና አንዱ የሌላኛውን ሀገር እንደ ሁለተኛ መኖሪያው በመቁጠር የቅርብ ግንኙነት የታጠረ ነው።

በመሆኑም የቀጣናው ሀገራት ይህን ዘመናትን የተሻገረ የህዝቦች ጥብቅ ቁርኝት በዘመናዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ይበልጥ አጥብቀው ለማሰር ተስማምተዋል። ለዚህ ደግሞ በየጊዜው እየተገናኙ የሚያደርጓቸውን ስምምነቶች ወደ ተግባር እየተለወጡ ነው። ዶክተር አብይ ከአገራቱ ጋር በአጭር ጊዜ ውስጥ ያደረጉት ውይይቶች ይህን መሰረት ያደረገ ነው።

አገራችን የልማት እመርታዋ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በዙሪያዋ ያሉት ጎረቤቶቿም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጠንካራ አካባቢያዊ ትብብርና የዲፕሎማሲ ቁርኝት እየፈጠረች ነው። ይህን በበቂ ሁኔታ እየተጠቀመችበት መሆኑ አያጠያይቅም።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ የሚፈጠር አለመረጋጋትን በመረጋጋት በመተካት፣ የተጎዱትን በማቋቋምና የተቸገሩትን በመርዳት የማይናወጥ አቋሟን ስታንጸባርቅ የኖረች አገር ናት። አህጉሪቱን ከቅኝ አገዛዝ ሙሉ በሙሉ በማውጣትና አፍሪካውያን ነጻነታቸውንና ክብራቸውን ለመመለስ እንዲሁም አፍሪካን ወደ ኢኮኖሚ ዕድገት ለመምራት በተደረገው ትግል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስታደርግም ቆይታለች።

ይህን የአገራችንን ነባር ባህል ይበልጥ ለማጎልበትና በአፍሪካ ውስጥ ያላትን የመሪነት ሚና ለመወጣት ዶክተር አብይ እየሰሩ ነው። ይህም በአፍሪካዊያንም ይሁን በሌሎች አገራት እንድትፈለግ ያደረጋት ሌላው ጉዳይ ነው።

ዛሬ በለውጡ ምክንያት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድም ያለን ተቀባይነት ከፍተኛ ሆኗል። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ መድረክም በአዲስ ገፅታ እየታየች ነው። በዚህም ሳቢያ ሀገሪቱ በምስራቅ አፍሪካም ይሁን በዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ መድረኮች ተሰሚነቷ ጎልቶ ወጥቷል።

በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መጥቷል። አገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን የተገነዘቡ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት የማሳየታቸው ምስጢርም ይኸው ይመስለኛል።

አገራችን በአሁኑ ሰዓት ትክክለኛ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ በግሉ ባለሃብት መሰራት የሚገባቸውና በመንግስት ሊከናወኑ የሚገቡ ተግባራት ተለይተው በመካሄዳቸው በሁለቱም በኩል ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው። ቀደም ሲል ያጣነውን እያገኘን ነው።

በአጭር ጊዜ ውስጥ የአገር ውስጥም ይሁን የውጭ ባለሃብቶችን የሚሰማሩባቸውን ዘርፎች በመለየት አንፃራዊ በመሆነ መንገድ ለአገሪቱ ዕድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ እየተደረገ ነው።

ባለፉት አራት ወራት ውስጥ ለዜጎች የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸው በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ እየተደረገ ነው። በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ዘርፍ የተገኘው ውጤት አበረታች ነው። ለዚህም በዶክተር አብይ ጋባዥነት የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የጂማ ኢንዱስትሪያል ፓርክን እንዲጎበኙና መዋዕለ ነዋያቸውን እነዲያፈሱ በማድረግ የተጫወተቱትን ሚና መጥቀስ ይቻላል።

እንዲህ ዓይነቱ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ጥረት ቀጥተኛ የውጭ ምንዛሬን የሚያመጡና በአገር ውስጥ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችንም የሚደግፍ ነው። የውጭ ምንዛሬ በበቂ ሁኔታ ማግኘት በአገር ውስጥ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን ያለ ስጋት ማከናወን ይቻላል።

ኢትዮጵያ ሰላማዊና የሚያሰራ የኢንቨስትመንት ድባብና ማበረታቻ እንዲሁም መስራት የሚችል የሰው ኃይል ያላት አገር ናት። የውጭ ምንዛሬ ግኝትን እያገኘች ያለችው በዚሁ ምክንያት ነው ማለት ይቻላል።

በአሁኑ ሰዓት አገራችን እያገኘች ያለችው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የስራ ዕድልን እየፈጠረ ነው። ይህም የዜጎችን ተጠቃሚነት በመፍጠር ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል። ታዲያ እነዚህን ሁሉ ተጠቃሚነቶች ለማጎልበትና የአገራችንን ተደማጭነት ብሎም የአገራት የስበት ማዕከልነቷን ለማረጋገጥ ሰላማችንን ማጠንከር ይኖርብናል።