ብስሉን ከጥሬው…

የሰው ልጅ በምድራዊ ላይ እስከኖረ ድረስ፤ በዘፈቀደ ሊንቀሳቀስ አይችልም። በየትኛውም የዓለም ክፍል ውስጥ ሰው የሚመራበት ያልተፃፉና የተፃፉ ህጎች አሉት። እነዚህ ህጎች ልማዳዊ ወይም የተፃፉ ሊሆኑ ይችላሉ። ልማዳዊ ህግ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚከበሩና ህብረተሰቡ ቅቡል ያደረጋቸው ባህሎች፣ የሞራል እሴቶችና ትውፊቶች ናቸው። እነዚህን ልማዳዊ አሰራሮች ተላልፎ የሚገኝ ግለሰብ ወይም ቡድን በዚያ ማህበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። በሌላ ዘውጉ ደግሞ፤ ልማዳዊ አሰራሮችንና ግብረ ገባዊ ወይም ሞራላዊ እሴቶችን (Moral Values) አክብሮ የሚንቀሳቀስ ግለሰብ የከበሬታ ካባን እያጣፋ በኩራት ይደርባል።

“ነገር በምሳሌ፤ ጠጅ በብርሌ” እንዲሉ አበው፤ ይህን እውነታ በምሳሌ አስደግፌ ልግለፀው—ጠጁን ከነብርሌው ወደ ጎን በማለት። ሁላችንም እንደምናውቀው፤ በሀገራችን ህዝብ ውስጥ ታላላቆችን ማክበር ማህበረሰቡ በስምምነት ያቀደቀው የሞራል እሴት ነው። በካፌዎች፣ በከተማ ታክሲዎና በአውቶቡሶች አሊያም በሌሎች ማህበራዊ መገልገያ ቦታዎች ውስጥ አንድ አዛውንት ቆመው ወጣት ልጅ ወንበር ይዞ ከተቀመጠ በነውርነት የሚታይ ድርጊት ነው። ምክንያቱም ወጣቱ ለአዛውንቱ የመነሳት የሞራል ግዴታ አለበት። ይህ ማህበረሰቡ ተቀብሎ ያፀደቀው ያልተፃፈው የሞራል ህግ አካል ነው።

ምናልባት ወጣቱ ልጅ በእንደዚያ ዓይነት ቦታዎች ላይ ለአዛውንቱ ባይነሳላቸው አጠገቡ ያለው ከእርሱ የሚበልጥ ጎልማሳ ወጣቱን፤ ‘ተነስላቸው እንጂ!’ ሊለው ይችላል። አሊያም ራሱ ጎልማሳው በመነሳት ወጣቱን በሃፍረት እይታ ሊመለከተው ይችላል። ይህ ክስተት እውን ሲሆን በአካባቢው የነበረ ማንኛውም ኢትዮጵያዊም፤ ለአዛውንቱ ያልተነሳውን ወጣት፤ ‘ምን ዓይነት ባለጌ ያሳደገው ነው…?!’ የሚል ትችት ሊሰነዝርበት ይችላል—ፊት ለፊት ባይሆንም በውስጡ። ካልሆነም በግርምታ ‘ወይ የዘመኑ ልጅ…?!’ ብሎት ያልፈዋል። ወጣቱ ለአዛውንቱ ከተነሳም በዚያው ልክ በስፍራው ባሉት ሰዎች የጥሩ አስተዳደጉና የግብረ ገብነት ልዕልናው የዳበረ ለመሆኑ ምልክት የደርጎ ይወሰዳል። እናም በአዛውንቱም ይሁን በሌሎች ምርቃትና ጥሩ እይታ ይቸረዋል። ያም ሆነ ይህ ግን፤ ምሳሌው ኢትዮጵያዊያን ግብረ ገብነት ለጎደለው የማህበረሰቡ አባል ከበሬታን እንደማይቸሩና ኢ-ሞራላዊ እሳቤዎችን እንደማይቀበሉ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። እንዲያውም ከማህበራዊ መስተጋብሮቻቸው ውስጥ በሂደት እስከማግለል ሊደርሱ ይችላሉ። በዚህም ማህበረሰቡ ብስሉን ከጥሬው ይለያል።

ታላላቆችን ያለማክበር፣ መግደል፣ መዋሸት፣ መስረቅ፣ ማጭበርበር…ወዘተ. የመሳሰሉ ተግባሮች ከእኛ ሀገር ግብረ ገባዊ እሳቤዎች ወይም የሞራል እሴቶች አጥር ውጭ ናቸው። እንዳልኩት እንዲህ ዓይነት ተግባሮችን መፈፀም በማህበረሰቡ ውስጥ የሚኖርን ተቀባይነት በመንፈግ ዋጋ ያስከፍላል።

በሌላ በኩልም፤ የትኛውም ማህበረሰብ የሚመራበት ህግና ስርዓት አለው። ብዙውን ጊዜ ዴሞክራሲያዊ በሆኑ ሀገሮች እነዚህ ህጎች በህገ መንግስት አማካኝነት ሊገለፁ ይችላሉ። ህገ መንግስት የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ ነው። በመሆኑም ህገ መንግስትን የሚፃረሩ ማናቸውም ልማዳዊ አሰራሮችና ህጎች ተቀባይነት አይኖራቸውም። ወይም ውድቅና ፈራሽ ናቸው። ስለዚህ በእነዚህ ሀገር ውስጥ በህዝቦች ፈቃድ እውን የሚሆነው ህገ መንግስት፤ የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ ሆኖ ያስተዳድራል። የሚወጡ ህጎች ህገ መንግስቱን መሰረት አድርገው እንጂ፤ በተቃራኒ ጎን ቆመው ሊረቀቁ አይችሉም።

እናም በእነዚህ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች በማናቸውም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብሮቻቸው ውስጥ ህገ መንግስቱንና እርሱን ተከትለው የወጡ ህጎችን ማክበርና ማስከበር ይኖርባቸዋል። በየትኛውም ዓይነት የህይወት ግንኙነታቸው ውስጥ ህጎቹን ተላልፈው ከተገኙ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ቅጣት ይጣልባቸዋል። በኢትዮጵያ ውስጥም ዜጎች በስራ ላይ የሚገኘውን ህገ መንግስትና ሌሎች የሀገሪቱን ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች በቅድሚያ ራሳቸው አክብረው፣ ለጥቀውም ሌሎች እንዲያከብሩ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ይህ ተግባር የዜጎች የህግ የበላይነትን የማስከበር ሀገራዊ ኃላፊነትና ግዴታ ነው። ህግን ተላልፎ የሚገኝ ዜጋም በህጉ አግባብ መሰረት መቀጣቱ አይቀርም።

ዳሩ ግን በቅርቡ እዚህ ሀገር ውስጥ እየታዩ ያሉት ድርጊቶች፤ አንድም፣ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውና የሀገሬ ህዝቦች የሚያወግዟቸው ያልተፃፉት ማህበራዊ እሴቶች (ማለትም ግብረ ገባዊ አስተሳሰቦችና የሞራል እሴቶች) በጠራራ ፀሐይ ሲፈፀሙ፤ ሁለትም፣ በሀገራችን ውሰጥ በስራ ላይ የሚገኘው ህገ መንግስት እየተጣሰ የህግ የበላይነት ውሃ ሲቸለስበት እየተመለከትን ነው። በማህበረሰቡ በነውርነት የተፈረጁና ከሀገሪቱ ህጎች ጋር የሚቃረኑ ተግባሮችን በየትኛውም ቦታዎች መፈፀም አደገኛ አዝማማያ ነው። ለተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ የማይበጅ ከመሆኑም ሌላ፤ እንደ ሀገር እንዳንቀጥል ሊያደርገንም ይችላል።

በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ከኢትዮጵያዊ የሞራል እሴቶች ባፈነገጠ መልኩ የሚፈፀሙ ተግባሮች፤ ራስ ፖሊስ፣ ራስ ከሳሽና ራስ ፍርድ ሰጪ በመሆን በዜጎች ላይ የደቦ ፍርድ የመስጠት እዲሁም በፖለቲካ ፓርቲዎች ሽፋን ዘረፋና ስርቆት የመፈፀምና ከፍ ሲልም ኢትዮጵያዊ ጨዋነታችንና የህግ ዘውጎቻችን በማይፈቅዱት ሁኔታ ህገ ወጥነት እየተከናወነ ነው።

በእኔ እምነት፤ ከኢትዮጵያዊ የሞራል አስተሳሰብ መስፈሪያዎች አጥር ውጭ የሆኑት እንዲሁም መንግስትና ህዝቡ ተስማምተው ያፀደቁትን ህገ መንግስትንም ጭምር የሚፃረሩት እነዚህ አስነዋሪ ድርጊቶች፤ ፈፅሞ ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው።  እናም ሁሉም ዜጋ ድምፁን ከፍ አድርጎ ሊያወግዛቸውም ይገባል። ለህግ የበላይነት ልዕልና ዜጎች ሊጮሁ ይገባል። የህግ የበላይነት ፈፅሞ ለድርድር መቅረብ የለበትም። በዚህ ረገድ፤ “ዝምታ ወርቅ ነው” የሚለው ይትብሃል የሚሰራ አይመስለኝም። አዎ! በእኔ እምነት ወርቅ ሊሆን የሚችለው፤ የዜጎችን ሰላምና ፀጥታ ለሚያመጣው የህግ የበላይነት ዘብ መቆም ነው።             

ርግጥ የህግ የበላይነትን የሚያስከበሩና የሚያከብሩ መንግስታዊ ተቋማት አሉ። እነዚህ ተቋማት፤ በላቸው አቅም በየቦታው የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየተንቀሳቀሱ ነው። በዋነኛነትም የፀጥታና የፍትህ አካላቱ ተቀናጅተው እየሰሩ ነው። ውጤትም በማምጣት ላይ ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል፤ በኦሮሚያ ክልል በሻሸመኔ የደቦ ፍርድ የሰጡ ግለሰቦች እንዲሁም ንብረትና ሃብት ያወደሙ ተጠርጣሪ ዜጎች፣ በደቡብና በአማራ ክልሎችም በደቦ ፍርድ ሲሰጡ ነበር የተባሉና በዘረፋ ተግባር የተጠረጠሩ ግለሰቦች በህግ ጥላ ስር እንዲውሉ መደረጉንና ጉዳያቸውም በፍርድ ሂደት ላይ መሆኑን መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል።

እነዚህ አካላት የኢኮኖሚ ማጭበርበርን ለመከላከል የተለያዩ ርምጃዎችን ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን እየወሰዱ ነው። ለዚህም ይህን ፅሑፍ እያሰናዳሁ ባለሁበት ወቅት ባለው አንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ ባካሄዱት የቁጥጥር ስራ፤ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጣ የነበረ 46 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፣ ሶስት ሺህ ዩሮ፣ ሶስት ሺህ 500 የአረብ ኤሚሬቶች ድርሃም እና 54 ሺህ የኢትዮጵያ ብር መያዛቸውን በማሳያነት ማቅረብ ይቻላል። ምን ይህ ብቻ!— የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ 199 የቀበሌ ቤቶችን በመለየት ለችግረኞች ማስተላለፉንም መጥቀስ ይገባል።

እነዚህ ተግባሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ሰው ከህግ የበላይ እንደማይሆን ሽራፊ አስረጅዎች ናቸው። ተግባሮቹ በሀገራችን ህዝቦች በኢ-ሞራላዊ ድርጊቶች የሚቆጠሩትን እንዲሁም የህግ ተጠያቂነት የሚያስከትሉትን እንደ ሰው መግደል፣ ዘረፋና ማጭበርበር ዓይነት እንዲሁም የመረዳዳት ባህላችንንና የእኩል ተጠቃሚነትን መርህ የሚፃረሩ ድርጊቶችን መከወን ከተጠያቂነት እንደማያድን ገላጮችም ጭምር ናቸው። ርግጥም ተግባሮቹ ብስሉን ከጥሬው እየለዩ ነው። ወደፊትም ልየታው ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ያም ሆኖ በእኔ እምነት፤ ህብረተሰቡ በሁለት ምክንያቶች ህግንና የበላይነትን አክብሮ ማስከበር ያለበት ይመስለኛል። አንደኛው፤ ህግን በማክበር ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረውን የነፃነት መንገድ እየተጠናከተ ሄዶ ዳር እንዲደርስ ያግዛል። ሁለተኛው ደግሞ፤ የህግ የበላይነትን በመፃረር ህገ ወጥ ድርጊትን መፈፀም የሚያስከትለውን የስርዓት አልበኝነትን ህገ ወጥ ተግባር መንግስት ከእንግዲህ ሊታገስ የሚችል ስለማይመስለኝ ነው። ስለሆነም በእነዚህ ምክንያቶች ሳቢያ ዜጎች ህገ ወጥነትን መታገል እንዲሁም ሌሎች ተግባሩን ሲከውኑ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን ርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ርግጥ እዚህ ላይ የህግ የበላይነትን የማስከበር ተግባር ለመንግስታዊ ተቋማት ብቻ የሚተው አለመሆኑን ዜጎች መገንዘብ አለባቸው። ህዝብ በውስጡ የሚፈፀሙ ማናቸውንም ሰናይና እኩይ ተግባሮችን የእጆቹ ጣቶች ያህል ያውቃቸዋል። ህዝቡ የትኛው ግለሰብና ቡድን በማህበረሰቡ የተወገዙ ኢ-ሞራላዊ ተግባሮችን እንዲሁም ህገ ወጥ ድርጊቶችን እንደሚፈፅም አሳምሮ ያውቃል። የትኛው ህግ አክባሪ ሆኖ በሰናይ ምግባር ደቀ-መዝሙርነት እንደሚንቀሳቀስ እንዲሁም የትኛው የህግ የበላይነትን እየደፈጠጠ የእኩይ ምግባር ሃዋርያ ሆኖ የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ እንደሚያውክ ከህዝቡ የተሰወረ አይደለም። እናም የሰላምና የፀጥታው አለመኖር ሰለባ የሚሆነው ህዝቡ በመሆኑ ብስሉን ከጥሬው በመለየት የዜግነት ድርሻውን ሊጣ ይገባል እላለሁ።