“ፍትህ የማህበራዊ ተቋም የመጀመርያ ፀጋው ነው”

ባሳለፍናቸው አስር ዓመት ኢትዮጵያ ከዓለማችን ፈጣን ኢኮኖሚዎች በመጀመርያ ረድፍ የምትጠራ አገር ሆናለች። ይህ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትም ተጨባጭ፣ሊካዱ እማይችሉና እሰየው እሚያስብሉ ልማታዊና ማህበራዊ ለውጦችን አስከትሏል። በኢኮኖሚው መስክ አገራችን ኢትዮጵያም ገፅታዋን በፍጥነት እየቀየረች ትገኛለች። GTP 1 አስፍቶ ማሰብንና አግዝፎ መስራትን ያስተማረ እቅድ ስለነበር እያንዳንዱ ዜጋ ላይ የፈጠረው መነሳሳት እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም። በተለጠጠ እቅድ እና  እጅግ በጣም ብዙ  በማለም ብዙ መስራት ፣ በፐርሰንት ሲታይ ትንሽ ቢመስልም ትንሽ አቅዶ እስዋን ብቻ ከማሳካት ግን ሺህ እጥፍ ይሻላልም ይበጃልም። ስለዚህ ambitious ፕላን መሆኑ ሊደነቅ ይገባዋል። ከጀርባው ያለው እሳቤም ማደግ ካለብን ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ያስፈልገናል፤ይህን ለማድረግ ደግሞ ተለቅ ያለ ስራ መስራት አለብን ነው። ይሄም በጎ እሳቤ ነው። ትልቅ ነገር ሳያስቡ ትልቅ አገር መገንባት አይቻልም።  

 

አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት በማስፈንና ሰላም ላጡ ህዝቦች የሰላም ሃይል በመሆን እሚደረገው የዲፕሎማሲና የመከላከያ ሃይላችን ጥረትም እጅጉን እሚመሰገን ነው። ኢትዮጵያ ላይ የሰፈነው አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት ዝቅ ተደርጎ ሊታይ የሚችል አይደለም፤ እነ ሶርያና ሊቢያ ከነ ሙሉ ሃብታቸው ምን አይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉም መርሳት የለብንም። እነ ኬንያና ሶማልያ በአሸባሪዎች ሲታመሱ በሰላም ተኝተን እምናድረው የሰፈነውን አንፃራዊ ሰላም ተማምነን ነው። ዋናው የሰላማችን ምንጭ ህገ-መንግስታዊ ስርዓታችን ቢሆንም የፀጥታ ሀይሎቻችን ልዩ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ተስፋ ሰጪ በሆነው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ምክንያት የተፈጠረው አገራዊ የህዳሴ መንፈስም ከምንም ሳይሆን መሬት ላይ ካለው እውነታ የሚመንጭ አወንታዊ ቁጭት ስለሆነ ለለውጥ ጉዞው እጅግ ጠቃሚ ግብአት ነው። ይሁን እንጂ የኑሮ ውድነት እጅግ እያሻቀበ በመሄዱና በሃብታምና ድሃ መካከል ያለው ልዩነት በዚህ ፍጥነት ከቀጠለ አደገኛ ስለሆነ ተገቢ እርምት መወሰድ አለበት፡፡

 

GTP1 በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት እንዳይሳካ ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግር በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ከአጠቃላይ የዴሞክራሲ ድባብ መጥበብ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የመልካም አስተዳደር አለመኖር፣ የሙስና እና የፍትህ መበደል ናቸው የGTP 1ን አፈፃፀም በሚፈለገው ፍጥነት ያላስኬዱት። መልካም/ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ማስፈን ከተበላሸ/ ካልተቻለ GTP2 አይሳካም ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት አገራችን የሰራቻቸውን የሚያፈርስ፣ሰላማችንንና መረጋጋታችን እንድናጣ የሚያደርግ መሆኑን መገመት አይከብድም።

 

መልካም አስተዳደር የሚለው ንድፈ ሃሳብ አዲስ ያልሆነና ለተለያዩ ሰዎች የተለያየ ትርጉም የሚሰጥ ነገር ነው። እንደ ናንዳ (Nanda, 2006: 271) ገለፃ፤አስተዳደር የሚለው ሃሳብ የትርጉም እልባት ያላገኘና ትርጉሙም ልናሳካ በምንፈልገው አላማና በምንከተለው ዘይቤ የሚመሰረት ነው፡፡ አስተዳደር የነባራዊው ፖለቲካዊ ስርዓት ነፀብራቅ ሲሆን በመጠነ ስፋቱና ተዛማጅ ትርጉሙም ከግዜ ወደ ግዜ እንዲሁም ከቦታ ወደ ቦታ የሚለያይ ነገር ነው። በፍፁማዊ የዘውድ አገዛዝና ሌሎች የአምባገነን መንግስታት አስተዳደር ሊያሳካ እሚችለው የመጨረሻው አላማ የአስተዳደር ቢሮክራሲያዊ ገፅታው፤ ማለትም ውጤታማነትና ብቁነት (ቅልጥፍና) ነው።

 

ማህበረ -ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገቶችንና የዴሞክራሲ ጅማሬን ተከትሎ ግን አስተዳደር የሚለው ሃሳብ መልካም አስተዳደር ወይም ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚሉትን በማካተት መልካም አስተዳደርን የዴሞክራሲ ፀጋ አድርጎ መቁጠር የተዘወተረ ነገር መሆን መጀመሩን መገንዘብ ይቻላል። መልካም አስተዳደር ወይም ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ከውጤታማነትና ብቁነት የሰፋና የገዘፈ ሃሳብ ሲሆን፤ ላጠቃላይ የፖለቲካ ስርዓቱ የሚቆምና የዜጎችን ፖለቲካዊና ሰብአዊ መብቶች እንዲሁም ነፃነቶች የሚያስከብርና ማንኛውንም ዓይነት አድልዎ የማይቀበል ሂደት ነው። ግልፅነትና ተጠያቂነትም በሲቪል ሰርቪሱ ብቻ የማይታጠር በፖለቲካ አመራሩና ተቋማት ሊተገበር እሚገባው ቁልፍ የመልካም አስተዳደር አካሎች ናቸው።ይህ ምልከታ ደግሞ አዲሱን የለውጥ አመራር የሚገዛ ሃሳብ እንደሆነ በጠቅላያችን በኩል በተደጋጋሚ ተሰምሮበታል።

 

ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የህዝባዊ ተቋማት ግልፀኝነትና ተጠያቂነት ይፈልጋል። ዜጎችም ስለ መንግስት ፖሊሲ፣ ውሳኔዎችና ተግባራት መረጃ የማግኘት መብት ሊኖራቸው ይገባል። እስከዛሬ በነበረው በእኛ አገር ሁኔታ ይህ እንዳይሆን እንቅፋት ከሆነው አንዱ የመንግስት የመረጃ አያያዝ ደካማነት፣ የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት እንዳላቸው አለመገንዘብና በዋናነት ደግሞ ሚስጢራዊና ሚስጢራዊ ያልሆኑ መረጃዎችን መለየት አለመቻል መሆኑ ላይ ብዙዎቹ የዘርፉ ጠበብቶች ያለልዩነት ይስማማሉ።

 

ይህ ሁኔታ ካልታረመ መሰረታዊ የዜጎች መረጃ የማግኘትን መብት ስለሚጋፋ ለዴሞክራሲ ምህዳር መጥበብ የራሱን አስተዋፅኦ ማድረጉ አይቀርም። ስለሆነም አዲሱ የለውጥ አመራር ጉዳዩ ላይ ማስመሩ ተገቢነት ይኖረዋል። አዳምስ  በሃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ለድርጊታቸውና ላፈፃፀም ግብራቸው ተጠያቂ መሆን አለባቸው ይላል። ጠቅላያችን ደጋፊ እና ተቆጣጣሪ የሆነውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአስፈጻሚው አካል ጋር የኮንትራት ውል የማስገባታቸው ምክንያትም ይህ ነው። የተጠያቂነትና ግልፀኝነት መርህ መንግስት አካባቢ የሚኖረውን ሙስና ለመግታትና የዜጎችን ተሳትፎ ለማበርታት ጠቃሚ ነገሮች ናቸው ይለናል የዘርፉ ሊቅ አዳምስ።

 

ዜጎች ሃሳብንና ራስን በነፃ የመግለፅ፣ የመደራጀት እንዲሁም ማንንም ሳይፈሩ ድርጅት የመመስረትና የተመቻቸውን ድርጅት የመቀላቀል መብት ሊኖራቸው እንደሚገባ ከሚያትትልን የአዳምስ ጥናት መረዳት የሚቻለው መልካም/ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሲባል ቁንፅል ፖለቲካዊ ሃሳብ ሳይሆን የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በአስተዳደር መዋቅርና ትግበራ ከግምት ማስገባት ማለት እንደሆነ ነው።

  

አዳምስን ጨምሮ በርካቶቹ የዘርፉ ጠበብቶችም ሆኑ በዘርፉ ላይ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መልካም አስተዳደር ስምንት ዋና ባህርያት እንዳሉት ይገልጻሉ። እነዚህም አሳታፊነት፣ መግባባት ላይ ያተኮረ (Concensus oriented) ፣ ተጠያቂነት፣ ግልፅነት፣ መልስ ሰጪ (Responsive)፣ ውጤታማና ብቁ (ቅልጥፍና)፣ፍትሃዊና ሁሉን አቃፊ (equitable and inclusive) እንዲሁም የህግ የበላይነት ናቸው ። መልካም አስተዳደር የህዳጣን (Minorities) እና የሌሎች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ሃሳብና ድምፅ በውሳኔ መስጠት ሂደት ላይ ግምት ውስጥ መክተትንም ይጨምራል። አሁን ላለውና ወደፊት ለሚመጣው ማህበረሰባዊ ፍላጎትም ጭምር ዝግጁ የሆነና መልስ መስጠት የሚችል አቅምና መዋቅር መፍጠር ነው መልካም አስተዳደር። ስለዚህ አሁን በጎ ጅምሮችን እያሳየን ያለውን የለውጥ ሃይል ልንደግፍም ሆነ ልንቃወምና ልንተች ከተገባና  ምክንያታዊ የሚያደርገን ከእነዚህ መለኪያዎች አንፃር ስንነሳ ነው።  

 

ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ስርዓት መንግስታዊ ስልጣን የያዙ ሰዎች ላይ ህጋዊ ገድብ ያስቀምጣል። ስልጣን ለተለያዩ የመንግስት አካላት የሚሰጥበት ምክንያትም በተወሰኑ ተቋማት ወይም ግለሰቦች ብቻ ሃይል እንዳይከማች ከሚል እሳቤ ነው። የተለያዩ የመንግስት አካላት በቂ የሆነ አቅምና ነፃነት ኖሯቸው አንዱ መዋቅር ሌላኛውን እሚቆጣጠርበትና ህገ መንግስታዊ ሚዛን የሚጠብቅበት አሰራር ያስፈልገዋል።  

 

ለአዲሱ የለውጥ አመራር መንስኤ ከሆኑት ጉዳዮች መካከልም በስርአቱ ስም የነበረው አስፈጻሚ እና ህግ አውጪ እንዲሁም ተርጓሚው ከመርህም ሆነ ከህግ ማፈንገጣቸው መሆኑ አያከራክርም። ይህም መልካም አስተዳደር ማረጋገጥ ባለመቻላቸው፣ ሙስና እና የፍትህ እጦት የስርዓቱ በሽታዎች የነበሩ በመሆናቸው ይገለጻል፡፡ እነዚህ በሽታዎች አጠቃላይ የዲሞክራሲ ሁናቴው ሲቀጭጭ ከቁጥጥር ውጪ የመሆን እድላቸው እንዲሰፋ በማድረግ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ እንኳ አዳጋች ሆኖባቸው በተጨባጭ አይተናል፡፡ ችግሮቹ አብረውን የነበሩና አሁንም እያኗኗሩን ያሉ በሽታዎች ናቸው፡፡  

 

አሁን ኢትዮጵያ ላይ ያለው የዴሞክራሲ ድባብ ሲታይ ዜጎች የሚሰማቸውን ቅሬታ ለመግለጽ አብዛኞቹ መንገዶች መከፈታቸውን ተመልክተናል፤ ስለሆነም አጠቃቀማችን ወሳኝ ይሆናል ማለት ነው። ከሞላ ጎደል መንግስትና ገዥው ፓርቲ ችግሮቻቸውን አራግፈው ለህዝብና በየደረጃው ለሚገኙ ባለድርሻ አካላቶች ሰጥተዋልና ነው አጠቃቀማችንን ወሳኝ የሚያደርገው። ስናወራላቸው የነበሩ አማራጭ የመረጃ ምንጮች እስከመሪዎቻቸው በከፍተኛ ፍጥነት ከውስጥም ከውጭም አደባባይ ወጥተዋል። የማህበራት ነፃነት የሚከበርበት ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑንም ታዝበናል። የመናገርና ባጠቃላይ ሃሳብን የመግለጽ መብቶች በሚታዩና በማይታዩ ዘዴዎች እየጎለበቱ መጥተዋል፡፡ መልካም አስተዳደር ህልም የሆነበት፣ ሙስና የያንዳንዱ መንግስታዊ መዋቅርና ሰዎች “ልሙድ ተግባር” የሆነበት፣ ፍትህ ከርትዕ ርቆ የጉልበተኞች መጫወቻ እየሆነ ባጠቃላይ ዜጎች በፍርሃት የተሸበቡበት ፖለቲካዊ ሁኔታ ነው አሁን ስለመለወጡ እነዚህ በቂ ማሳያዎች ይሆናሉ፡፡

 

አካፋን አካፋ ማለት ተጀምሯል። ውሸት ሃይል አግኝቶ እውነትን የመተካት አቅሙ የማሸሸበት ስርአት መፈጠሩን የሚያጠይቁ በርካታ ሁነቶችን ታዝበናል፡፡   ህዝባዊነት በግለኝነት የሚሸራረፍበት የእድል በር ሁሉ ተጠርቅሟል፡፡ ህዝብ የበላይ ወሳኝና ተቆጣጣሪ መሆኑ ተረጋግጧል። የግል ጥቅምና ምቾትን ለማሳካት መንቀሳቀስ በኢህአዴግ ውስጥ አፈር ድሜ የሚበላባቸው ማእቀፎች ተነድፈዋል፡፡

  

ህዝብን የሚሰማ እየጠፋ ‘እኔ አውቅልሃለሁ’ ባይ እየበዛ፣ ህዝቡ ችግሩን ሲናገር ከተቃዋሚዎች ጋር እያስተሳሰሩ የማሳደድ ዘመን አብቅቷል። እንደ ፓርላማ የመሳሰሉ የዴሞክራሲ ተቋማት ግዴታዎችን በበቂ ሁኔታ የሚወጡባቸው አሰራሮች ተቀንብበዋል። የስራ አስፈፃሚውን ጡንቻ የሚያስተነፍስ ማእቀፍም ተዘጋጅቷል።  

ለበሽታዎቻችን እንደ የአቅም ማነስ፣ ድርጅታዊ ድክመት፣ ያልዳበረ ህዝባዊ የተሳትፎ ባህል የመሳሰሉት ነገሮች  በምክንያትነት የሚጠቀሱበት እድል ጠቧል። የችግሩ ሁሉ መነሻና መድረሻ አጠቃላይ የዴሞክራሲያዊ ሁናቴ እጥረት ነው የሚለው ምልከታ ዛሬ በአዲሱ አመራር ተገቢውን ስፍራ ይዟል፡፡

 

ግን ደግሞ ይህን አዲስ የለውጥ ሂደት ስናግዝ ከላይ ከተመለከቱት መርሆዎች ማጠየቂያነት ባሻገር እንከን የለሽ ዴሞክራሲ እሚባል ነገር እንደሌለና ኢትዮጵያችንም ጀማሪ ዴሞክራሲ መሆንዋንም ግምት ውስጥ ማስገባት ተገቢ ይሆናል፡፡ አልያ ለቀልባሾች መመቻቸት ይመጣል።

 

ስለዚህም ስለ አገራችን የዴሞክራሲ ሁኔታ ስናወራ ስለ ሂደት እንጂ ህልመኛ በሆነ ጀብደኝነት፤ መሆን የማይችለውንና እስከ አሁን አለም ላይ የሌለውን ገነት መሳይ ዴሞክራሲ በመሻት ሊሆን አይገባም። በሃገራችን  ሁኔታ ተደጋግሞ እንደተገለጸው፤ ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ እየተንገራገጨ ቢሆንም ሁል ግዜ ወደፊት መጓዙን ማረጋገጥ ይኖርብናል እንጂ አጠቃላይ ቅልበሳ አገሪቱን ወደ አደገኛ ቀውስ ይመራታል፡፡ ዴሞክራታይዜሽንና ኢ-ዴሞክራታይዜሽን ሂደቶች ሁሌም መሳሳብና ውጥረት ይኖራል። መንግስት እንደ መንግስት ግን የዴሞክራታይዜሽን አጋዥ አልያም የኢ-ዴሞክራታይዜሽን አሳላጭ ነው መሆን የሚችለው፤ መሀል ላይ የሚንገዋለል መንግስታዊና ተቋማዊ አቋም ሊኖር አይችልም። ስለዚህ ምርጫው አንድና አንድ ነው፤ ለዴሞክራሲ መስራት ወይም የፀረ ዴሞክራሲ ሃይል መሆን። ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩ በጠበበ ቁጥር የዜጎች ተስፋ እየተሟጠጠ ስጋታቸውና ፍርሃታቸው እየጨመረ ከቁጥጥር ውጪ የመሆኑ እድል ይሰፋል፡፡አሁን ይህ እድል ነው የተዘጋው። ምክንያቱም ይህን መሰል ሁኔታም ከውስጥም ከውጪም ሊነሱ ለሚችሉ ፅንፈኛ ሃይሎች ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር አገሪቷን ወደ አላስፈላጊ መንገድ ሊመራ የሚችል መሆኑ በአዲሱ አመራር የማይናወጽ አቋም ተይዟልና፡፡ ፍትህ ተራ ፍርድ የማግኘት ጉዳይ እንዳልሆነ አሁን ተረጋግጧል፡፡ ፍትህ የማህበራዊ ተቋም የመጀመርያ ፀጋው ነው የሚለው የጆን ራውልስ ምልከታ የአዲሱ አመራርም የስራ እና የአሰራር ፍልስፍና ሆኗል፡፡ ሙስናና መልካም ያልሆነ አስተዳደርም ሃገርን ሊበትኑ የሚችሉ፤ እየታየ ያለውን ኢኮኖሚያዊ እድገት ገደል የመክተት አቅም ያላቸው ስርዓታዊ በሽታዎች ስለመሆናቸው ባለፉት ሶስት የቀውስ አመታት በሚገባ አይተናልና ይህን ታሳቢ ያደረገ ድጋፍና ተሳትፎ ከያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡