ሠላም “ለክብርኪ”!

የሀገር ሠላም የሰው ልጅ በሕይወት ዘመኑ የሚኖረውም ታላቅ ፀጋና ሀብት ነው፡፡ የሠላምን ታላቅነት ለመግለጽ ቃላቶች ሁሉ አቅም ያንሳቸዋል፡፡ የቤተሰብም ሆነ የግል ሕይወት፣ የእምነት አምልኮት ነፃነት፣ የሀገር ልማት እድገት ስልጣኔ ከሰላም ውጭ አይታሰብም፡፡ ሠላም ከሌለ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውድድርም ሆነ ፉክክር አይኖርም፡፡ የሰላም እጦትና መደፍረስ ሥርዓተ አልበኝትን የሚያሰፍን በመሆኑ የህዝብ መሠረታዊ ፍላጎትና  ሕይወት የሆነው ሰላም ይታወካል፣ይደፈርሳል፡፡ በሰላም ከቤት ወጥቶ በሰላም መመለስ አይቻልም፡፡ ሰላም ለክብርኪ ያልኩትም ለዚህ ነው፡፡ ሠላም ሲኖር ሁሉም ያከብሩናል፣ ያደምጡናል፤ በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳጅ፣ ተመራጭና ተደማጭ መሆን ያስችለናል።

ሠላም ከሌለ ወጣቶች ትምህርታቸውን መማር፤ ሠራተኛውም መደበኛ ሥራውን መከወን  አይችልም፡፡ ነጋዴውም የቱንም ያህል ሀብትና ወረት ቢኖረው ያንን አውጥቶ ለሕዝብ ማቅረብም ሆነ መሸጥ አይሞከርም፡፡ሰላም  ከሌለ ነገን የተሻለ ሕይወት እናደርጋለን ተምረን ትልቅ ደረጃ እንደርሳለን የሚለው የሰዎች ሕልምና ተስፋ አብሮ ይጨልማል፡፡ በሰላም መዘዋወር ተንቀሳቅሶ መሥራት መነገድ መማር ሰላማዊ የቤተሰብ ሕይወት መኖር ሌሎችም ነገሮች ሁሉ አይኖሩም፡፡የሰላም ለሀገርና ለህዝብም ዋነኛው የማዕዘን ደንጋይ ነው፡፡

የሀገራችንን ሰላም የምንጠብቀው ለማንም ብለን አይደለም፤ለራሳችን ስንል ነው፡፡ በሀገር ሰላምና ደኅንነት ጉዳይ መደራደር አይቻልም፡፡የሀገር ሰላምና ደኅንነት የሚከበረው የሕግ የበላይነት በአግባቡ መኖርና መከበር ሲችል ብቻ ነው፡፡የሕግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሥራ አይደለም፡፡ዜጎች ከዚህ የተሳሳተ ግንዛቤ መውጣት አለባቸው፡፡መንግሥት ሕግና ሥርአትን የዜጎችን ሰላምና ደኅንነንት የመጠበቅ መንግሥታዊ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም በዋነኛነት ሰላሙን መጠበቅና ማስጠበቅ ያለበት ሕዝቡ ነው፡፡

የመንግሥት የፀጥታ አስከባሪ አካላት መከላከያውም ሆነ ፖሊሱ የተውጣጡት ከህዝቡ ነው፡፡ለዚህ ነው ሕዝቡ በሚኖርበት አካባቢ ሁሉ ተባብሮ የአካባቢውን ሰላም ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ሆኖ ማስከበር ያለበት፡፡ በሰላም እጦት እና መደፍረስ የበለጠ ተጎጂዎች የሰው ልጆች ናቸው፡፡ በአለፉት ግዜያት ያስተዋልነውም እውነት ይሄንኑ ነው፡፡

የሰላም እጦት የመንገዶች መዘጋት የሸቀጥና የተለያዩ መሠረታዊ የምርት አቅርቦቶች ከገጠር ወደ ከተማ እንዳይገቡ ያደርጋል፡፡ገንዘቡ ቢኖርም የምግብ እህሎችን ማግኘትና መሸመት የማይቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡የተወሰኑ ቢገኙም ዋጋቸው ይንራል፡፡በዚህም መሀል ነጋዴው እንደተለመደው አጋጣሚውን በመጠቀም የምርትና የሸቀጥ እጥረት ተፈጠረ በሚል ያለውን ለገበያ ከማቅረብ ይልቅ የበለጠ ዋጋ ያስገኝልኛል በሚል ይደብቃል፡፡በዚህ መልኩ ሕዝብ ቤተሰቡ ሕጻናት ጭምር ምን ያህል ተጎጂ ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት አይከብድም፡፡ሰላም ሲኖርና ፀጥታ ሲከበር እነዚህ ችግሮች አይኖሩም፡፡ለዚህ ነው የሰላም ዋጋ በዓለማችን እጅግ ውድ ነው የሚባለው፡፡

ሁሉም ሰው ለሰላም መከበር መቆም ያለበትም ከብዙ መነሻ ምክንያቶች ነው፡፡ሰላም ከሌለ ሕግና ሥርዓት ካልተከበረ ሥርአተ አልበኝነት ከሰፈነ የዜጎች ሕይወት አደጋ በሌለው ዋስትና ውስጥ  ይወድቃል፡፡ይህ ዓይነቱ ሁኔታ እንዳይፈጠር ዜጎች በያሉበት አካባቢ ሰላማቸውን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ነቅተው ሊንቀሳቀሱ ይገባል፡፡ሕገወጦችን በመያዝ  ከአቅማቸው በላይ ከሆነም ለሕግ አስከባሪ አካላት በመጠቆም ሁኔታውን መቆጣጠር ይችላሉ፡፡የጋራ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ የውዴታ ግዴታ ኃላፊነት በመላው ሀገሪቱ ለሚኖሩ  ዜጎች ሁሉ ቀዳሚ ተግባር ነው፡፡

ፖሊስ ወይንም ወታደር ብቻ ነው ሰላም የሚያስከብረው የሚለው የተሳሳተ አመለካከት በዚህ ዘመን አይሠራም፡፡መደበኛ ሠራዊትና ፖሊስ በሀገራችን ባልነበረበት ዘመን አካባቢውን ሆነ ሀገሩን አስጠብቆ የኖረው ሕዝቡ ነው፡፡በያለበት አካባቢ በመደራጀት በመሰባሰብ አለቃና ምንዝር በመምረጥ ጥፋተኛና ወንጀለኞችን በማጋለጥና አድኖ በመያዝ  ለሕግ በማቅረብ ተከብሮና ሰላሙን አስከብሮ ኖሯል፡፡

ወጣት ወንድና ሴቶች፣ ሽማግሌዎችና እናቶች ምሁራን፣ የሀይማኖት አባቶች በአጠቃላይ ኅብረተሰቡ የራሱን ሰላም የማስከበር ታላቅ ግዴታና ኃላፊነት አለበት፡፡ይህንን ለማድረግ አለመቻል የሚያስከፍለው ዋጋ ከፍተኛ ነው፡፡ዘረፋ ወንጀል በአደባባይ ንጥቂያ በቡድን ተደራጅተው መዝረፍ፤የመኪና ስርቆት፤ በተደራጀ ሁኔታ የተሰረቁ መኪኖችን በመጠቀም የሚፈጸሙ የከፉ አደገኛ ወንጀሎች የበለጠ የሚጎዱት ሕዝቡን ነው፡፡ሊበራከቱም ይችላሉ፡፡ወንጀል ፈጻሚዎቹ የሚኖሩት በኅብረተሰቡ ጉያ ውስጥ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ በየቀበሌው በየመንደሩ ነቅሶና ለይቶ ካወጣቸውና ለሕግ እንዲቀርቡ ካደረገ የወንጀል ድርጊቱን መከላከል ሕግና ሥርዓትን ማስከበር ይችላል፡፡መፍትሄውም ይሄ ብቻ ነው፡፡

ለአንዲት ሀገር ሕልውና ቀጣይ ዕድገትና ለውጥ ከሰላም በፊት የሚያስፈልጋት ነገር የለም፡፡ የሕግ የበላይነትን መከበር ወሳኝ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡የሀገር ሰላም የቤተሰብ ሰላም የጎረቤት ሰላም የመንደሩና የአካባቢው ሰላም የወረዳው አውራጃው የክልሉ ብሎም የሀገር አጠቃላይ ሰላም ነው፡፡እያንዳንዱ በያለበት በሚኖርበት በሚሠራበት ስፍራ ሰላሙን ሲጠብቅ ነው ሰላም መከበር የሚችለው፡፡ ሀገራዊ ሠላምም የሚሰፍነው፡፡

ቀደም ሲል ሆን ተብሎ ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት ሥራ ተሰማርተው በሀገራዊ ሰላምና በኅብረተሰቡ ህይወት ውስጥም መፈናቀል ሞትና ስደት እንዲሰፍን አድርገው የነበሩ  ግለሰቦች ከራሱ ከኅብረተሰቡ በሚደርሱ ተጨባጭ ጥቆማዎች መሠረት ከያሉበት እየተያዙ ለሕግና ፍትህ እንዲቀርቡ በመደረግ ላይ ነው፡፡በአሁን ሰአት ሕግና ሥርዓትን የሕግ የበላይነትን የማስከበሩ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡የሕዝብና የሀገር ሰላምን በማወክና በማደፍረስ ተጠቃሚ እንሆናለን ብለው የሚያስቡ ክፍሎች ሴራው እየመከነ መሆኑን በዐይናቸው እየታዘቡ ነው፡፡ ሕዝብ ሀገሩን ወዶ ሰላሙን ያስከብራል፡፡

ግጭቶች ሆን ተብለው ተቀስቅሰውባቸው በነበሩ አንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች በተለይም በኢትዮጵያ ሶማሌ፤ በኦሮሚያና በደቡብ ግጭቶችን አልፈው በማስፋፋትና በመቀስቀስ  በማቀጣጠል ቀንደኛ ተዋናይና ተሳታፊ የነበሩ አመራሮችና ግለሰቦች በሙሉ በቁጥጥር ሥር ውለው ለሕግ እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡ይህ በመንግሥት በኩል እየተወሰደ ያለ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ወንጀል ፈጽሞ ሕዝብን አደጋ ላይ ጥሎ ማንም ከሕግና ከተጠያቂነት ማምለጥ አይችልም፡፡ የሕግ እርምጃዎች የሚወሰዱት ተከሳሾች ባጠፉት ክብደት መጠን ሲሆን ይህም በየደረጃው ለሕዝብ የሚገለጽ ነው የሚሆነው፡፡  ሕዝብ እያጋለጣቸው ለሕግና ፍትህ አካላት አሳልፎ እየሰጣቸው ያለው የሰላም መደፍረስን የማይቀበልና በፈጠሩትም ችግር ተጎጂ የሆነው ነው፡፡

እነዚህ ኃይሎች በሰላም አደፍራሽነት ተግባር ውስጥ ተሰማርተው በቆሰቆሱት ግጭት   ሳቢያ ከመኖሪያ ቀኤያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖቻችንን ወደቀድሞ መኖሪያቸው የመመለሱ ሥራ ተጀምሮ በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡ወደ ቀድሞው ቀኤያቸው  የተመለሱት ዜጎች በግልጽ በሕዝቦች መካከል አንዳችም ግጭት አለመኖሩን፤ የተፈጸሙት ተግባራት የትኛውንም ብሔር እንደማይወክሉ በቀጣይም ለሠላማቸው ጠንክረው እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል፡፡  

የሀገራችንን ሠላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሲባል  ጫካ ገብተው የነበሩ ታጣቂ ኃይሎች በሠላማዊ መንገድ ለመታገል ወደሀገር ውስጥ እየገቡ ይገኛሉ፡፡በዚህ ታሪካዊ ወቅት  በየአካባቢው ብልጭ ድርግም የሚሉ ግጭቶች ከጀርባቸው ገፊ ኃይል እንዳላቸው መንግሥትና ሕዝብ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ሰላሙን ነቅቶ መጠበቅና ሰላምን የሚያደፈርሱ አካላትን ማጋለጥና መከላከል ለሕግም እንዲቀርቡ ማድረግ የለውጡን ሂደት ለማስቀጠል ወሳኝ እርምጃ ነው ፡፡

በሀገራችን የተጀመረውን ለውጥ ከግብ ለማድረስ መንግሥት የኅብረተሰቡን ጥያቄዎች ከልብ በማድመጥ በብዙ መልኩ ወሳኝ የሆኑ ርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡ቀደም ብለው የወጡ በሕዝቡ ቅሬታ የቀረበባቸውን የተለያዩ ሕጎችና አዋጆችን ለማሻሻል በባለሙያዎች እየተደረጉ ያሉ ጥናቶችና ውይይቶች ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በመነጋገር በመደማመጥ መፍታት እንደሚቻል ተጨባጭ ማሳያዎች ሀገራዊ ሠላምን ከሕብረተሰቡ ጋር በመሆን የመጠበቅ ዋነኛው ኃላፊነት የወጣቱ ነው፡፡ የለውጥ እንቀሳቃሹ ዋነኛ ሞተር ወጣቱ እንደመሆኑ መጠን ለውጡ ከግብ እንዲደርስና የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ነቅቶ ሰላሙን መጠበቅ ያለበትም ወጣቱ ነው፡፡ የታገለለትን ዓላማ ከዳር ማድረስ የሚችለው በምክንያታዊነት አስተሳሰብ እየተመራ የበኩሉን ሀገራዊ ኃላፊነትና ድርሻ ሲወጣ ነው፡፡በስሜታዊነት ሊነዳና ሊጎርፍ አይገባም፡፡ ሀገራችን ከመቸውም ግዜ በላይ የሚያስፈልጋት በምክንያት ላይ ተመስርቶ የሚቃወምና የሚደግፍ  ከስሜታዊነትና ከግብታዊነት የራቀና የፀዳ ወጣት ነው፡፡ለሀገር ሰላምና ዕድገት ያለው ሚናም የገዘፈ ነው፡፡