የዲፕሎማሲው ስኬት

ሀገራችን በዲፕሎማሲው መስክ በቅርቡ ግዙፍ እርምጃዎችን ተራምዳለች፡፡ አህጉራዊና አለም አቀፍ ግንኙነቷ የበለጠ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ቀድሞም የነበረው ተሰሚነቷ የበለጠ እየጨመረ እየጎላ የመጣበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኃላ በአካባቢው ሀገራት የጀመሩት ግንኙነት ሶማሊያ፤ ጅቡቲ፤ ኬንያ፤ ኡጋንዳን ከዚም አልፎ ሳኡዲ አረቢያን፣ግብጽን፣አረብ ኢምሬትን፣ኤርትራን በኦፊሴል በመጎብኝታቸው አንድም ከሀገራቱ ጋር የነበረንን የነበረውን የቆየ ዲፕሎማቲክ ግንኙነት ያጠናከረና ያጎለበተ በሌላም መልኩ በሁለትዮሽ የጋራ ግንኙነት ላይ የቀደመውን  ግንኙት ወደ ላቀ ምእራፍ ያሸጋገረ ነው፡፡

በየሀገራቱ መካከል የተደረገው  ግንኙነት በበርካታ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት ለሀገራችን በሚጠቅም መልኩ ፈርጀ ብዙ ስምምነቶች የተደረሱበት ነው፡፡ይህም በሀገር ደረጃ ያለንን የዲፕሎማሲ ብቃትና ደረጃ አሳድጎታል፡፡ ኢትዮጵያ ከበርካታ የአለም ሀገራት ጋር የቆየና የኖረ ዲፕሎማቲክ ግንኙነት ያላት ሀገር ነች፡፡ የኖረውን ወዳጅነት ጠብቀን ዛሬ ደግሞ ለበለጠ ዲፕሎማሲያዊ አለም አቀፍ ትስስር እየተሰራ ያለበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡

በቅርቡ ቤጂንግ በተካሄደው የቻይና አፍሪካ የትብብር መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያ ልኡካንን በመምራት በስፍራው በመገኘት ተሳትፈዋል፡፡ቻይና ከኢትዮጵያ አጋሮችና ወዳጆች ውስጥ በኢንቨስትመንት ረገድ ቁጥር አንድ ድጋፍ የምታደርግ ሀገር ናት፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ግዙፍ የመሰረተ ልማት ለውጦችን በማምጣት ረገድ የቻይና አስተዋጽኦ የላቀ ነው፡፡ ይሄው የዲፕሎማቲክ ግንኙነትና የኢኮኖሚና የኢንቨስትመንት ትብብር ወደፊትም የበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ቻይና ለአፍሪካ ሀገራት በኢኮኖሚ በልማት በኢንቨስትመንት በቴክኒዮሎጂ ሽግግር ረገድ የምታደርገው ድጋፍና ትብብር አህጉሪቷን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድጋት ይታመናል፡፡ የቻይና እገዛና ፈርጀ ብዙ ትብብር  ለአህጉሪቱ ያለው ፋይዳ  የጎላ ነው፡፡የአፍሪካ ሀገራት ችግር  የተፈጥሮ ሀብት ችግር አይደለም፡፡አፍሪካ ግዙፍና ከአለማችን ውስጥ ያልተነካ ለብዙ ተግባራት የሚውል የተፈጥሮ ሀብት ያላት አህጉር ነች፡፡ አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች አፍሪካ ላይ ሲረባረቡ የነበረበትም አንዱና ትልቁ ምስጢር ይሄው ነው፡፡ የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብት ለማጋዝና ለመመዝበር፡፡  

ዛሬም ቢሆን ይሄን ህልማቸውን በሌላ መልኩ ለማሳካት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡አፍሪካ የወርቅ፣የአልማዝ፣የፖታሺየም፣የአልሙኒየም፣ የኮፐር፣ የኡራኒየም፣ የታንታለም፣ የሜርኩሪ ፣የተፈጥሮ ነዳጅ ሀብትና ሌሎችም የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት የሆነች አህጉር ነች፡፡

የአፍሪካ ወጣት ትውልዷ በቂ የተፈጥሮ ሀብት እያለው በዘመኑ እውቀት ሳይንስና ምርምር የገፋ ባለመሆኑ ሊጠቀምበት ባለመቻሉ እውቀቱ ያላቸው ምሁራን በሀገራቸው ሁነው ከመስራትና  ሕዝባቸውን ከማገልገል ከመለወጥ ይልቅ የተሻለ ክፍያና ኑሮ ፍለጋ በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች በብዛት ወደ ስደት የሚጎርፉበት ሁኔታ ለበርካታ አስርት አመታት አህጉሪትዋ በእድገት የአለም ጭራ እንድትሆን አድርጓታል፡፡

የአፍሪካ ምሁራን በገፍ እየተሰደዱ በከፍተኛ ክፍያ የሚያገለግሉት ያደጉና የበለጸጉ ሀገራትን ነው፡፡ ወደ ሀገሮቻቸው ተመልሰው ቢሰሩ በአጭር ግዜያት አህጉርዋን የመለወጥ አቅም አላቸው፡፡ ቻይና በጋራ መድረኩ ላይ ለአፍሪካ ሀገራት የመደበችው 60 ቢሊዮን ዶላር በአግባቡ ከተሰራበት የአፍሪካ ሀገራትን መሰረተ ልማት በከፍተኛ ደረጃ ሊለውጥ ይችላል፡፡ በዚህ ላይ የአህጉሪቱ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በቴክኒዮሎጂና በዘመናዊ እውቀትና ምርምር ታግዞ በአፍሪካውያን ከተሰራበት እያላት እንደሌላት በድህነት የምትጠቀሰውን አህጉር ወደላቀ ደረጃ  ያሸጋግራታል፡፡

የቻይና አፍሪካ መድረክ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዚሁ የቻይና አፍሪካ መድረክ ከቻይና ፕሬዚደንትና ከከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል ስላለው ጥብቅ ወዳጅነት በተለይም በኢንቨስትመንት ረገድ ስላለው ግንኙነትና በሌሎችም የጋርዮሽ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነትና ግንኙነት ከዚህ ቀደም ከነበረውም በላይ እንደሚያድግ ይጠበቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በዚሁ ስብሰባ ላይ ከተሳተፉት የአፍሪካ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡ በዲፕሎማሲው ረገድ በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን ከሌሎች ግዜያት በተሻለ ከአፍሪካም ሆነ ከአለም ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በማስፋት ላይ ትገኛለች፡፡ በተለይ ምእራባውያን መንግስታት በአጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት ባካሄደው ስርነቀል ሪፎርም መነሻነት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያን በብዙ መልኩ ለመርዳት ለማገዝ ቃል ከመግባታቸውም በላይ ለልማትና ለተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚውል ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ የሀገራዊ ዲፕሎማሲያዊ ስኬታችን ዋነኛው መገለጫ ነው፡፡

ከዚህ በፊት በተለያዩ ምክንያቶች ከሰብአዊ መብት አያያዝና ረገጣ ጋር በተያያዘ ለሀገራችን ያደርጉት የነበረውን ድጋፍና የገንዘብ እርዳታ አቁመው ወይም አግደው የነበሩ መንግስታት ዛሬ እየለቀቁ ይገኛሉ፡፡ ይህም የዲፕሎማሲው ውጤትና ስኬት ነው፡፡  

የበርካታ ሀገራት ልዑካን ቡድኖች ግዙፍ አህጉራዊና አለም አቀፍ ተቋማት አዲስ ከተደረገው ለውጥ ወዲህ ቀድሞ አድሮባቸው ከነበረው “ሀገሪቷ አደጋ ላይ ነች ሰላምና መረጋጋት የለም” ከሚለው ፍርሀታቸው ተላቀው ኢትዮጵያን ለማገዝ ለመርዳት ከፍተኛ ተነሳሽነት በማሳየት ላይ  ያሉ ሲሆን በዚህም መሰረት ሀገራችንን በተደጋጋሚ በመጎብኘት ላይ ይገኛሉ፡፡

ሀገራችን ካስመዘገበችው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትና የመሰረተ ልማት መስፋፋት ጋር ተያይዞ  እንዲሁም ልዩ የቱሪስቶች መዳረሻ በመሆኗም የውጭ መንግስታት ከሀገራችን ጋር በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት ኢንቨስት ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ ይህም በሀገራችን እየተካሄደ ላለው አለምን ያስደመመ ሁሉን አቀፍ ጥልቅ ተሀድሶ የተሰጠ እውቅናና ድጋፍ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ስኬትና ድል ነው፡፡

የኢትዮጵያ ተሞክሮና ልምድ ለሌሎች ታዳጊ የአለም ሀገራት በተምሳሌነቱ ተጠቃሽ ነው፡፡ በእጅጉ የሚጠቅም ትምህርት ሊወስዱበትም ይችላሉ፡፡ኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ምህዳሯን አስፍታለች፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ልዩነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በሰላም በመቻቻል በመከባበር በይቅርታ በምህረት ወደ ሀገራቸው ገብተው ለሀገራችን ይበጃል ያሉትን በውይይት በሀሳብ ክርክር እንዲያራምዱ ሰፊ በር ተከፍቶላቸው ወደ ሀገራቸው ገብተዋል፡፡ በርካታ እስረኞች ከእስር ተለቀው ቤተሰባቸውን ተቀላቅለዋል፡፡

ከሀገር ውጭ በተለያዩ ሀገራት በእስር ሲማቅቁ የነበሩ ዜጎችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎበኟቸው ሀገራት ሁሉ በማስለቀቅ ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ አድርገዋል፡፡ከኤርትራ ጋር የነበረው የድንበር ግጭት የብዙ ሺህ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈ የነበረ ከመሆኑም በላይ የድንበር ፍጥጫው ከአስርት አመታት በላይ የዘለቀበት፤ አካባቢውም ሆነ ሕዝቡ በመሳቀቅ የሚኖርበት፤ ልማትና እድገት ጭርሱንም የማይታሰብበት፤ በድንበር ለተሰለፈውም ሰራዊት ከፍተኛ ገንዘብ ይወጣ የነበረበት ሁኔታ ለሁለቱም ሀገራት አልጠቀመም፡፡

ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ተሳክቶ በሁለቱ ሀገራት መካከል እርቅና ሰላም ወርዷል፡፡የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኤርትራን ጎብኝተው ከተመለሱ በኃላ የኤርትራው ፕሬዚደንትም ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል፡፡

ይህ ሀገራችን በዲፕሎማሲው ረገድ የተጎናጸፈችውን ታላቅ ስኬትና ድል ያረጋግጣል፡፡  ከሰሞኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በኤርትራ ተገኝተው የአሰብና ምጽዋ ወደቦችን ጎብኝተው በቅርቡ ስራ እንደሚጀምር ገልጸዋል፡፡ የመጀመሪያዋ የአትዮጵያ የንግድ መርከብም ከበርካታ አመታት በኃላ መልህቋን በምጽዋ ወደብ ላይ አሳርፋለች፡፡ የዲፕሎማሲው ስኬት ማሳያ ነው፡፡

ጅቡቲና ኤርትራ በተመሳሳይ ግጭት ውስጥ የቆዩ ሀገራት በመሆናቸው ግንኙነታቸው  ከተቋረጠ የቆየ የነበረ ሲሆን በኢትዮጵያ አደራዳሪነትና ሸምጋይነት የእርቅ ስምምነት ላይ  ደርሰዋል፡፡ ይህም ሀገራችን በቀጣናው እየተጫወተች ላለችው ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ሚና ጉልህ ማረጋገጫ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ከቻይና ኤርትራ ቆይታ በኋላ በሠጡት መግለጫ  የኢትዮጵያ ኤርትራና ሶማሊያ መሪዎች  በአስመራ   የደረሱበት ስምምነት የሦስቱ አገራት ህዝቦች ለሰላምና ለልማት በጋራ በመሥራት ግንኙነታቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያስችል ነው ማለታቸው የዲፕሎማሲውን ውጤታማነት ይመሰክራል፡፡ ኢትዮጵያ በአህጉራዊና አለም አቀፍ ዲፕሎማሲው  ረገድ  የላቁ  ስኬቶችን በማስመዝገብ  ጉዞዋን  ቀጥላለች፡፡