ስሌት ከስሜት ከፍ ይላል!

ሳንፈልግ የጋቱን ሳንወድ የረጩብን መርዝ ዛሬ ላይ በተለያዩ ከተሞቻችን ላይ ሥቃይ ፈጥሮ አገራችን እያነባች ልጆቿም በየአቅጣጫው ያላግባብ እየተፈናቀሉ ባስ ሲልም እየገበረች ትገኛለች። በነጋ በጠባ ቁጥር ለመስማት የሚከብድ ሰው መሆንን የሚያስጠላ ሰቅጣጭ ዜና መስማት ሰርካችን ሆኗል። የምንወዳት አገራችንን ሠላም እንዳይናጋ አንድነትዋ እንዳይፈርስ በሥጋት መተከዝ  ተላምደናል። መልካ ነገር አንዱ አካባቢ ሰምተን ሳናጣጥም ሌላ መርዶ ከሌላኛው አካባቢ ሰምተን ደስታችን ወደ ሐዘን ይቀየራል፡፡

ለዚህ መድኃኒቱ ፍቅር ነው፡፡ አንድነትን መስበክ፣ የሰው ልጅ እኩልነትን ማወጅና ፍትህን ማንገስ። ያኔ የሠላም አየር ይነፍሳል፣ የተረጨብን መርዝ ይረክሳል፣ የላላው አንድነታችን ይጋመዳል፣ ያኔ ሰላማችን ይረጋገጣል አትራፊነቱ ከኛ ልቆ ጎረቤትም ይደርሳል። ምንም ሳናጣ ምንም የተከለከልን ነን። የተከለከልነውን ለማግኘት በአንድነት እንቁም ያለንን ለመጠቀም በፍቅር እንመካከር፡፡ ማንም ምንም እንዳያጣ ማንነትን ትተን ሰው መሆንን እናልቅ። ሰው ሰው እንሽተት ስብዕናን እንላበስ። ያኔ ሁሉም መልካም ይሆናል፡፡

በማህበራዊ ሚዲያ በተለይም በፌስቡክ መልካምነትን በሌላው ላይ ከማስረጽ ፍቅርን ከመስበክ ይልቅ  ውድ የሆነውን ጊዜያቸውን መሰሪ ለሆነ አላማ በማዋል አንደን ህዝን በመዝለፍ በማንቋሸሽ ግለ ሰቦችን በማነወር የተጠመዱ በዝተዋል፡፡ የውሸት ወሬ በመንዛት እርስ በእርስ የሚያጋጩ ከኢትዮጵያዊያን  ስነ ምግባ ያፈነገጡ ቧልተኞች ተበራክተዋል፡፡ አላማቸው ምንም አይደለም የተገኘውን ሰላም ማሳጣት ህዝብን አስቆጥቶ ለአመጽ መቀስቀስ ነው፡፡እኛም ሳይገባን አላማውን የማናውቀውን መልዕክትና ፎቶ እንቀባበላለን በሀላፊነት ስሜት ከመመርመር ይልቅ ስሌቱን ትተን በስሜት መመራትን ተያይዘንዋል፡፡ 

ስማኝ አንተ የፌስ ቡክ አርበኛ እቤትህ ቁጭ ብለህ አንዱን ብሄር ከሌላው ብሄር ጋር የምታናጭ፣ ማንነትህን ደብቀህ አስፀያፊ ቃላትን በህዝብና በሰዎች ስብዕና ላይ የምትከምር፣ ተራ መንደርተኛ ሆነህ ሀገርን የሚያጠለሽ ህዝብን የሚጎዳ ሰላምን የመያደፈርስ የጥላቻ ንግግሮችን በመለጠፍ የምትጠቀመው ምንድነው? የዚህ ዘመን ጀግንንት ፍቅር መስበክ ሰዎችን ማዋደድ ሰውን ማክበርና  እራስን ዝቅ አድርጎ ሌላን ከፍ ማድረግ ነው፡፡ ጥላቻ ቂምና ፉከራ የተሸናነት ካርድ በራስ ላይ መምዘዝ ነው፡፡ ማነህ? ቢሉህ ቀድመህ ሰው ከመሆንህ ውጪ ምን ልትገልጽ ምንስን ልታሳይ ትችላልህ? እኔ የበላይ ነኝ ሌላው ግን ከእግሬ ስር የምትል የዘመኑ ቧልተኛ አናካሽ ሆይ አንተ ልታፍር ይገባል፡፡ በዚህች ሰፊ ምድር መቻቻልን ከመስበክ የሰፋውን ነገር አጥበህ የምታመላክት ገና ሙሉ ሰው አልሆክም፡፡ ሰው መሆን ከአንተነትህ ላይ ጎሏል፡፡

እመነኝ ወዳጄ ሰው ሆነህ በብሄርህ ወይም በጎሳህ መኩራት ከጀመርክ፤ በማንነት መመካት ካበዛህ ሰው በሰውነቱ ማክበር ትተህ ንቀት ውስጥ ከገባህ ከሰውነት ወተሀል፡፡ በፈጣሪ ማመንህ እምንት ሚሉት ነገር ከላይህ ላይ ተኗል፡፡ በሰው ልጆች እኩልነት የሚያምን ለማህበራዊ ቀውስ መፍትሄ የሚሆን እንጂ ጨለምተኞች በሚተገብሩትና በሚለፍፉት ተራ ቧልት የሚነዛ በማህበራዊ ሚዲያ ጥላቻን የሚቀሰቅስ  አይደለም። የሌላውን ብሄር የሚያንቋሽሽ በመሰሪ ተግባም የሚሳተፍ አይደለም፡፡ እምነቱ እንዲከበርለት የሚፈልግ የሌሎችን እምነት ማክበር አለበት። ጤነኛ ሀይማኖተኛ ሰው በእርግጥም ይህን ተግባር ያወግዛል። ግን ደግሞ አቅጣጫን ማሳየት መፍሄ ማመላከት እንጂ ችግሩ እንዲባባስ አያደርግም፡፡

እቤትህ ቁጭ ብለህ ይህን የምታደርግ ከሆነ እመነኝ  የሰው ልጅ እኩል አድርጎ መፍጠሩን ክደሀል፡፡  ክፋትን ተላምደኸው ከሆነ እንዲላቀቅህ ጣር አዕምሮህ ውስጥ ያለው ትንሽነት ሰው ሆነህ በእኩልነት አምነህ ወደ ሰው ሚባል ማንነት ለውጠው፡፡ አቤት! ስብዕናን መላበስ ምንኛ ውስጣዊ ሰላም ይሰጣል መሰለህ፡፡ ፍቅርን መስበክ ሰዎችን መውደድ ትርፉ ውስጥን በሀሴት እንዴት እንደሚያጥለቀልቅ ባወከው፡፡ ዘረኝነት እንዴት ይሰነፍጣል መሰለህ፡፡ ሰዎችን እኩል ማየት አንድ መሆናቸው ማሰብ ደግሞ  ውስጥን ሰላም ሲሰጥ ብታይ እስካሁን የኖርክበት ጽልመት ያስቆጭህ ነበር፡፡ በቃህ ሰው መሆን ጀምርና እራሰህን ነጻ አውጣ፡፡ በጥላቻ በምቀኝነት በጥበት ውስጥን መሞላት እውነት ነጻነትን ይነሳል፡፡ ሰው ውደድና እራስህን ነጻ አድርግ ሰው አፍቅርና ደስታህን አቅርብ፡፡ መለወጥ ሰው መሆን አቅቶህ የተሸናፊነት ካርድ አትምዘዝ እባክህን ሰው ሁን!

አንተ የነጻነት የፍትህ ታጋይ የሆንከው ፋኖ፡ ቄሮ፣ ዘርማ ሆይ ትላንት ተበደልን ተጨቆንኩ ብልህ እሳት ለብሰህ እሳት ጎርሰህ በተቻለህ ሁሉ በደልና ጭቆናውን ከራስክ ላይ ለማሸሽ ታግለሀል ቆስለሀል ተገለህል ዛሬ ላይ ደርሰሀል፡፡ የተሻለ ክብርና እውቅናም ተችሮሀል፡፡ ምነው ታዲያ ከዚህ ደርሰህ አንተም ለመግደል እኔ የሌላው የበላይ ነኝ ብለህ በማን አለብኝነት ሌላወን ለመጨቆን ሌላውን ለመበደል ሌላውን ለማግለል ከቆምክ ምኑ ላይ ነው የአንተ የነጻነት ታጋይ የፍትህ አርበኛ ነኝ ማለት፡፡ ስንበደል ጮኸን እድሉን ስናገኝ ሌላውን መንከስህ የተነሳህበት አላማ ነበርን? በጭራሽ ይህቺ ሀግር ለሁላችን የምትበቃ ሰፊ ናት ለሁላችንም የሚተርፍ የበዛ ሀብት ያላት፡፡

ከተፋቀርን፤ ከተዋደድን ፤በፍቅር ካደርን፤ ካወቅንበት ከማንም በላይ ከፍ ማለት እንችላለን፡፡ይህቺ ኢትዮጵያ ናት! በዚህጭ ሀገር የእምነት ተቋማት በየትኛውም እምነት የተከበሩ ናቸው።  ኢትዮጵያውያንም አክብረው አንዱ ለአንዱ ይቆማሉ። ይህቺ ውብ ሀገር ሰዎች ተፈቃቅረው የሚያድሩባት ውብ ሀገር ናት። አንዳንድ ትንንሾች ግን ከመሀል አይጠፉም ቢሆንም ቅሉ ትልልቆች ስለሚበዙ መዋጣቸው አይቀሬ ነው። ሁሌም አሸናፊው እያደር የሚደምቀው እውነትና ፍቅር ነውና፡፡ ኢትዮጵያዊነት ተቻችሎ በፍቅር መኖርና በህብረ ቀለም ማጌጥ ይበልጥ ይጠነክራል፡፡ ምክንያቱም ይህቺ ሀገሬ ኢትዮጵያ ናት።

ስማኝ ፋኖ፣  ቄሮ፣  ዘርማ ከአርማው ወይም ከባንዲራው ቀድሞ ሰው ነበር፡፡ ከባንዲራው በኋላም ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ያለ ሰው ያለ ሀገር ባንዲራ ወይም አርማ ምንም ነው፡፡ የኔ ይህ ነው የአንተ ወደኔ አታምጣ እነካ የኔን ወስደህ አንተ ጋር አድርግ የአንተ ግን በአይኔ እንዳታሳየኝ ማለት ምን የሚሉት ትዕቢት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ማንም በማንም ላይ ሊጭነው የማይገባ ግለኝነት እራስ ወዳድነት ነው፡፡ የራሱን የሚወድ የሌላንም ማክበር ግድ ይለዋል፡፡እኔ የበላይ ነኝ የሚል ከንቱ ስሜት ተራ ፉከራ የትም አያደርስም፡፡ ማነው ለማን ይህ የኔ ነው ማንም አያዝበትም የሚል የራሱ ብቻ የሆነ ሀገር የሰጠው፡፡ ይህቺ ምድ የሁላችንም ናት እያሰላን ከተጓዝን ከፍ ብልን በየራሳችን አንዳጭን አንዳጭንን ሳንነካ መብረር የምንችልባት፡፡ያላትን በጋራ ተቋድሰን እራሳችን የምንለውጥባት፡፡ነገር ግን መሰማማት ርቆን መደማመጥ አቅቶን የተገኘውን እድል መስዕዋት የተከፈለበት ዛሬ በጨለመው ነገ እንተካዋለን፡፡ያኔ ሀገር ፈርሶ ፍትህ ከኛ ይርቃል፤ያኔ ሰላም ጠፍቶ ወቶ መግባ ይናፍቃል፡፡ ሀገራችን ሰፊና ሁሉ ያላት ናት አውቀን በፍትሀዊነት መጠቀም ከቻልን፡፡ ካላወቅንበት ለሁላችንም ቀርቶ ለጥቂቶቻችንም ትጠባለች፡፡

የአንተ የተሻለ መሆኑ ለማሳወቅ  በፍቅር መብለጥ በመውደድ መላቅ አለብህ ፡፡ ማነው ሀይልና የበላይነትን ተጠቅመህ ጥሩ ያከውን ነገርህ ሊቀበል የሚችለው፡፡ በፍቅር ብለጥና አንተ ጋር ያለው የተሻለ ነገር ከፍ አድርግ፡፡ የአንተን ለሌላው በሀይልና በግድ ለመጋት መሞከር ግን የአንተንም ያሳጣሀል፡፡በውይይት በመነጋገር ለሁሉም የሚስማማ ሁሉም የሚቀበለው ማግኘት ይቻላልና፡፡ ሁሉም ዛሬ የራሱን ነገር ይዞ ሰላማዊ በሆነ መልኩ  እንዲያንጸባርቅ  መንገድ እንክፈትለት መልካም የሆነው ይቆያል.. ይቀጥላልም፡፡ መልካነት ውስጡ ከሌለ አንተ እኳን እንዲጠፋ እንዲከስም ባትጥር እንኳን መልካም ስላልነበረ መቆየት አይችም፡፡ እናም አንተ ያደረከው እራስህ የተገበርከው በዚያው መልኩ ሌላው ሲተገብር አይንህ አይቅላ በመልካም ጎኑን ተመልከት፡፡ እንዲያውም እረሱን ለመግለጽ እየሞከረ ስለሆነ የሚተገብረው መልካም ነገር ከሆነ እርዳው በፍቅር ቅረበውና ከሱ ጋር አብረህ ቁም፡፡

እመነኝ አንተ ቄሮ፣ፋኖ፣ዘርማ ነገ በፍቅር አብሮ ቆመህ የማይፈታ ችግር አይኖርም፡፡ ፍቅር የማያሸንፈው ነገር ምድር ላይ አልተፈጠረም፡፡ መልካም እና ሰናይ ዘመን ከፊትህ አለና ከራሰህ አታርቀው፡፡ ታገስ ነገን እይ አብረህ ካልሆንክ በጋራ ለሰላም ካለቆምክ ነገ እራስህ ትበላለህ፡፡ ካልተዋደድክ እርስ በእርስ ከተጠላለህ እመነኘኝ አውሬው አንተ ነህ እራስህ ወገንህን የምትበላ፡፡

መልካም ነገሮችን ማጉላት ላይ ትኩረት እናድግ ቆዩማ ሰዎች ሚመስላቸው ሀሳብና እምነት ያራምዱ ግን የኛን ሳይጋፉ ተባብለን አይደል እንዴ በፍቅር ለመደመር ቃል የተግባባነው፡፡ በቃ ተዋቸው እንዴ ያነሱት የሚያራምዱት ሃሳብ እነሱ በገባቸው ልክ ነው፡፡ እኛ እሩቅ ሆነን እነሱን ከመተቸትና ትክክል መሆን ወይም አለመሆናቸውን ከማራገብ ይልቅ እኛ የገባን መልካም ነገር እንተግብር፡፡ ፍቅርን እንስበክ አንድነትን እናጠንክር መዋደዳችንን እናስቀጥል፡፡ ማንም ምንም ያነሳ ምንም ይበል በፍቅር ከኛ ጋር ይደመራል፡፡ ለኔ መፍትሄ የሚመስለኝ ፍቅር አሳይቶ ሌላን ማቅረብ መልካምነትን ሰብኮ ጥላቻን ማጥፋት እንጂ ለምን እንዲህ አሰብክ ብሎ አመለካከትን በስድብና በውግዘት ማስለወጥ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ እንድንግባባ ከተፈለገ የማያግባቡን ነገሮች በሚያግባቡን መንገድ ብንፈታ መልካም ነው፡፡ አንድ ነግር ግን ያግባባናል ሁሌም አንድነትና ፍቅር ማንንም ያንበረክካል ማንም ያባባል፡፡

ዘርማ፣ፋኖና ቄሮ የሀገሬ ልጆች! እኛ ኢትዮጵያውያን የችግሮቻችን መፍትሄ ያለው እኛው እጅ ላይ ነው። ተቀራርበን እንነጋገር እንግባባ እንደራደር የሚለያየን ነገር ይቀረፋል፡፡ ልዩነታችን የሰፋ ቢሆን እንኳን ተቀብለን አንደኛችን የሌላውን አክብረን በልዩነት ውስጥ በፍቅር እናድራለን። አንድ አመለካከት ሀገርን ቀይሮ አያውቅም አንድነት ፍቅርና ህብረት እንጂ ። የጎደለው የሚሞላው ያለውን በማጉደል አይደለም። ሀገር የሚለውጠው በሰፊ ሀሳብ እንጂ በረጅም ምላስ አይደለም። ሀገር ማለት የክብርህ መጎናፀፈያ የችግርህ መከለያ ጥላ ናት። ለራሳችን ብለን ሀገራችንን እንውደድ ለሀገራችን በጎ እንመኝ ያኔ ከፍታ ላይ እንገኛለን። ከፋታ ላይ የሚያደርሰው ደግሞ ፍቅር ብቻ ነው።

             ብሩህ ዘመን በሰው ልጆች እኩልነት ለሚያምን ሁሉ!

                          

በ  ተገኝ ብሩ/ሻሚል/