በለውጡ ዘመን የመጣልን እንቁጣጣሽ

ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ሀገርና ህዝብ በአዲስ መንፋስ በአዲስ ዕቅድ አዲሱን ዓመት በመቀበል አሮጌውን ትተው በአዲሱ ዘመን መልካም ነገሮችን ይዘው ይነሳሉ። ስለ አዲሱ ዓመት ከማንሳታችን በፊት እስቲ በጥቂቱ ያሳለፍነውን አሮጌውን ዓመት ወደ ኋላ መለስ ብለን እናስተውለው። 2010 ዓ.ም ገና ከጅምሩ ዘመኑ የከፍታ ዘመን ነው ብሎ መንግሥት መሪ ቃሉን ያወጣበት ዓመት ነበር። በዚህ ባሳለፍነው ዓመት በሀገራችን በጣም ብዙ ነገሮች ተከናውነው አይተናል።እነዚህ ነገሮች እስከ ዛሬ በሀገራችን በፍፁም አስተውለናቸው የማናውቃቸው ብዙ ክፉ ነገሮችንና መልካም ለውጦችን ያየንበትም ዓመት ነበር ።

 በ2010 ዓ.ም በብዙዎች ልብ  ሊጠፉ  የማይችሉ  ብዙ አስገራሚ ክስተቶችን ያስተዋልንበት ዓመት እንደነበር ይታወቃል። ለአብነት ያክል በአገራችን በከፍተኛ ሁኔታ የፖለቲካ መውደቅና መነሳትን ያስተዋልንበት፣ የአገራችን ኢኮኖሚ የተንገዳገደበት፣ በነበረው አለመግባባትና እርስበርስ ግጭት ብዙዎች ከአከባቢያቸው የተፈናቀሉበትና ብዙ ወገኖቻችንን በሞት ያጣንበት ዓመት ነበር። የዚያኑ  ያክልም በፍፁም በጎ ነገሮችንም ያየንበት ዓመትም ነው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም  በዚሁ ዓመት አጋማሽ ላይ ነበር ወደ መንበረ ሥልጣኑ ብቅ ያሉት ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ዕለት አንስቶ በሁላችንም ልብ ደብዝዞ የነበረውን ኢትዮጵያዊነትን ለማደስ ደፋ ቀና ማለት የጀመሩበት፣ በአገራችን የወደቀውን ፖለቲካ ለማንሳት የታገሉበት፣ በተለያዩ አከባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን ግጭትና አለመግባባትን ለማርገብ የተሯሯጡበት እና መልካም አገራዊ መግባባቶችን ለመፍጠር ብዙ የሠሩበት ዓመት ሆኖ አልፏል።

በአጠቃላይ በ2010 ዓ.ም በሀገራችን እጅግ በጣም ብዙ መልካም ነገሮችን ያስተዋልንበትም ዓመት ነበር። ለአብነት ያህል  መቼም ልንረሳቸው የማንችላቸው ነገሮች መካከል  ዋነኛው በኢትዮጲያና በኤርትራ መካከል ለብዙ ዓመታት የነበረውን አለመግባባት ወደ መልካም መግባባት ተቀይሮ ሁለቱ ሀገራት በሰላምና በፍቅር በአንድ መድረክ ላይ አብረው የታዩበትና በሁለቱም ሀገራት የሚኖሩ ህዝቦች የተገናኙበት ዓመት ሆኖ ማለፉም ሁላችንም የማንዘነጋው  ነገር ነው። እንዲሁም በተለያዩ ጊዚያት በፖለቲካ ምክንያት ለብዙ ዘመናት በወህኒ ቤት የነበሩ ዜጎችም ከእስር የተፈቱበትና የዲሞክራሲ ጭላንጭልን ለማየት የቻልንበት ዓመት ሆኖ አልፎዋል። ካለፉት አምስት ወራት ወዲህ የታየው የለውጥ ጅማሬ መንግሥትና ህዝብ የ2011ዓ.ም አዲሱን ዓመት በብሩህ ተስፋ ለመቀበል ያስቻለበት ወቅት ነው።

በሀገራችን አሁን ያለው መረጋጋትና ከቀደሙት  ወራት በእጅጉ የተሻለ እና በአጠቃላይ መልኩ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ሲታይ ሰላማዊ በመሆኑ ከዘመን መለወጫና ዋዜማው በዓል ጋር ተያይዞ በኅብረተሰቡ ዘንድ የተፈጠረውን ሰላማዊ ድባብ ቀጣይነት እንዲኖረው ልንጥርና ሰላማችንን ልንከባከብ ይገባል። ምክንያቱም ይህ ሰላም ለሀገራችንና ለህዝባችን በጣም ዋስትና ስላለው ነው።

ዘመን በዘመን ሲለወጥ አንዱ ዓመት አልቆ ሌላው ሲተካ  ዘመናችንን የምናከብረው ሰላምና ፀጥታ ሲኖር ነው። ሰላም ሲኖር ህዝቦች በፍቅር አብሮነታቸውን አስከብረው መኖር የሚችሉት፤ በጥቂቱም ቢሆን ባሳለፍነው ዓመት በሀገራችን በነበረው ግጭት ብዙ ወገናችንን እንዳጣንና ብዙ ኪሳራ ውስጥ እንደገባን የሚረሳ ነገር አይደለም። መንግሥትም ሁልጊዜ  ስለ ሰላም አበክሮ የሚናገረው የሰላምን ፋይዳ ዜጋው እንዲረዳው ነው ።

አዲስ ዓመትን ስንቀበል መዘንጋት የሌለብን ሌላኛው  ነገር ከአዲስ ዓመት አከባባር ጋር በተያያዘ በኅብረተሰቡ ዘንድ የተፈጠረውን የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ለመሥራት የነበረውን ከፍተኛ መነቃቃትን ማስቀጠል ይገባል። ለአብነት ያህል የዐቅመ ደካሞችን ቤት መጠገን፣ አቅም ለሌላቸው ወላጆች ለልጆቻቸው  በአዲሱ ዓመት  ትምህርት እንዲቀጥሉ በቁሳቁስ መደገፍ፣በበጎ ፍቃድ ደም መለገስ እና የመሳሰሉት መልካም ተግባራት በአዲስ ዓመት ዋዜማ ሲካናወኑ የነበሩ ሥራዎች ናቸው።እነዚህ ተግባራት በዓላትን ወይም የሆነ ወቅትን ጠብቀን የምናከናውናቸው ሊሆን አይገባም። ሁሌም ሊከናወኑና ባህላችን የሆነውን መረዳዳትን ማጠናከር ይገባናል። “ለወገን ደራሽ ወገን ነው ”እንደሚባለው እርስ በርሳችን መደጋገፍና  መቆም ካልቻልን የተሻለችና የተለወጠች ኢትዮጵያን ማየት አንችልም።

በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የዐቅመ ደካሞችን ቤት ከማደስ በተጓዳኝ በአዲስ አበባ ከተማ በሕገ ወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ የቀበሌ ቤቶችን ለዐቅመ ደካሞች መተላለፉ፣በክልሎችም“ ፈለግህን እንከተል” በሚል መሪ ቃል የተለያዩ በጎ ሥራዎችም ሲሠሩ ነበር። ለአብነት ያህል በደቡብ ክልል በተለያዩ ከተሞች ተመሳሳይ የድጋፍ ሥራዎች ሲሠሩ ለማስተዋል ችለናል። ይህ መልካም ተግባር በተወሰኑ አከባቢዎች ብቻ የሚቀር መሆን የለበትም በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሁሉንም ኅብረተሰብ ባሳተፈ መልኩ ዘወትር ሊከናወን የሚገባው ተግባር ነው። ነገር ግን በሀገራችን የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴና በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ላይ የታየው የህዝቡ ፍቅርና በጎ ተግባር ያልጣማቸው አንዳንድ ቀናተኞች በአዲስ አበባና በአንዳንድ አካባቢዎች ህዝቡ እንዲቃቃር ለማድረግ ቢፍጨረጨሩም ሊሳካላቸው አልቻለም።

ሌላኛው የዘንድሮውን አዲስ ዓመት አዲስ ሊያደርገው የሚችለውና ልዩ የሆነው ነገር ደግሞ በተለያዩ ጊዚያት በሀገራችን በነበረው የፖለቲካ አለመግባባት የተነሳ ከሀገራቸው ርቀው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ልሂቃን ወደ ትውልድ ሀገራቸው በመግባት ከቤተሰቦቻቸውና ከሚወዳቸው ህዝብ ጋር አዲስ ዓመትን እንዲያከብሩ የተደረገበት እና እነሱም የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው ለብዙ ዓመታት የራቁባት ሀገራቸውንና በጉጉት ሲጠብቃቸው የነበረውን ህዝብ አክብረው በሰላም ገብተው ከሚወዳቸውና ከሚያከብራቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የዘንድሮን አዲስ ዓመት በሰላምና በደስታ አክብረውታል።

በዓሉን ለማክበር ከውጪ  ከመጡ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ በአሜሪካ ከፍተኛ ተሰሚነትን ያተረፉ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገ/ማርያም ይገኙበታል። ከ48 ዓመታት የስደት ቆይታ በኋላ ወደ ሀገራቸው የተመለሱት እና የዳበረ ዕውቀትና ልምድ ባለቤት እንደሆኑ የሚነገርላቸው ፕሮፌሰር አለማየሁ ወደ ግል የሚዛወሩ የልማት ድርጅቶችን ጉዳይ በተመለከተ ለመንግሥት የማማከር አገልግሎትን እንዲሰጡ  የተሰየመውን ሀገራዊ መማክርት ጉባኤ በሰብሳቢነት ሲመሩ የነበሩ መሆናቸው ይታወቃል። እኚህም ምሁር በአዲሱ ዓመት ወደ ሀገራቸው ከገቡ ኢትዮጲያውያን መካከል  አንዱ ናቸው።

የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጥሪ ተቀብለው በዘመን መለወጫ በአል ላይ ለመታደም ከውጪ ሀገራት የመጡ ኢትዮጵያውያንና የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራችን እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ምንነትና ጠቀሜታውን ተረድተው ለውጡን ለማስቀጠል እነሱም የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል። የለውጥ ጅማሮው እንዲቀጥል፣ የዲሞክራሲ ሥርዓት እንዲሰፍን፣ የሕግ የበላይነት እንዲረጋጋጥ እና ጥላቻና አለመግባባት ከአገራችን እንዲርቅ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸውን  መወጣት አለባቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ “በፍቅር እንደመር በይቅርታ እንሻገር” በሚል መሪ ቃል በሚሊኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው የአዲስ ዓመት አቀባባልና ወደ ሀገራቸው ለገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተደረገው ደማቅ አቀባባል ስነ ሥርዓት  ላይ እንደተናገሩት ያተጠናቀቅነው 2010ዓ.ም እኛ ኢትዮጵያውያን በአስፈሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነን ማሳለፋችንን በመጠቆም  አዲሱን ዓመት  በስጋትና በተስፋ፣ በጨለማና በብርሃን፣ በጥላቻና በይቅርታ እንዲሁም በቂምና በፍቅር መካካል ሆነን እንደምንቀበለው አስታውቀው  ያሳለፍነው 2010 ዓ.ም በሀገራችን በነበረው የተቃወሰ የፖለቲካ ሁኔታ ሳቢያ ኢኮኖሚው የተቃወሰበት፣ ማኅበራዊ ህይወታችን ለሽብር የተጋለጠበት፣ ወጣቶች በአመፅ ሰልፍና በሞት ጥላ ሥር የዋሉበት አስጨናቂና ከባድ ዓመት ነበር ሲሉ በጥቂቱ  ባሳለፍነው  ዓመት በሀገራች የነበረውን ውጥረት ገልፀዋል።

ሁሉም ወደ ሀገራቸው የገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገራችን እስከ ዛሬ በተለያዩ ውጥረቶች ውስጥ እንደነበረች አውቀውና ተረድተው ከዚህ ውጥረት ሀገሪቷን ሊያወጣ የሚችል መልካም ሃሳብን በማምጣት ከመንግሥት ጋር በመሆን ከዚህን ቀደም ሀገራችን የታወቀችበትን መጥፎ ገፅታን ከመቀየር አኳያ ከፍተኛ ሚናን መጫወት ይኖርባቸዋል። ይህ ካልሆነ የተሻለችና በሁሉም መስኮች የተሳካላት ኢትዮጵያን ማየት ህልም ሊሆንብን የሚችል ነገር ነው። ይህ ህዝብ እንዲ በነቂስ እየወጣ እነዚህን የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያለምንም መሰላቸት ሲቀበል የነበረውም ይህንን ተስፋ አድርጎ መሆኑን አውቀው ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገራችን አሁን ላይ የጀመረችውን የለውጥ ጅማሮች ማስቀጠልና የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።

ሌላኛው በአዲሱ ዘመን የተከናወነዉ ተግባር ደግሞ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱን ዓመት በቡሬና በዛላንበሳ ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ሠራዊቶች ጋር አንድ ላይ በጋራ በፍቅር አክብረዉ ውለዋል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የራሳቸዉን ቤተሰብ ያላቸው ቢሆንም በዓሉን ከቤተሰባቸዉ ተለይተው በኢትዮ ኤርትርያ  ድንበር ላይ ባሉ አጎራባች ህዝቦችና ሠራዊት ጋር በጋራ ማክበራቸው ሀገራዊ ግዴታቸዉን ለመወጣት ያላቸዉን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በሁለቱ ሀገራት የተጀመረውን መልካም ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር ተግባር ነዉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጉብኝታቸዉ ሲመለሱ እንደገለፁት ቀደም ሲል በገቡት ቃል መሠረት አዲስ ዓመትን አብረው ድንበር አካባቢ የነበረዉን ምሽግ አፍርሰዉ በጋራ ደስ በሚል መልኩ ዳስ በመጣል በፍቅር ዓመቱን እንደተቀበሉት ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም የዚህ ጉብኝት ዋንኛ ዓላማው ሰላም ምን ያህል ጉልበት እንዳለዉና በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረዉን ሰላም የበለጠ ለማጠናከር እንደሚረዳ ገልፀዋል፡፡ በኢትዮ ኤርትራ ድንበር ላይ ያሉት አጎራባች ህዝቦችና ሠራዊቶች  ለዘመናት በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረዉ አለመግባባት በእንደዚህ ዓይነቱ መንገድ በሰላም ተፈቶ በዓሉን በጋራ በፍቅር በማክበራቸዉ ከፍተኛ ደሰታ  እንደተሰማቸው ተናግረዋል ፡፡ 

ሌላኛው የዘመን መለወጫን በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲከበር በተጓዳኝ ደግሞ የሀገራችን ብሔር ብሔረሰቦች የየራሳቸዉን የዘመን መለወጫ በዓላትን እንደሚያከብሩ ይታወቃል። ለአብነትም ጨምባላላ፤ ዘንድሮ ከመቼውም በተለየ መልኩ የሚከበረዉን የኢሬቻ በዓልን ማንሳት እንችላለን፡፡ እነዚህን በዓላት ስናከብር ሁሉም ብሔር ብሔረሰብ በፍቅርና በመከባበር አብሮ በማክበር ኢትዮጵያዊ ባህላችንን ጠብቀን አቅመ ደካሞችን በማሰብና በመርዳት መሆን  ይኖርብናል፡፡

አዲስ ዓመትን አንድ ብለን ስንጀምር ሌላኛው የምናስበው ነገር ደግሞ የትምህርት ቤቶችን መከፈትን ነው። የትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ ህፃናትና ወጣት ተማሪዎች በመነቃቃት ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ የሚደርጉትን መነሳሳት ሁላችንም የምናዉቀዉ ነገር ነው፡፡ ትምህርት ቤቶችም ተማሪዎቻቸውን ለመቀበል ዝግጅቶቻቸዉን ጨርሰው ወደ ሥራ ለመግባት በቁርጠኛነት ተነስተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀዉ በሀገራችን ምሁራን ረቂቅ ጥናት ሰነድ በትምህርትና ስልጠና ችግሮችና መፍትሄ ዙሪያ ተጠንቶ የነበረዉ ፍኖተ ካርታ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ይህ ፍኖተ ካርታ ለቀጣይ 15 ዓመታት የሚያገለግል ሲሆን ሰሞኑን በሀገራችን ላሉት መምህራን በሙሉ ስለፍኖተ ካርታው ምንነት በቂ ግንዛቤ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ የመማር ማስተማር ሂደቱ ተጠናክሮ እንዲከናወን የሚረዳው ስለሆነ በሁሉም ደረጃ ያሉ መምህራን በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ያሉትን ችግሮችና መፍትሄዎቻቸዉን እንዲረዱ ለማድረግ ታስቦ የቀረበ ጥናት ነው፡፡ ከዚህ ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በኋላ ሁሉም በሀገራችን ያሉ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሁሉም  የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓቱ ይጀምራል፡፡ በተጨማሪም ሀገሩን የሚወድ፣ ምክንያታዊ የሆነ፣ ለሁከትና ብጥብጥ ያልተመቸን ዜጋን ከመቅረፅ አንፃር ትምህርት ቤቶች ያለባቸውን ኃላፊነትን አውቀው ለነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን መፍጠር ይገባቸዋል።