መቃቃርና ጥላቻ ይቅር ብቻ ይቅር ብቻ

አገራችን ኢትዮጵያ ካሏት መልካም ዕሴቶች ውስጥ አንዱ መደጋገፍ፣ መረዳዳትና ያለንን ማካፈል ዋነኛው ነው፡፡ በያዝነው አዲስ ዓመት ዋዜማና መባቻ ይህንን ዕሴት ለማዳበር  የተለያዩ የበጎ ፍቃድ ሥራዎች ሲከናወኑ ተስተውሏል፡፡ በዚህም  የ2010 የበጎ ፍቃድ  ሥራዎች ክንውን  ያማረና የሰመረ፣ ብዙ ዜጎችም የተሳተፉበት ነበር፡፡ ይህም በሀገሪቱ ለተፈጠረው ለውጥ አንዱ ማሳያ ነው ማለት ይቻላል፡፡  

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  በድንበር ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ ሥራዎች ዙሪያ ከወጣቶች ጋር ሠፊ ውይይት አድርገዋል፡፡ ወጣቶች በተለያዩ ክልሎች ለበጎ ሥራ መሳተፋቸው  ባህልን ከማወቅ፣  አንድነትን ከማጎልበት እና ጥላቻን ከማራቅ አንፃር ጉልህ ሚና እንዳለው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም በሰኔ 16ቱ የቦንብ ፍንዳታ ለተጎዱ ወገኖች ደም ለግሰዋል፡፡  የአንዲት እማሆይ ቤትን በማየትም እንዲታደስ በመጣርና ለመተግበር በመሞከር ለሌሎች አርአያነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በፍቅር እንደመር በይቅርታ እንሻገር በሚል የአዲስ ዓመት መሪ ቃል  ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለተቸገሩ ወገኖች ደም በመለገስ፣ ቤት በመጠገን እንዲሁም  የትምህርት መሣሪያዎችን በማሟላት  ሓላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ መስተዳድር የአዲስ ዓመት ስጦታ ለእናት ሀገሬ በሚል መሪ ቃል ከነሀሴ 28/2010 እስከ ጳጉሜ 1/2010 በሚሊኒየም አዳራሽ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ግለሰቦች፣ አርቲስቶች፣ ተቋማት ተሳትፈዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የቀበሌ ቤት ወይም የመኖሪያ ቤት ለሌላቸው የተወሰኑ ግለሰቦችና ለዐቅመ ደካሞች ቤት  ተሠጥቷቸው የቤት ቁልፍ ተረክበዋል፡፡

እነዚህ ሁሉ ነገሮች የተከናወኑት በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንዲል ተረቱ፡፡ አንድነትና መተባበር ካለ የማይፈታ ችግር የለም፡፡  ነገር ግን የበጎ ፍቃድ ሥራዎች የክረምት፣ የአዲስ ዓመት ወይም የአንድ ሰሞን ሆይ ሆይታ ብቻ መሆን የለባቸውም፡፡

በርግጥ በአብዛኛው በበጎ ፍቃድ ሥራዎች ላይ የሚሳተፉት በትምህርት ላይ የሚገኙ  ወጣቶች ቢሆንም ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችም ዐቅማቸው በፈቀደ መጠን የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይገባቸዋል፡፡

በጎነት በብዙ ነገር  ይገለፃል፡፡ ዕውቀት ያለው በዕውቀቱ፣ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ሀሳብ ያለው በሃሳቡ  በአጠቃላይ በጎ ነገርን ለማድረግ ቅንነቱና አዎንታዊ አመለካከት ካለን ምንም የሚያግደን ነገር አይኖርም፡፡

“ሀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሀምሳ ሰው ጌጡ” እንደሚባለው ተቋማትም በዋናነት ከሚያከናውኗቸው ሥራዎች ጎን ለጎን የበጎ ፍቃድ ሥራዎች ላይ መሳተፋቸው ተገቢ ነው፡፡በዚህም እርስ በርስ የመደጋገፍ ባህልን በማዳበር የብዙ ወገኖችን ችግር መቅረፍ ይችላሉ፡፡

በ2011 ዓ.ም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው የሚለውን መሪ ቃል በመያዝ በበጎ ፍቃድ ሥራዎች መሳተፍ አለበት፡፡ በጎ ነገርን ለማድረግ ሁኔታዎችን መጠበቅ የለብንም፡፡ በእለት ተእለት አኗኗራችን ልንተገብረው ይገባል፡፡ ጊዜ ቦታና ሁኔታዎች እስኪመቻቹ ጠብቀን የምናደርግ ከሆነ ግን የይምሰል ወይም የታይታ ይሆናልና፡፡   

ሀገራችን የጀመረችውን የለውጥ ጎዳና ለማስቀጠል ዘር፣ ብሔር ሀይማኖት ሳንለይ እጅ ለእጅ በመያያዝና አንዱ ለሌላው አለኝታነቱን በመሳየት እንዲሁም ከእኔነት ወደ እኛነት በመሸጋገር  ወደ ፊት መጓዝ አለብን፡፡ እኛነት ጥላቻን ሳይሆን ፍቅርን መለያየትን ሳይሆን አንድነትን ይሰብካልና እኛ ለማለት በዘር በሀይማኖት በብሔር አንድ መሆን የለብንም ያን ጊዜ መደመራችን በተግባር ያሳየናል፡፡መቃቃርና ጥላቻ ይቅር ብቻ ይቅር ብቻ ያልነውም ትብብርና ፍቅርን እናዳብር ለማለት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት