ሀገሬን የምትል ሆይ ስማኝ!

በቃ እጣ ፋንታህ ሆነና አሁን የተገኘህበት ያለህበት ቦታ ያንተ መገኛና መታያ ሆነ፡፡ ማንም ማመልከቻ አስገብቶ ከዚህኛው ብሔርና ማህበረሰብ እዚህ ቦታ ላይ መወለድ እፈልጋለሁ ብሎ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል አመልክቶ አልተፈጠርንም፡፡ አዎ አሁን ላይ የተገኘነው እሱ ሀያሉ አምላክ በወደደውና በፈቀደው ቦታ ነው፡፡ የእኛ አስተዋጽዖ ምንም የለም፡፡ አንተን ከተገኘህበት ማህበረሰብ ውስጥ ሊያስገኝህ ፈልጎ ነበር አደረገው፡፡

ውደደው ወይም ጥላው በቃ አንተ ማለት አንተ ነህ፡፡ የአንተ ከፍታ ልክ ምታሰምረው አንተው እራስህ ነህ፡፡ ላንተ አድልቶ የሰጠህ ወይም ያሳነሰብህ ነገርም የለም፡፡ ምክንያት ስላለው በዚህ መልክ አስገኘህ፡፡ ሰው ሆነህ እራቆትህ ምድርን ሳትፈልግ ተቀላቀልክ፡፡ ንጹህ የሆነ ልብና አይን ተላብሰህ ተገኘህ፡፡   

እናም ሰዎች ንጽህናህ አነተቡት፡፡ ሞረዱህ እኛ ምርጥ ዘር ነን እነ እንትና ደግሞ ምራጭ አሉህ፡፡ እኛ ተመርጠን የተገኘን ነን ብለው ያልተመረጡ ናቸው ያሉትን ሌሎችን እያሳዩህ፡፡ ቤተሰብህን ወደህ የከበቡህ ጎረቤቶችህን የጎሪጥ ማየት ጀመርክ፡፡ ምልከታህን አስፍተህ የሌላን በጎነት ከማየት ይልቅ ያጠለቁልህ ጥቁር መነጽር በጎነትን በክፋት የሚቀይር ነውና የሌሎች መልካም ስራ እንደ ሴራ ታየህ፡፡ ሲፈጠር ብሩህ ነገር እንዲያሳይህ የተፈጠረለህ አይንህ ጋርደውት አጠበቡብህ፡፡ ፍቅር ሞልቶት የፈጠረው ልብህ በጥላቻና ምቀኝነት ሰፍረው በጎነትን አብሮነትንና ህብረትን አልቀበል አለህ፡፡

እስቲ አንድ ማሳያ እንመልከት ዛሬ ጠዋት ከቤቴ ወደ መስሪያ ቤት የሚያደርሰኝ ታክሲ ይዣለው፡፡ ከጎኔ ቆንጅዬ ህጻን ልጅ/ እድሜዋ በግምት ከሶስት አይዘልም/ ከአባትዋ ጎን ቁጭ ብላ የሁሉም ተሳፋሪ ትኩርት የሚስቡ ጣፋጭ ወሮዎችን በቃለ መጠይቅ መልክ ከአባትዋ ጋር ትቀባበላለች፡፡ ሁሉም ተሳፋሪ በዝምታ ተውጧል፡፡ ልጅትዋ ጥያቄዎችዋን ቀጥላለች ተሳፋሪው የሰማውን ያህል በሳቅ እያጀባት ጉዞው ቀጥሏል፡፡..መሀል ላይ ግን ሁሉንም ፀጥ ያደረገ ጥያቄ ጠየቀች ይሄ ግን የሚያስቅ አይደለም ፊትን ቅጭም የሚያደር ብዙ የሚያሳስብ የሚያስደነግጥም….ዛሬ ያለንበት የሚያመላክት ትውልዱ እያስተማርነው  ያለውን  የሚያሳይ፡፡

ልጅ፡-“……አባቢ ምንድነህ?”  አባት፡-“እንዴ ሚጣዬ ምን አይነት ጥያቄ ነው….ምንድነህ ማለት…”
ልጅ፡-“እራስህ እንዴ… ምን እንደሆንክ አታውቅም ቆይ ምንድነህ ነው ያልኩህ ? ”
አባት፡- “ሰው ነኛ ሚጣዬ…”  ልጅ፡- “ እሱን አልኩህ ባባ ደሞ… ለምሳሌ እኔ ….ነኝ /አንድ ብሄር ጠርታ/ ፡፡ አንተ እንትን ነህ እንትን ወይስ እንትን /አሁንም ሶስት የተለያዩ ብሄረሰቦችን ለምሳሌነት ጠቅሳ መልስ ጠበቀች፡፡ አባትዬውን ጨምሮ ሁሉም ተሳፋሪ መልስ አልሰጣትም ግን ሁሉም እርስ በእርሱ ተያየ፡፡ ተሳፋሪው እርስ በእርሱ ምንድነህ እየተባባለ ይሆን እንዴ ? ፡፡ መውረጃዬ ደርሶ ለመውረድ ረዳቱን ምልክት ሰጥቼው ታክሲው ቆመልኝ፡፡ አንድ ነገር ብዬ ወረድኩ፡፡ “ይሄው!. የዘራነው ፍሬ ማፍራት ጀምሯል፡፡ይሄን ክፉ አረም ለመንቀል ካልጣርን ነገ አብረን ታክሲ አንይዝም፡፡ ሚጣዬ መልሱን እኔ ልንገርሽ አባትሽም አንቺም ሰው ናችሁ እሺ፡፡

ይህች ልጅ ጥያቄዋ መሆን የነበረበት ከዚህ ፈጽሞ የራቀ ነገ ስታድግ የሚጠቅማትን ነበር ግን እኛ ለዚህ ጥያቄዋ በጭንቅላትዋ መቀረጽ አስተዋፅዖ አደረግን፡፡ ማንም ንጹህ ነኝ ብሎ ደረቱን ነፍቶ ሊናገር አይችልም፡፡ ሁሉም የቤት ስራውን በትክክል አልተወጣማ፡፡  

የህዝቡን ስሜትና መንጋነት እየተከተላችሁ በየ እለቱ አቋማችሁን የምትቀያይሩ ፖለቲከኞቻችን ፖለቲካችሁ እንጨት እንጨት ብሎናል። ምናችሁም አይጥምም እስቲንትርካችሁ ቆም ጋብ አርጉትና ስለ ሰላም ብቻ ስበኩ ስለ ፍቅር አንድነት አውሩ። ተሸናንፈሰችሁ ስልጣን ላይም ብትወጡ(እዚህ ሀገር ላይ እስካሁን ማሸነፍ ስለሌለ ነው)እንኳን ህዝብ ከሌለ ማንን ልትመሩ ነው? አዎ የሰለቸን የፖለቲካ ንትርካችሁ አቁሙና ሰው አዕምሮ ላይ ስሩ።

 ኢትዮጵያዊያን ጨዋዎች ነን ፣ሀገራችን ቅድስት ናት ህዝባችን ብሩክ ነው እየተባለ እንሰበካለን ተደጋግሞ ይነገረናል። ግን ደግሞ አውሬዎችም ታቅፈናል። ይሄም ይወራ፡፡ እያየነው ያለውን ጉድ የሚያሳዩን የኛ ጉዶች ጉዶች አይደሉ? ከየትም አልመጡም ከኛው የበቀሉ ናቸው፡፡

በየ ቦታው ለሰው ልጅ ርህራሄ የሌላቸው ስብዕና የሚባል ነገር ያልተጠጋቸው ሰው መሳይ መሰሪ ኢትዮጵያዊያን በርክተዋል። ሁሉንም ክልል ባዳረሰ መልኩ ይህቺ ብሩክ በተባለች ምድር የሰው አውሬ በቅሎ ሰዎችን መብላት ጀምሯል። አዎ ኢትዮጵያዊ ነው ይሄ ሰው ሚሉት ሴጣን። የትም ይሁን በማንም ታዞ ብቻ ስው እንዲያርድ ሰው እንዲፈጅ ሰው ሊበላ ሰው መስሎ የተላከ አውሬ ነው ።

ኢትዮጵያ የተባረከች ምድር ስለሆነች ከስዋ የተፈጠረ አይደለም ብሎ ሚክድ የለም። እዚሁ የተፈጠሩ የኛው ጉዶች ናቸው። እነዚህ ሰው በላ አውሬዎች ለማስቆም ሁሉም የቤት ስራ ይጠበቅበታል። መሰል እንከፎች እንዳይፈጠሩ ቤተሰብ ስለ ልጆ መጨነቅ ይኖርበታል። አካባቢ ስለራሱ ስለ ትውልዱ ሊመክር ይገባል። የሀይማኖት አባቶች ሴጣኑን ለማውጣት ክፋቱን ለመቅበር አምላከረን መማፀን ይገባቸዋል። ለወንጀለኞች በበራከት እንዳሻቸው መፈንጨት መደላደልን የፈጠረው መንግስት ስራውን ለመስራት መርፌ እስኪወጋ መተኛቱን ማቆም ይገባዋል።

ሚዲያው የወቅቶችና ሁነቶች ዋይታን ብቻ ሳይሆን እውነት እንዲወጣ ፍትህ እንዲሰፍን ፍቅር እንዲነግስ መስበክ ይገባቸዋል። ትውልድ እንዲገራ ሀገር እንዲደረጅ መጣር ይጠበቅባቸዋል። ሁሉም የሚኖረው መገኘትም የሚችለው በጎ የሆነውን የቤት ስራውን ሲሰራ ነውና። ዛሬ ላይ እርስ በእር መጠላለፍ አቁመን እርስ በእርስ መወነጃጀሉ ጋብ አድርገን ጥሩም መጥፎም ምናስተናግድባት ሀገር እናድን። ሀገር ከሌለ ድነትም ሽረትም ከፍታም ዝቅታም የለም። ከጥፋትና ሲቃ ውጪ፤ ከእሳትና ሞት ውጪ።

ሀገሬ ክብሬ የምንላት ሀገር እንገንባ አፍራሹን እናንፅ። ትውልድ እንደ ህንፃ አይደለም ህንፃ ሲሰራ ከተጣመመ ብሎኬት ነውና ፈርሶ ተደርምሶ መልሶ ይደለደላል ይታነፃል ከዚያም ቀጥ ይላል። የሰው ልጅ ባህሪው ያልተገራ ጥሜትን የተላበሰ ሆኖ ከተገኘ እንደ ብሎኬቱ አይፈር ስ ነገር ሰው ነው። ይህን መግሪያው የተጣመመውን ትውልድ ማቅኛው አንድ ነገር ብቻ ነው። እሱም ፍቅር ነው። በፍቅር የማይናድ ተራራ ያህል ጥላቻ የማይረጥብ ድንጋይ ልብ የለም። ሳናቋርጥ ፍቅርን መስበክ እንተግብር በፍቅር ጥላ ስር ተቻችሎ ማደር ተባብሮ ማደግ ደስታና ሀሴት ለሁሉም ይዳረሳል። ይሄ መርዝ ማርከሻው ፍቅርና ፍቅር ብቻ ነው።

እዚህ ላይ ግን መልካምነትን ሚሰብኩ አንድነትን የሚናፍቁ ለሰው ልጆች ሰላም ውሎ ማደርና በፍቅር መኖር የሚታትሩትን ልፋት ገደል መክተቴ አይለም፤ይታወቅልኝ፡፡ ሁሌም ይህችን ሀገርና ህዝብ ለማቅናት መልካም መንገድን ለማመላከት የሚለፉ ብዙ አሉ ክብር ለነሱ ይገባቸዋል፡፡እውቅናም መስጠት ይገባል ለነዚህ የሰላም አምባሳደሮች የፍቅር ጀግኖች፡፡

በአንጻሩ ደግሞ አንዳንድ አሳፋሪዎች ምን አይነት ልዩ ማፈር ልናፍርባቸው እንደሚገባ ሁሉ ግራ ያጋቡናል። እንደኔ ግን በጥላቻ ተሞልቶ ህዝብን ከህዝብ የሚያናክሱ የክፋት መልዕክተኞች እወቅና ባንሰጣቸው። እነዚህ ጎጠኛ ሙህር ተብዬ መንደርተኞ ለህዝብ ክብር እንደሌላቸው በደንብ ማሳያ ሰዓታቸው ነውና የተፋፋመው መፈቃቀራችን በፅልመት ውስጥ ሆነው በሸውራራ መነፅራቸው እየተመለከቱ ባደፈ አፋቸው ምንም ቢሉ ምንም አለማለት የሚሻል ይመስለኛል። እናንተ በዘረኝነት ናላችሁ የዞረ ቆሻሻ ነገር ሙጭጭ ያላችሁ ትንንሾች ሆይ። ተግባርና ሀሳባችሁ የመዝቀጣችሁ ማመላከቻ ነው። እንዴት እምነት አለን ብላችሁ በፍቅር ጥላቻ ለመቀየር ትደክማላችሁ፣ በዘረኝነት ሰውን ከሰው ለማናከስ ታሴራላችሁ? ያሳፍራል፡፡

በቃ እኛም ትንሽነታቸው ተረድተንና  አውቀን ከእነርሱ መልካም ነገር መጠበቅ እናቁም!  ተግተን ቤታችንን ካፀዳን ዝንቦች መች ይኖሩበትና።  ንቀን እንተዋቸው አቦ። ደግሞ አጋጣሚ ካገኘን ተግባራቸው መልካም አለመሆኑ እንገር፤ እንገስጽ እናውግዝ፡፡  ግን አደራ ህዝብና ግለሰቦችን እየለየን ። እንደ ህዝብ ፈፅሞ መተቸት ከኛ አይጠበቅም። መስፋት ህዝብን ማክበር ሁሉም ወገን መሆኑ ተገንዝቦ ሳይሰስቱ ፍቅርን መግለፅ የዘወትር ምግባራችን ይሁን። እነዚያ ማፈሪያዎች ግን እውቅና ባንሰጣቸው መልካም ነው። ክርፋታቸውን እየተቀበልን ማስተጋባት ነው የሚሆነው ትርፋችን። ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ያለው የኢትዮጵያ አየር የሀገሬን ምድር ሰላም ውሎ ይደር።

መቼም የተንሸዋረረ እይታ ያለው ካልሆነ በቀር ሀገር ምድሩ ስለ ፍቅር ሲዘምር ስለ አንድነት ሲሰብክ ማን ይከፋዋል። ለመደመር ቀድሞ መመርመርን ይቅደም። ከዘረኝነት፣ከጥላቻና ከምቀኝነት ደዌ መፅዳቱን ያረጋግጥ። እነዚህ ውስጡ ያሉ መቶ ድምቀቶችንን ከሚያደበዝዝ እዚያው ይቆይ። ተደምሮ አይቀንሰን ይሄ ኔጌቲቭ።ባይሆን ይታከም የእውነት ከገባን ከፍቅር በላይ መድሀኒት ከአንድነት በላይ ፈውስ የለም።ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ እና ብቻ የላቀ ክብር በሁሉም ሊሰጠው ይገባል። በሰውነት መበላለጥና ማነስ የለም ሁሉም ሰው በሰውነቱ እኩል ነው።በጎ የሰራ ፍቅርን የሰበከ መዋደድን ያፀና ለሰው ልጆች በጎ የዋለ ሰውን ያልበደለ ፍትሀዊ የሆነ ግን ላቅ ይላል በምግባሩ።

 
ወዳጆቼ ስለፍቅር ብሎ ሁሉንም ከመተው በላይ አሸናፊነት የት አለ። ይቅር ተባብሎ ከመደመር በላይ ከፍታ የቱ ጋር ነው። አሁንም ሴጣን ደሙ ውስጥ ያለ አለ።መፈወስ ውስጡ ያለን ጥልሸት ወደ ብርሀን መለወጥ የተሳነው በተለይ በዚህ መንደር ብዙ ነው። ቢሞክሩት በፍቅር ማደር ምንኛ ልዩ ጣም እንዳለው ባወቁ።አሳዛኞች ናቸው አሁንም በክፋት መረብ ተተብትበው ጭለማ ገደል ውስጥ ይዳክራሉ።

ሰው ለፍቅር ብሎ እራሱን ይሰዋል የዚህ አይነቱ ጥላቻ ለመዝራት እያሴረ ያለ እንቅልፍ ያድራል።ቆዩኝማ ሰው እንዴት እራሱን ጭንቀት ውስጥ ይከታል። እንዴት በራሱ ላይ ጦርነት ያውጃል። አዎ አንድ ነንና አንድ አይነት ነን ይለያያል ። አንድ ሆነን በልዩነታችን ለማደር ይህቺ ውብ ሀገር ትጠበን ይመስል። ሴራ የምንጎነጉነው ለየትኛው ቀሪ እድሜያችን ነው።እስኪ አስቡት ማነው ነገ ለመዋሉ እርግጠኛ የሆነ።ተፈቀደልን እንበል እስከ እርጅና ለመኖር ።

ስንት አመት ቀረን 30፣40፣ 50ወይም ስልሳ እና የምን ተንኮል ለየትኛው እድሜ።ኧረ ሼ ነው። ባይሆን በመላካምነት በፍቅር ፍሬው ያማረ ተግባር ከውነን ዘላለማዊ መሆን አይሻልም? በመልካም ምግባር ሞተንም በጥሩ እንነሳለን። ባደፈው ማህደራችን ግን ትውልድ ሁላ ያፍርብናለ። ሀገሬን የምትል ሆይ ሰረማኝ ሰውን ያለ ገደብ አፍቅር ጥላቻን በፍቅር አሸንፍ።

ፍቅር ጥላቻን ማጥፋት ይችላልና የተበረዘው ልብህ በፍቅር ሞልተህ፣ቀናነትን ተላመድና የኑሮን ጣዕም ማጣጣም ጀምር፡፡የእውነት ሰዎችን በእኩል ማየት ካልጀመርክ ስቃይ ውስጥ ነህ፡፡ ልብህ ውስጥ ጥላቻ ካለ ምንም ብሩህ ነገር መመልከት አያስችልህም፡፡ ጽልመት ነው፡፡ ጽልመት ደግሞ ምንም ተስፋ የለውምና ይጎመዝዛል፡፡ ያለ ተስፋ ህይወት ይቀፋል፡፡ ተስፋ ካጣህ ምኑን ኖርከው ወዳጄ፡፡