የለውጡ ነፀብራቆች

ይህ ወቅት ኢሕአዴግ ድክመቶቹን ገምግሞ  ሕገ- መንግሥታዊ ሥርዓቱን በአዲስ መንፈስ በመተግበር የተነቃቃውን  የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በማስቀጠልና  ወደተሸለ ደረጃ በማሸጋገር የሕዝቦችን  እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከምንግዜውም በላይ ቁርጥ አቋም ይዞ እየሠራ የሚገኝበት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሀገሪቱን መምራት ከጀመሩ ወዲህ ይህንኑ የለውጥ ጉዞ ሊያስቀጥሉ የሚችሉ ፍሬያማ ተግባሮችን  ሲያከናውኑ ከርመዋል፡፡ በመሆኑም አብዛኛዎቹ  የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለውጡን ተቋማዊ ለማድረግ ቀደም ሲል የነበሩባቸውን ድክመቶች በመፈተሸና በማረም ህብረተሰቡን የማገልገል እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡

ከሰሞኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኢንቨስትመንትና በተለያዩ የልማት ሥራዎች ስም ለበርካታ ዓመታት ታጥረው የተቀመጡ የመሬት ይዞታዎችን ወደ ከተማ አስተዳደሩ የመሬት ባንክ እንዲመለሱ ማድረጉ ለውጡ ተቋማዊ እየሆነ ስለመምጣቱ አንድ ማሳያ ነው፡፡ ኢንቨስትመንት በተገቢው መንገድ መመራት ከቻለ የሥራ አጥነት ችግርን የመቅረፍ፣ የከተሞችን ዕድገት የማፋጠንና  ምጣኔ ሀብትን  የማሳደግ ሚናው ከፍ ያለ ነው፡፡ በመዲናችን ብቻ በኢንቨስትመንት ስም እዛና እዚህ  እየታጠሩ ለረዥም ዓመታት የተቀመጡት ቦታዎች በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ወደ ሥራ ባለመግባታቸው ምክንያት  በከተማው ውበትና ንጽህናም ይሁን  በሥራ እድል ፈጠራና በኢኮኖሚው ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድረዋል፡፡

ህብረተሰቡ ቅሬታ ከሚያሰማባቸው ጉዳዮች  አንዱ የሆነው ይህ የማስፈጸም ችግር በከተማ አስተዳደሩ አዳዲስ ሹማምንት  እንዲህ ዓይነት ውሳኔ  ማግኘቱ  ለውጡ ወደ ተቋማት እየተሸጋገረ እንዳለና ተጨባጭ ጅምር እየታየ መሆኑን አስመስክሯል፡፡ የተወሰደው እርምጃ አሁንም ተዘናግተው ለተቀመጡ ባለሀብቶች  በውላቸው መሠረት በፍጥነት  ወደ ሥራ እንዲገቡ  የማነቃቂያ ደውል እንደሆነ ተነግሯል፡፡  ይህ አሠራር ቀደም ሲል እንደ ኦሮሚያ ባሉ ክልሎችም ተግባራዊ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን ሌሎችም ክልሎች ተመሳሳይ እርምጃ በመውሰድ የተጀመረውን ንቅናቄ ማገዝ ይኖርባቸዋል ፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተደረገው የሰነድ ምርመራ  ከሕግ አግባብ ውጭ ተይዘው የነበሩና ባለቤት የሌላቸው ቁጥራቸው 500 የሚደርስ  የቀበሌና የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ማግኘቱን የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት አስተዳደር ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙኃን አሳውቋል፡፡ አብዛኛዎቹ  በከተማዋ ውስጥ ያሉት የመንግሥት የመኖሪያ ቤቶች የከተማውን ነዋሪ የመኖሪያ ቤት ችግር በመቅረፍ አስተዋጽዖ እያበረከቱ እንዳሉ ባይካድም  የተወሰኑ መኖሪያ ቤቶች ግን ከሕግ አግባብ ውጭ በግለሰቦች እጅ እንደነበሩና እነዚህንም በማስመለስ ለችግረኞችና ለአቅመ ደካሞች የማስተላለፍ ሥራ እየተሠራ መሆኑ ተዘግቧል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በቀበሌና በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የሚስተዋለው  የተዝረከረከ አሠራር   ቀደም ሲል ህብረተሰቡ ሲያነሳቸው ከነበሩ የመልካም አስተዳደር  ችግሮች አንዱ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ በአዲስ አበባ አንዳንድ ቦታዎች ባለቤት አልባ የሆኑ ሕንጻዎች አሉ መባሉና የህንንም ለማረጋገጥ አስፈላጊው የኦዲት ሥራ እየተካሄደ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ክስተት ቀደም ሲል የነበረው የከተማ አስተዳደሩ አሠራር የቱን ያህል ክፍተት እንደነበረበት እና አሁን ያለው አመራር  ሁኔታውን ለማስተካከል ምን ያህል ጥልቀት እንደሄደ የሚያመላክት ነው፡፡ እንደ አብዛኛው ሰው አስተያየት ለውጡ በላይኛው መዋቅር ብቻ ተንጠልጥሎ መቅረቱ ማብቃት ይኖርበታል ፡፡  መንግሥት አስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ  ያሉትን አመራሮች በመፈተሽ ጠንካሮቹን በማበረታታት ደካሞቹን በመተካት ለህብረተሰቡ ጥያቄ  መልስ የመስጫ ጊዜው አሁን ነው፡፡ ዛሬም ድረስ ህብረተሰቡ የተሸከማቸውና ለውጡ ያላንገጫገጫቸው ጥቅመኞች፣ግለኞችና ሴረኞች በየተቋማቱ እንዳሉ መረሳት የለበትም ፡፡

አዲሱ አመራር  የአገሪቱን  ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ከወሰዳቸው እርምጃዎች አንዱ  በትርፍ ሥራ ላይ የተሰማሩ የመንግሥት ተቋማትን ወደ ግል ባለሀብቶች ለማዛወር ያቀደ መሆኑ ነው ፡፡ ይህ ውሳኔ ያስፈለገበት ምክንያት እንደ መብራት ኃይል፣ ቴሌ እና የመሳሰሉት አትራፊ የመንግሥት ድርጅቶች  ለህብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት የበለጠ  ተደራሽ ለማድረግና መንግሥት እራሱን  ከንግድ ዘርፍ አውጥቶ ለባለሀብቱ  የሥራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚውን  አስተማማኝና ዘላቂ ለመድረግ ከማለም ነው፡፡ 

ኢትዮጵያ የራሷንና የአካባቢዋን ገጽታ ለመቀየር በወሰደቻቸው ርምጃዎቿ እና ከተቀረው ዓለም ጋር በመሠረተችው ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷ አለም ትኩረት እንዲሰጣት ሆናለች፡፡ ወዳጆቿና ደጋፊዎቿም ከቀን ወደ ቀን ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ  ምቹ አጋጣሚ የፈጠረ ክስተት ነው፡፡  

በቅርቡ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥት የኤሌክትሪክ  ኃይል ለመግዛት መወሰኑ ተሰምቷል፡፡  ታዲያ ይህ ጉዳይ በተለያዩ ዓለምአቀፍ ሚዲያዎች መዘገቡ ኢትዮጵያ  የኃይል አቅርቦት ችግር  የሌለባት ፣ ሰላሟም የተጠበቀ እና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የሆነች አገር ተደርጋ እንድትታይ የሚያስችል ነው፡፡ ከተቀሩት አረብ አገራትም ጋር የተደረጉት የተለያዩ ስምምነቶች ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለው ጠንካራ የዲፐሎማሲ መርህና የለውጡ ነጸብራቅ ነው፡፡ 

ስመ-ጠሩ የኢትዮጵያ  አየር መንገድ የ2018 የአረቢያን ትራብል አዋርድ ‹‹ ምርጥ የአፍሪካ አየር መንገድ ›› በመሰኘት መሸለሙ ለአገሪቱ ገጽታ ግንባታ ከሚኖረው አስተዋጽዖ በዘለለ የወጪ እና ገቢ  ግብይት ሥርዓቱ  ያለውን አቅምና ቅልጥፍና ያሳየና የውጭ ባለ ሀብቱንም ጭምር ያነቃቃ መሆኑን የተለያዩ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ኢትዮጵያ መጪውን ምርጫ ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ከወዲሁ  ከሌሎች አገራት ልምድ ለመውሰድ እተንቀሳቀሰች ነው፡፡ ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩ የምርጫ ቁሳቁስን በመተው  በዲጂታል ሲስተም መጠቀም የሚያስችሉ ግብዓቶችንም ለማሟላት እንቅስቃሴ መጀመሩን የሀገሪቱ ምርጫ ቦርድ አሳውቋል፡፡ ይህም በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል መተማመን እንዲፈጠር የሚያስችል አንድ እርምጃ እንደሆነና   በአገሪቱ የተጀመረው ለውጥ በተቋማትም  እየተንጸባረቀ  ስለመሆኑ አመላካች ነው ሲሉ በርካታ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን ሰጥተውታል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይፋ ያደረጉትን የኢኮኖሚ ዘርፍ ፍላጎት ለማገዝ በማለም እና በኢትዮጵያ ያለውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማጥናት በሚስተር ጁሊዮ ኢስኮላኖ የተመራ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ አቅንቶ የጥናት ውጤቱን ለዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ፈንድ እንዳቀረበ ዘገባዎቹ አስረድተዋል፡፡ በዚህም በ2018/19 የኢትዮጵያ አጠቃላይ ዕድገት 8.5 እንደሆነ ተገምቷል፡፡ የጥናት ቡድኑ አባላት ከጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድና ከብሔራዊ ባንክ ገዢው ከዶክተር ይናገር ደሴ ጋር ተገናኝተው ውይይት አድርገዋል፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ አለመረጋጋት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና ባህላዊ የሆኑ የውጭ ንግድ ፈተናዎች የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እየተፈታተኑ ሳለ እንዲህ አይነት ለውጥ መታየቱ አበረታች መሆኑን  አስረድተዋል፡፡ በተያዘው የለውጥ ጉዞ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ  ሊያሳድጉ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ መሻሻሎች የታዩ ስለመሆኑ የተለያዩ የዓለም መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ይገኛሉ፡፡