ዩኒቨርሲቲዎችና የሰላም እሴት ግንባታ ጥረቶቻቸው

በአገሪቱ ታሪክ በተለያዩ ጊዚያት እያበቡ የመጡ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን በማስተናገድ   በኩል የትምህርት ተቋማትን  ያህል  የላቀ  ሚና  የተጫወት የለም  ቢባል ማጋነን አይሆንም ።   ስለ ዓለም የፖለቲካ ሁኔታና በአገሪቱ  ስለሚኖረው አንደምታ እንዲሁም  ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታን  ለመቀየርና ለውጥ ለማምጣት ከሌሎች የአገሪቱ ዜጎች በተለየ ሁኔታ ዘመናዊ ትምህርትን ለመቋደስ የበቁት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከፍተኛ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በማድረግ አስተዋጽኦ  ማበርከታቸውን  ታሪክ እራሱ  በገሃድ  ይመሰክራል ።

በተለይም  በ1960ዎቹ  በተካሄዱት  አጠቃላይ  የፖለቲካ  እንቅስቃሴዎች የያኔው የኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሲያካሄዱት የነበሩት የለውጥ  እንቅስቃሴዎች የአገሪቱ  መጻኢ ዕድልን  በመወስንና ገዠ የፖለቲካ  አስተሳሰቦች ላይ ተጽዕኖ  በመፍጠር  ታላቅ አሻራ  አኑረዋል ።

የአዲስ  አበባ ዩኒቨርስቲ ተራማጅ ተማሪዎች  በወቅቱ  የነበረውን የዘውዳዊ አገዛዝ  በግልጽና በጽኑ   በመቃወም በአገሪቱ   አብዮት  እንዲነሳና  በመላ አገሪቱ  እንዲቀጣጠል  ያበረከቱት አስተዋጽኦ  ምን ያህል  እንደነበር  ብዙ ጸሓፊያን  በከተቡት  ብዕራቸው ገልጸውታል ። 

በወቅቱ ተራማጅ አስተሳሰብን የያዘው ትውልድ በቁጭትና በቆራጥነት ተደራጅቶ  ለመታገል       የተነሳው ፣ ኢትዮጵያ  ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ተላቃ  በሰላምና  በዕድገት  ጎዳና እንድትራመድ  እንዲሁም  አዲስ  ዘመናዊ ሥርዓትን  መመሥረት  አስፈላጊ  መሆኑን በማመን ጭምር  ነበር ።

ሆኖም በኢትዮጵያ ከተማሪዎች የወቅቱ  ጥያቄዎችና ፍላጎት ውጭ ደርግ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ይበልጡኑ አምባገነናዊ ሥርዓትን በመዘርጋቱ  ምክንያት የዩኒቨርስቲ  ተማሪዎች   ቀድሞ እንደሚያነሱት የዴሞክራሲ ፣ የፍትህና የእኩልነት ጥያቄዎችን ለማንሳት ምንም አይነት  ዕድል አልነበራቸውም ።

ሆኖም የኢህአዴግ መንግሥት በ1983 ዓም ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላም የወቅቱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች  በ1985 ዓም  በተካሄደው  የኤርትራ ሪፍረንደም እንዲሁም  በ1997 ዓም በተካሄደው ምርጫ የወቅቱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከፍተኛ የሆነ የተቃውሞ ድምጻቸውን መንግሥት ላይ  ማሰማታቸው የሚታወቅ ሐቅ ነው ።

ባለፉት 13 ዓመታት በአገሪቱ  በተከናወነውና እየተከናወነ ባሉ የልማት ሥራዎች የዩኒቨርስቲ  ቁጥር  እጅጉን  እያደገ  መጥቶ  በአሁኑ ወቅት ከ40  በላይ  ዩኒቨርስቲዎች የተከፈቱ ሲሆን  የከፍተኛ ትምህርት  ተቋማት  ተማሪዎች  ቁጥርም  በመቶ ሺዎች  የሚቆጠር  ሆኗል ።

ባለፉት 40 ዓመታት የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች የዴሞክራሲ፣ የልማት፣ የእኩልነትና የፍትህ ጥያቄዎችን አንግበው አገራዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን በጋራ በማስነሳት ለመንግሥት ለውጥ እንደ ዋናኛ ምክንያት መሆናቸውን በፖለቲካው ዘርፍ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች የሚጠቅሱት ጉዳይ ነው ።

 ሆኖም  ካለፈው የአገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ታሪካዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በተለየ  ሁኔታ ግን ባለፉት  ሦስት ዓመታት በአገሪቱ  በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ   በተማሪዎች  መካከል ከማንነት ጋር በተያያዘ  የሚመነጩ  ግጭቶች  ቀስ በቀስ  እያቆጠቆጡና  እየጎሉ  መጥተው  ከፍተኛ ደረጃ ላይ  የደረሱበት ጊዜ ላይ እንገኛለን  ።

ኢትዮጵያ የተለያዩ ባህል፣ቋንቋና ማንነቶች ያሏቸው የተለያዩ የብሔሮችና ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚገኙባት አገር ብትሆንም አንዱ የሌላውን ባህል፣ቋንቋና ማንነት የመጋራትና የመተዋወቂያ መደበኛ ስልትና አሠራር ግን በአግባቡ ተግባራዊ  ሲደረግ አይታይም ፡፡

በተጨማሪም ባለፉት ዓመታት የማንነት ልዩነቶች ወይም የብዝሃነት ላይ ሰፊ ፖለቲካዊ  ሥራዎች ሲከናወኑ ቢቆይም ፤ በአንጻሩ ደግሞ ሕዝቦች ለዘመናት በታሪክ፣በባህልናበደም   ስለሚያስተሳስራቸው የሕዝቦች አንድነት አጀንዳ ላይ ግን ላይ ምንም አለመሠራቱ ለብሔር ተኮር ግጭቶች መባባስ በምክንያትነት ይጠቀሳል።

ለዚህም ነው በአገሪቱ እየተስፋፉ በሚገኙት የትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች  በአስደንጋጭ ሁኔታ አላስፈላጊ በሆኑ ግጭቶች  ውስጥ  በመግባት ህዝብና አገር ከሰጣቸው  አደራ የሚያፈነግጥ  ተግባር ላይ  ተሠማርተው የሚገኙት ። 

የተለያዩ የአገሪቱ ዩኒቨርሰቲዎች የሚገኙት የተለያዩ ባህል ፣ ቋንቋና ማንነት ያላቸው ተማሪዎች እርስ በራሳቸው በመተዋወቅና በመግባባት አገራዊ  አንድነትን ለመፍጠር የሚያስችሉ እድሎችን መፍጠር እንደሚገባቸውም እየተካሄዱ  ባሉት የተለያዩ የሰላም እሴት መገንቢያ የውይይት መድረኮች ጥሪ እየቀረበላቸው ነው ።

እንደ አብነት በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ሰሞኑን ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ  ተማሪዎች  የኬንያና የሱዳን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በመጋበዝ ጭምር ስለሰላም  የመከሩበት መድረግ እጅጉን መጎልበትና መቀጠል  ይኖርበታል ።

የሰላም  ምክክሩ መድረኩ  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የመከባባር እና የመቻቻል እሴቶችን ለማጎልበት ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ በምክከሩም ከጅማ፣አዲስ አበባ ፣ሀሮማያ ፣ከአንቦ፣ከባሕር ዳር እና ከጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የባህርዳር  ዩኒቨርስቲ  ሰላም እና ልማት ማዕከል ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባባር  ነው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት  የሰላም ምክክር   መድረክን  ያዘጋጀው   ።

ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው ከሚያገኙት እውቀት በተጨማሪ የመቻቻል እና አንዱ የሌላውን እሴት እና ባህልን ማዳበር፤አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ነገሮችን በውይይት የመፍታት ባህላቸውን ማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው፡፡

የሰላም እና ልማት ማዕከል ድርጅት አስተባባሪ አቶ ንጉሱ አንጌሳ ሰላም እና መቻቻል በትምህርት ተቋማት እንዲሰፍን ድርጅቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከአምስት ዓመት በፊት ፕሮጀክቱን መጀመሩን  አስታውቀዋል ፡፡ በተጨማሪም ድርጅቱ በስድስት ዩኒቨርሲቲዎች በሰላም እና እሴት ግንባታ ዙሪያ እየሰራ እንደሚገኝ በመድረኩ ገልጸዋል፡፡

ተማሪዎች የሁለተኛ  ደረጃን ትምህርትን ጨርሰው ዩኒቨርስቲ  በሚመርጡበት  ወቅት  ራቅ  ባሉና በማያውቁት አካባቢዎች በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የመማር ፍላጎት የሚያሳድሩት የማያውቁትን  ባህል ፣ ቋንቋና የአኗኗር  ዘይቤን ጭምር ለማወቅ በመሆኑ ይህን ፍላጎት ይበልጥ በማጠናከር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የአንዲት አገር ልጆች በመሆናቸው   ይበልጥ እንዲቀራረቡና አንድነት እንዲፈጥሩ  እንደ መልካም  አጋጣሚ መጠቀም ይገባል ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በአገር ደረጃ የፍቅርን፣ የይቅርታና መደመር  አስተሳሰቦች  ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተሰበከ  ባለበት ወቅት  ተማሪዎች  በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ወደ የተመደቡባቸው ዩኒቨርስቲዎች ሲደረሱ የአካባቢው ማህበረሰብ ና በነባር ተማሪዎች የትምህርት ተቋማት ደማቅና ፍቅር የተሞላበት አቀባባል መደረጉም በመልካምነት የሚጠቀስ ተግባር ነው  ።           

በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት በሀገሪቱ በነበረው ችግር ዩኒቨርስቲዎች አካባቢ ሲታይ በነበረው የሰላም መደፍረስ የተነሳ ተማሪዎች የትምህርት ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዳይጠቀሙ ከማድረጉም ባሻገር ተማሪዎች በብሄር ተለያይተው ግጭት ውስጥ  በመግባታቸው ትልቅ  ስጋት ፈጥሮ እንደነበረም ማስታወስ ይቻላል ፡፡

ቀደም ሲል የተከሰቱ ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱና ዩኒቨርስቲ  የሰላምና የፍቅር ቦታ እንዲሆን ሁሉም ዜጋ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በመወጣት ከዩኒቨርስቲ  የሚወጡ ተማሪዎች  የወደፊት ህይወት መሠረት የሚጣልባቸው ሥፍራዎች በመሆናቸው የፍቅር፣አንድነት እና መቻቻልን ባህል በተማሪዎቹ ውስጥ ለማስረጽ አሁን በመንግሥትና በተባባሪ አካላት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች መቀጠል አለባቸው ፡፡

በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች በ2009/10 የክረምት ዘመን የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ከሚኖሩበት ዞንና ክልል ወጥተው በሌሎች ክልሎች የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ  ላይ እንዲሠማሩ የተደረገበት መንገድም ሌላው ሊጠቀሱ ከሚገባቸው የበጎ ጅምር ሥራዎች  መካከል ይገኛል ።  

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በዘንድሮ ዓመት በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመደቡ አዳዲስ ተማሪዎች ከዚህ ቀደም የነበረው ችግር ይከሰታል ብለው እንዳይሰጉና ያለጭንቀት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በትምህርት ተቋማት አመራሮች፣  ተማሪዎች ህብረት አማካይነት ከየዲፓርትመንቱ ከተመረጡ ሌሎች  ተማሪዎች ጋር  በመቀናጀት ምክር እየሰጡ እንደሆነም ተናግሯል፡፡

ተማሪዎቹ በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው በዘር፣በቋንቋ እና በመሳሰሉት ልዩነት ሳይፈጥሩ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ በፍቅርና በመደጋገፍ ትምህርታቸውን በመረዳዳት እንዲማሩ የተለያዩ አካላት ለተማሪዎቹ መልዕክት ከማስተላለፋቸው በተጨማሪም በትምህርት ሂደቱና አገልግሎት አሠጣጡ ላይ ችግርን እንዳያጋጥም ያልተቋረጠ ክትትል እንደሚደረግም  በሚመለከታቸው አካላት ገለጻ ተደርጎላቸዋል  ።

ከዚህም በተጨማሪም ባለፈው ወር በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ዘጠኝ ዩኒቨርስቲዎች በአዳማ ከተማ  በመሰባሰብ   የሰላም ምክክር  ማድረጋቸው ይታወሳል ።  በኦሮሚያ ክልል  የሚገኙት  ዘጠኙ ዩኒቨርሰቲዎች የሰላም  ፎረም  በማቋቋም ጭምር  የሚንቀሳቀሱ ሲሆን  በአዳማ ውይይት  መድረክ ላይ  ከሰላም ፎረም አባላት ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የተማሪዎች ህብረት በተጨማሪ  የክልሉ የፀጥታና አስተዳደር ኃላፊዎች እንዲሁም ከሳይንስና  ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል ።

በተለያዩ  ዩኒቨርስቲዎች  የሚገኙ  የሰላም ፎረሞች ለዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ የሰላም መሣሪያ መሆናቸው  በማመን  ነው በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ዘጠኝ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የሰላም ፎረም አባላት የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ  ያካሄዱት ፡፡ ከሰላም ፎረም አባላትና የተማሪ ህብረት አባላት በተጨማሪ የክልሉ ዞኖች የፀጥታና አስተዳደር ኃላፊዎች፣ ከትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ እና የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በአዳማው መድረክ የግጭት መከላከልና አፈታት ላይ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥልጠና፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሰላም ፎረም ማቋቋሚያ መመሪያ፣ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ፎረም ምክር ቤት ተሞክሮ ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ዘጠኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲ የሰላም ፎረሞች የ2009 ዓ/ም ግማሽ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ተገምግሟል፡፡

በመድረኩም የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ፎረም ምክር ቤት ተሞክሮ ያቀረቡት የሰላም እሴት አማካሪ አቶ አባቡ መኮነን ዩኒቨርሲቲው በአርአያነት የሚጠቀሱ በርካታ ስራዎችን መስራቱንና በርካታ ውጤቶችም እንደተገኙ  ገልጸዋል ፡፡

በቀረበው ሰነድም የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የሰላም ፎረም ምክር ቤት አደረጃጀት፣ የፎረሙ ውስጣዊ አሠራር፣ ከሌሎች አደረጃጀቶች ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሰራር፣ የአባላትን ቁጥር ለማስፋት ፎረሙ የተጠቀመባቸው ስልቶች፣ የፎረሙ የግጭት መከላከልና አፈታት ስራዎች እና ተያያዥ ነጥቦች በአንኳር ይዘትነት ይዟል፡፡ 

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በአምስቱ ግቢዎች፣ 30ሺህ ተማሪዎችን የሚያስተምር ሲሆን የሰላም ፎረም ምክር ቤቱ በአምስቱም ግቢዎች ውስጥ ወንድ 2,328 ሴት 873 በድምሩ 3,201 አባላቶች እንዳሉትና ይህም በጠንካራ የተማሪዎች ተሳትፎ የሰላም እሴትን መገንባት  የሚያስችል  ተጠቃሽ  የሰላም ፎረም ምክር ቤት መቋቋሙን እንደሚያሳይ አቶ አባቡ ይገልጻሉ፡፡

18 አንቀጽ ያለው የሰላም የምክር ቤቱ የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ እየተመሩበት እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን የሰላም ፎረም ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚዎች የመረጃና ክትትል ጉዳይ ተጠሪ፣ ግጭት መከላከልና አፈታት ጉዳይ ተጠሪ፣ የብሄር ብሄረሰቦች ጉዳይ ተጠሪ፣ የዲሲፕሊን ክትትል ተጠሪና የሴቶች ጉዳይና ስርአተ ፆታ ተጠሪ የሚባሉ የሥራ ድርሻ ያላቸው መሆኑም መረዳት ተችሏል፡፡

በተጨማሪም በመድረኩ በዩኒቨርስቲዎች የግጭት መንስኤዎችን በመለየት በቅንጅት በመስራትና አስፈላጊ ቁጥጥር እና ክትትል  በማድረግ  በግጭት አመላካች ሁኔታዎች ላይ የዳሰሳ ጥናት ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ አለመግባባቶች ወደ ግጭት ሳያመሩ መከላከል እንደሚቻልም  በተግባር መታየቱ ተገልጿል ፡፡

በአገሪቱ  በሚገኙ የከፍተኛ  ትምህርት ተቋማት ውስጥ የተለያዩ እምነት ተከታዮች መካከል ሲፈጠር የነበረውን አለመግባባት ለመፍታትም  የሃይማኖት አባቶች የሚመሩት ስብሰባ ተዘጋጅቶ በማወያየት ተቻችለውና ተከባብረው እንዲኖሩ ማድረግ መቻሉንና ከተማሪዎች የሚቀርቡ የተለያዩ ቅሬታዎችን በማሰባሰብና በወቅቱ ምላሽ እንዲሠጡ የማድረግ ሥራዎች በዋናነት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ማወቅ ተችሏል ፡፡

የአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች አስተዳደሮች ለሰላም ቅድሚያ መሥጠት እንደሚገባቸውና  የክትትልና ድጋፍ ሥራ በማጠናከር ሁሉም አካላት በሰላም ጉዳይ ላይ የቅንጅት ሥራን ተግባራዊ እንዲያደረጉም  በአዳማው የሰላም ምክክር መድረክ ላይ  ጥሪ ቀርቧል   ፡፡