ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሃገሪቱን የመምራት ሃላፊነት ላይ ከመጡ ወዲህ በኢትዮጵያ በርካታ ለውጦች ተከስተዋል፡፡
የለውጥ ሂደት በባህሪው ፈተና የሚበዛበት በመሆኑ ኢትዮጵያ እና ለውጡ በ2011 የበጀት ዓመት በእጅጉ ተፈትነው ነበር፡፡
መንግስት በበጀት አመቱ ትኩረት በመስጠት ሊተገብራቸው ካቀዳቸው ተግባራት መካከል የሰላም፣ የጸጥታና የዴሞክራሲ ጉዳዮች፣ አኮኖሚ እና ዲፕሎማሲ ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ በውስጣቸውም በርካታ ዝርዝር ተግባራትን ያካተቱ ነበሩ፡፡
ባለፉት ሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ የተከሰተው አለመረጋጋት እና ከለውጡ ጋር ተያይዞ የተፈጠሩት ሁኔታዎች ድምር በበጀት ዓመቱ የሃገሪቱን ፈተናዎች በማብዛታቸው መንግስት ተረጋግቶ እቅዱን ለመተግበር ምቹ ሁኔታን ባይፈጥሩለትም እንኳ ወሳኝ እና አስፈላጊ ስኬቶች መመዝገባቸው አልቀረም፡፡
ካለፈው ዓመት አንስቶ በርካታ የሪፎርም ስራዎች በመሰራት ላይ ሲሆኑ ይህንን እውን ለማድረግ በ2011 የበጀት ዓመት የመንግስት ዋና ዋና እቅዶች የነበሩት የዴሞክራሲውን አውድ የማስፋት፣ ሰላምና መረጋጋትን የማስፈን፣ ኢኮኖሚውን የማነቃቃትና ለውጡን የሚሸከሙ ተቋማትን መገንባት ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የ2011 በጀት አመት የመንግስትን የስራ አፈጻጸም ሪፖርትና አሁን ያለው አጠቃላይ ሃገራዊ ሁኔታ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡ ከምክር ቤት አባላቱ ለቀሩላቸው ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ይህ ጽሁፍም የ2011 በጀት ዓመት የመንግስት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ተንተርሶ፣ የተመዘገቡ ስኬቶችን፣ ያጋጠሙ ፈተናዎችን እና ፈተናዎቹን ለማለፍ የተደረጉ ጥረቶችን፣ ቀጣይ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫን እንዲሁም መሰል ጉዳዮችን ይዳስሳል፡፡
ከበጀት ዓመቱ ቀድሞ የነበሩት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ኢትዮጵያ በህዝባዊ ተቃውሞዎች ስትናወጥ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የመንግስት ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅሞች ተዳክመው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከለውጡ በኋላም ካለፉት ዓመታት የዞሩ ፈተናዎች የተከሰቱ ሲሆን የእነዚህ ፈተናዎች ውጤትም በዜጎች ላይ ሞት፣ ጉዳትና መፈናቀልን አስከትለዋል፣ በመሰረተ ልማት ላይ ጥፋትን አድርሰዋል፣ ሃገራዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን አስተጓጉለዋል፡፡
አክራሪ ብሄርተኝነት፣ ግጭትና የዜጎች መፈናቀል፣ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች የሚፈጥሯቸው ነውጦች፣ የወሰን የማንነት እና የአደረጃጀት ጥያቀዎችን ተገን አድርገው የሚየሚከሰቱ ችግሮች፣ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ የሚዲያ ጽንፈኝነት እና ከሕዝብ ሰላም በተቃራኒው መቆም፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ግጭት መግባት፣ የከተማ ውስጥ የተደራጁ ወንጀለኞች፣ የኢኮኖሚ አሻጥሮች እና ህገ ወጥ ንግድ የበጀት አመቱ ዋና ዋና ፈተናዎች እንደነበሩ ጠ/ሚ አብይ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡
እንደ መንግስት ገለጻ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ሲሆን በዚህም ለህዝብ ተቃውሞ ምክንያት የሆኑ አመራሮችን የመቀየር፣ አሰራሮችን የማስተካከል፣ ተቋማዊ መዋቅሮችን የመቀየር የማስፋት እና የመገንባት እርምጃዎች ከለውጡ ማግስት አንስቶ በመወሰድ ላይ ናቸው፡፡
በዚህ ረገድ ሶስት ዋና ዋና ተግባራት መንግስት በማከናወን ላይ ሲሆን ተቋማትን ሪፎርም የማድረግ ተግባር እና ለዜጎች ችግር እና ግጭት ምክንያ የሆኑ ጉዳዮችን በዘላቂነት መፍታት የመንግስት የመጀርያው ተግባር እንደነበር ደዶ/ር አብይ አስረድተዋል፡፡
በበጀት አመቱ በሁሉም የደህንነት እና የጸጥታ ተቋማት የህግ፣ የአሰራር ስርዓትና የአመራር ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ ማሻሻያ እየተደረገባቸው ከሚገኙ ተቋማት መካከል የሃገር መከላከያ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ፣ የፌዴራል ፖሊስና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ተጠቃሾች ናቸው፡፡
የዜጎች ሰላምን ለማረጋገጥ የተከናወነው የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራ ሁለተኛው ተግባር ሲሆን በዚህም የፍትህ አካላትን ለማሻሻልና ለማጠናከር ከተሰሩ ስራዎች በተጨማሪ አጥፊዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እንደተሞከረ በሪፖርቱ ተካቷል፡፡
ከእርምጃዎቹ መካከል በሰብዓዊ መብት ጥሰት እና በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የስራ ሃላፊዎች እና ግብረአበሮቻቸው በህግ እንዲጠየቁ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡ ለአብነትም ከፍተኛ የሽብር ተግባር ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ 48 የሽብር ቡድን አባላትን በቁጥጥር በማዋል ጥቃቱን ማክሸፍ ተችሏል፡፡
በተጨማሪም ብሄርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችን በመቀስቀስ እና ጥቃቶች በማድረስ እንዲሁም ዜጎችን በማፈናቀል ወንጀሎች ውስጥ የተሳተፉ 799 ተጠርጣሪ አመራሮች እና የጸጥታ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡
የሃገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት በሚያስከትሉ ወንጀሎች ላይ ከተሰማሩ ተጠርጣሪ የባንክ እና የኢትዮ-ቴሌኮም ሰራተኞች መካከል 34ቱ ተይዘው ለህግ መቅረባቸውን መንግስት በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
የህግ የበላይነትን ለማስፈን በህዝብ ዘንድ ተቀባይት ያላቸውን ህጎች ማዘጋጀትና ነባሮቹን መከለስ አስፈላጊ በመሆኑ መንግስት ከዴሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብት ጋር የማይሄዱ ህግጋትን የማሻሻል ስራ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ረገድ የሲቪል ማህበረሰብ አዋጅ እና የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጆች ተሻሽለው የጸደቁ ሲሆን የጸረ ሽብር አዋጅ፣ የማረሚያ ቤቶች አዋጅ፣ የምርጫ ህግ አዋጅ እና ሌሎች በርካታ ህግጋት የማሻሻያ ስራ እየተሰራባቸው ይገኛል፡፡
የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት የ2011 በጀት ዓመት መንግስት በትኩረት የሰራበት ዘርፍ ሲሆን በውጤቱም ከ10 የሚበልጡ የታጠቁ ሃይሎች ወደ ሃገር እንዲገቡ ሆኗል፡፡
ከ45 ሺህ በላይ ዜጎች የምህረት አዋጅ ተጠቃሚ መሆን ሲችሉ ከ100 ሺህ በላይ እስረኞች ከሁሉም ክልሎች ተፈተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙ ፈታኝ ጉዳዮች አንዱ የዜጎች መፈናቀል ነው፡፡ ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ የመኖሪያ ስፍራቸው ለመመለስ እና ለማቋቋም መንግስት በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ያቀረቡት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ሁለት አይነት መፈናቀሎችን ውዝፍ እና ከለውጡ በኋላ የተከሰቱ መፈናቀሎችን ለመፍታት ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ከለውጡ በፊት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ከለውጡ በኋላ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን፣ በድምሩ 2 ነጥብ 3 በላይ ሚሊዮን ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 400 ሺህ የሚሆኑት በድርቅ እና የጎርፍ ችግሮች ሳቢያ የተፈናቀሉ ናቸው፡፡
በፌዴራል እና በክልል አካላት የጋራ ጥረት ከእነዚህ ተፈናቃዮች መካከል 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንደተመለሱ እና ቀሪዎቹን በቅርብ ለመመለስ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
የዜጎችን መፈናቀል በዘላቂነት ለማስቀረት መንግስት ግጭት የማስቆም እና ዘላቂ ሰላም የማስፈን ስራ በመስራት ላይ ነው፡፡
የበጀት ዓመቱ ሌላኛው የመንግስት ዕቅድ የኢኮኖሚው ዘርፍ ሲሆን የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በአጠቃላይ የፋይናንስ ዘርፉን በተለይ ወደ ቀውስ እንዳይገባ በመከላከል እንዲያገግም ማድረግ ነበር፡፡
በተጨማሪም ጥቅል ፍላጎትን መሰረት ካደረገ የኢኮኖሚ እድገት እንቅስቃሴ ገበያ ላይ ወደ ተመሰረተ ለአቅርቦት ወደሚያደላ የአኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲሸጋገር ማድረግ ሁለተኛው የዘርፉ ዕቅድ ነበር፡፡
በዚህም መሰረት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸምን በተመለከተ ሃገሪቱ በተከተለችው የልማት ፋይናንስ ሞዴል ችግርና ባለፉት ሶስት አመታት ባጋጠሟት ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ችግሮች ሳቢያ የኢኮኖሚው የእድገት ምጣኔ ከዓመት ወደ ዓመት ዝቅ እንዲል ሆኗል፡፡
የ11 ወራት የሸቀጦች ንግድ አፈጻጸም ከእቅዱ አንጻር ዝቅተኛ ከመሆኑ በስተቀር የኢኮኖሚው አጠቃላይ የፍላጎትና አቅርቦት እንቅስቃሴ ማገገሙን መረጃዎች እንደሚያመለክቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ጠቁመዋል፡፡
የኢኮኖሚ ጠቋሚዎች እንደሚያመለክቱት በዘንድሮው በጀት ዓመት የሃገሪቱ ኢኮኖሚ 9 ነጥብ 2 በመቶ እድገት ያስመዘግባል፡፡
የስራ እድል ፈጠራን በተመለከተም በኢትዮጵያ የስራአጡ ቁጥር ከ11 ሚሊዮን በላይ ሲሆን በተጨማሪም በየአመቱ ከ2 ሚሊዮን ያላነሰ የሰው ሃይል ወደ ስራ ፈላጊው ጎራ እንደሚገባ የመንግስት ሪፖርት ያሳያል፡፡ በበጀት አመቱ ችግሩን ለመቅረፍ ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ተግባር የገባ ሲሆን በ2011 በጀት ዓመት ለ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዘጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ እስከ ቀጣዩ በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስም ባጠቃላይ ለ3 ሚሊዮን ዜጎች በሃገር ውስጥና ከሃገር ውጭ የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ ይገኛል፡፡
የመንግስት ገቢና ወጪ በጀት አፈጻጸምን በተመለከተ በበጀት ዓመቱ 11 ወራት 178 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ10 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ይህ አሃዝ ቢያንስ 189 ቢሊዮን ብር ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፡፡
የውጭ ንግድ አፈጻጸምና አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በተመለከተም በበጀት ዓመቱ 10 ወራት ከአገልግሎት ወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ የ25 በመቶ እድገት በማስመዝገቡ ከዘርፉና ከሸቀጦች ንግድ የተገኘው የውጭ ምዛሪ መጠን የ10 ነጥብ 5 በመቶ እድገት እንዲያሳይ አስችሏል፡፡
በተጨማሪም ከሌሎች የውጭ ምንዛሪ ምንጮች 19 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህም ባለፈው አመት ከተገኘው የውጭ ምንዛሪ በ20 ከመቶ እድገት አሳይቷል፡፡
በፋይናንስ ዘርፍ በ10 ወራት ሁሉም ባንኮች ያሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ ከአምናው በ22 በመቶ ያደገ ሲሆን ሁሉም ባንኮች ያሰራጩት አዲስ ብድር በ35 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ ከዚህ ብድር ውስጥ የግል ዘርፍ (ማህበራትን ጨምሮ) ድርሻ 65 በመቶ ሲሆን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በ54 በመቶ ከፍ ያለ ነው፡፡
የዋጋ ሁኔታን በተመለከተ በበጀት አመቱ ባለፈው የበጀት አመት መጨረሻ የተመዘገበውን 16 ነጥብ 8 በመቶ የዋጋ ግሽበት ከ10 በመቶ በታች ለማውረድ በሁሉም አቅጣጫ ታቅዶ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት በአብዛኛዎቹ የበጀት አመቱ ወራት የዋጋ ግሽበቱ ከ12 በመቶ በታች እንዲሆን የተደረገ ሲሆን ይህ ቁጥር በግንቦት ወር ግን ወደ 16 ነጥብ 2 በመቶ አሻቅቧል፡፡
በበጀት አመቱ ግዙፍ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዘወር ስራ ከመንግስት እቅዶች መካከል አንዱ ሲሆን ወደ ግል የሚተላለፉ የልማት ድርጅቶች ለታሰበለት አላማ እንዲዉሉ የማዘጋጀት ስራ ተጀምሯል፡፡ ወደ ግል የማዛወሩ ሂደት በቅደም ተከተል እንዲሆን ተደርጎ በመጀመሪያው ረድፍ ቴሌኮሚዩኒኬሽን እና የስኳር ልማት ፋብሪካዎች ተቀምጠዋል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የሃይል ማመንጫዎች፣ የባቡር ኮርፖሬሽን እና የሎጀስቲክ ተቋማት የተቀመጡ ሲሆን በመጨረሻው ረድፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተካተዋል፡፡
የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ እቅድ አፈጻጸምን በተመለከተ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ዋነኛ ማጠንጠኛ ዜጎቿ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሪፖርታቸው አስቀምጠዋል፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ገለጻ የውጭ ግንኙነት እንቅስቃሴው የሃገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ፣ ዓለም አቀፍና ክልላዊ ሁኔታን በሚያንጸባቅ መልኩ የዜጎቻችንን ክብር፣ መብት እና ጥቅምን በሚያስከብር መልኩ ተከልሷል፡፡
በየክፍለ አለማቱ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በማጠናከር የዜጎችን ደህንነት እና ክብር ለማስጠበቅ ጥረት መደረጉን አስረድተዋል፡፡ በዚህም መሰረት በተለያዩ ሀገራ የታሰሩ ከ 15 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ተፈተው ወደ ሃገራቸው ገብተዋል ብለዋል፡፡ በተለያየ ምክንያት የስራ ውላቸው የተቋረጠ ከ76 ሺህ በላይ ዜጎች ያለ እንግልት ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን አስታውሰዋል፡፡
የውጭ ግንኙነት ጥረት ከዜጎች በመቀጠል በዋናነት በጎረቤት ሃገራት ላይ ያተኮረ እና ሁሉንም ጎረቤት ሃገራት ያማከለ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡
በተለይ ከኤርትራ ጋር የነበረንን የጦርነት ጥላ ያጠላበት ድባብ ወደ ሰላማዊ አየር ለመቀየር ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል፡፡ በኬንያ እና ሶማሊያ፣ በጂቡቲ እና በኤርትራ፣ በደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች መካከል ሰላምን ለመፍጠር የድርሻችንን እየተወጣን ነው ብለው አሁን ደግሞ በሱዳን ሰላምን ለማምጠት ቀጣናዊ የመሪነት ሚናችንን እየተወጣን ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በሌላም በኩል ለክፍለ አህጉራዊ እና አህጉራዊ ሰላም እየተሰራ ሲሆን በተለይ በቀይ ባህር ላይ ክፍለ አህጉራዊ የጋራ የቀይ ባህር አካባቢ ፖሊስ እንዲኖር ጥረቶች መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ዋነኛ የንግድ መተላለፊያ በሆነው ቀይ ባህር የባህር ላይ ውንብድና፣ ሽብርተኝነት እና የታጠቁ ሃይሎች እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር የባህር ሃይል ማቋቋም አስፈላጊ በመሆኑ የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡
በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ረገድ ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ኢትዮጵያ ከተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት ለኢኮኖሚ ማሻሻያ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንዳገኘች ይታወሳል፡፡