51ኛውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና መጋቢት 19 ይጀመራል

መጋቢት 16/2014 (ዋልታ) 51ኛውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከመጋቢት 19 ጀምሮ ለ6 ተከታታይ ቀናት በሐዋሳ ከተማ እንደሚካሄድም ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሻምፒዮናውን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ከ1963 ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኘው ይህ ሻምፒዮና እንደ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ በርካታ ስመጥር አትሌቶችን ማፍራት የቻለ ሲሆን ተተኪ አትሌቶችን ከማፍራት አንፃር ጉልህ ሚና ያለው ውድድር ነው ተብሏል፡፡
በዘንድሮው ውድድር 7 ክልሎች እና 2 ከተማ አስተዳደሮች የሚሳተፉበት ሲሆን በሁለቱም ፆታዎች በአጠቃላይ 1 ሺሕ 33 ተወዳዳሪዎች እንደሚሳተፉ ተጠቁሟል፡፡
በሻምፒዮናው አለምዘርፍ የኃላ፣ ሙክታር እድሪስን ጨምሮ ሌሎች አትሌቶች እንደሚሳተፉ እና ውጤት ለሚያስመዘግቡ አትሌቶችም በአጠቃላይ 541 ሺሕ ብር የገንዝብ ሽልማት መዘጋጀቱ በመግለጫው ተነስቷል።
ለውድድሩም ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መደረጉ ተጠቁሟል፡፡
በደግነት መኩሪያ