6ኛው የኢትዮጵያ ዊልቼር ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና ውድድር ተጠናቀቀ

በኢትዮጵያ የዊልቼር ቅርጫት ኳስ አሶሴሽን አዘጋጅነት ከመጋቢት 7 እስከ 12 በባህርዳር ከተማ በድምቀት ሲካሄድ የሰነበተው 6ኛው የኢትዮጵያ ዊልቼር ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና ውድድር ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል።

ዛሬ በማጠቃለያው በተደረገ ውድድር በሴቶች አማራ ክልል አዲስ አበባን 6 ለ 3 ሲያሸንፍ፤ በተመሳሳይ በወንዶች አማራ አዲስ አበባን 25 ለ 15 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡

በዚሁ መሠረት የአማራ ክልል በወንዶችና በሴቶች አሸናፊ በመሆን የወርቅ ሜዳልያና የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን ፤ አዲስ አበባ የብር ሜዳልያ፤  አሮሚያ ደግሞ የነሐስ ሜዳልያ በሁለቱም ፆታ ወስደዋል።

የአማራ ክልል የዊልቼር ቅርጫት ኳስ አሰልጣኞች  በሀይሉ አዲሱ እና ጥላሁን አያሌው ኮኮብ አሰልጣኝ በመሆን ተመርጠዋል።

በተመሳሳይ በሴቶች ውብርስት ጌትነት ከአዲስ አበባ በወንዶች ፍቃዱ ከድሬዳዋ ኮከብ ተጨዋች ሆነዋል።

ኦሮሚያ ክልል የፀባይ ዋንጫ እንዲሁም ሐረሪ ክልል ደግሞ የልዩ ዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል።

በውድድሩ ከአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ እና ሀረሪ ክልሎች እንዲሁም ከድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ከ160 በላይ የልዑካን ቡድን አባላት ተሳታፊ መሆናቸውን ከኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡