7 አገራትን ወክለው በኮፓ አሜሪካ የሚፋለሙት ሰባት አርጀንቲናዊያን አሰልጣኞች


ሰኔ 9/2016 (አዲስ ዋልታ) ከሰኔ 13 እስከ ሐምሌ 7 በሚካሄደው የኮፓ አሜሪካ እግር ኳስ ውድድር ሰባት ትውልደ አርጀንቲናዊያን አሰልጣኞች የሰባት አገራትን ብሔራዊ ቡድኖች ይዘው ይሳተፋሉ።

በዚህም መሰረት የዓለም ዋንጫ አሸናፊው የአርጀንቲናው አሰልጣኝ ሊዮኔል ስካሎኒ አገራቸውን አርጀንቲናን፣ ፈርናንዶ ባቲስታ ቬንዙዌላን፣ ማርሴሎ ቤይሳ ኡራጓይን፣ ዳንኤል ጋርኔሮ ፓራጓይን፣ ጉስታቮ አልፋሮ ኮስታሪካን፣ ሪካርዶ ጋሪቻ ቺሊን እና ኔስቶር ሎሬንዞ የኮሎምቢያ ብሔራዊ ቡድኖችን ይዘው ይቀርባሉ።

በአሜሪካ አዘጋጅነት በሚካሄደው የኮፓ አሜሪካ ውድድር ከሰሜን፣ ከደቡብና ከማዕከላዊ አሜሪካ እንዲሁም ከካረቢያን ደሴቶች የሚወከሉ 16 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ።

በዚህ ውድድር ሌላው አስገራሚው አጋጣሚ በውድድሩ ሶስቱ አርጀንቲናዊያን አሰልጣኞች የሚመሯቸው ብሔራዊ ቡድኖች በምድብ አራት አንድ ላይ መመደባቸው ነው።

በዚህ ምድብ በአርጀንቲናዊያኑ አሰልጣኞች የሚመሩት ኮሎምቢያ፣ ፓራጓይ፣ ኮስታሪካ በቦሪቫል ጁኒዬር ከምትመራዋ ብራዚል ጋር ተመድበዋል።

በዚህም ዳንኤል ጋርኔሮ፣ ጉስታቮ አልፋሮ እና ኔስቶር ሎሬንዞ የሌላ አገሮችን ብሔራዊ ቡድኖች ይዘው እርስ በርሳቸው የሚፋለሙበት መድረክ እንደሚሆን ዳዝን የተባለ ስፖርታዊ መረጃዎችን የሚያቀርብ ድረገጽ ዘግቧል።

በሌላ በኩል በምድብ አንድ ቺሊን የሚያሰለጥኑት ሪካርዶ ጋሬቻ በሊዮኔል ስካሎኔ የምትሰለጥነው አገራቸውን በተቃራኒ ይገጥማሉ።

በውድድሩ አርጀንቲና፣ ፔሩ፣ ቺሊና ካናዳ በምድብ አንድ፤ ሜክሲኮ፣ ኢኳዶር፣ ቬንዙዌላና ጃማይካ በምድብ ሁለት፤ አሜሪካ፣ ኡራጓይ፣ ፓናማና ቦሊቪያ ደግሞ በምድብ ሶስት ተደልድለዋል።