ሀገሬ-ሶፍ ኡመር ዋሻ – የተፈጥሮ ጥበብ ማህደር!

ሶፍ ኡመር ዋሻ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ባሌ ዞን የሚገኘው አስደናቂ የተፈጥሮ ዋሻና ድንቅ የመስህብ ሥፍራ ነው። ከባህር ጠለል በላይ 1 ሺሕ 200 እስከ 1 ሺሕ 385 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ ሲሆን ዙሪያው በተዋቡ የተፈጥሮ ፀጋዎች የተከበበ ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻ ነው።

የዋሻው ውሰጥ ለውስጥ መንገድ ርዝማኔው 15 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር ሲሆን የጎን ስፋቱ ደግሞ 1ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ነው። የዋሻው መግቢያ በር ጉለንተናየው መኩ ሲባል መውጫው ሁልቃ ይባላል፡፡

ከመግቢያው እስከ መውጫው ድረስ ከሁለት እስከ ሶስት ስዓት ጉዞ እንደሚጠይቅ የሚነገርለት ይህ ሚስጥራዊው ዋሻ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ በርዝመቱ ቀዳሚ ነው። በአለም 306ኛ ደረጃን እንደያዘም ነው የሚነገረው።

ይህ አስደማሚው የተፈጥሮ ዋሻ ከአዲስ አበባ 532 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

ሌላው ተጨማሪ የዋሻው ድምቀት ከባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ መነሻውን ያደረገውና ወደ መቶ አሥር ኪሎ ሜትር ተጉዞ ዋሻውን የምድር ውስጥ መሻገሪያ መንገድ አድርጎ የሚያቋርጠው የዌብ ወንዝ ነው።

ዋሻውን አቋርጦ የሚያልፈው ይህ ወንዝ ውስጥ ለውስጥ ሰባት ጊዜ የሚተጣጠፍበት ቦታዎች ያሉት ሲሆን በዋሻው የሚጓዝ ሰውም ሰባት ጊዜ ወንዙን መሻገር ይጠበቅበታል።

ታዲያ ይህን የዋሻ ውስጥ ወንዝ ሲሻገሩ አምስት ጊዜ በእግርዎ ሁለቱን በዋና መሆኑ ድርብርብ አስደናቂነቱን ያጎላዋል። ለወደፊቱ ደግሞ የዋሻ ውስጥ ጀልባ ኖሮት ድንቅ መስህብነቱን እንደሚያልቅ ያሳብቃል።

ይህ ተፈጥሮ ያበጃጀው ሚስጥራው ዋሻ ውስጣዊ ውበቱና የተፈጥሮአዊ ሥነ ህንፃ ጥበብ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚገዛና የሚያስደምም ነው።

ከአምስት ሚሊዮን ዓመት በፊት እንደነበረ የሚነገርለት የተፈጥሮ ዋሻው ስያሜውን ያገኘው ከ1000 ዓመት በፊት ሶፍ ኡመር ከሚባሉ የሀይማኖት አባት ነው። ሼክ ሶፍ ኡመር በዋሻው ለብዙ ዓመታት እንደኖሩና ሀይማኖታዊ ትምህርት ያስተምሩ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።

ታዲያ የዚህን አስደናቂና ምስጥራዊውን የተፈጥሮ ዋሻ ዝና የሰሙት ሥፍራውን ለመጎብኘት ይተማሉ። ቀድሞ የሚያውቁትም ደጋግመው ለመጎብኘት በናፍቆት ይመላለሳሉ።

ይህ የጎብኚዎችን ቀልብ በመግዛት የሚታወቀው የቱሪዝም መዳረሻ ደረጃውን የጠበቀ መሠረተ ልማት አለመሟላት ተግዳሮት ሆኖ እንደቆየ ይነሳል።

በአሁኑ ወቅት ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ እና ጎብኚዎች እንደልብ እንዲመላለሱ ዕድል የሚፈጥር ብሎም አስደናቂው የሶፍ ኡመር ዋሻ እንደ ድንቅ መስህብነቱ ለሀገር የሚጠቅበትን ድርሻ እንዲያበርክት የሚያስችል የማልማት ሥራ እየተካሄደ ይገኛል።

የበጀት ምንጩ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጻፉት የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ ገቢ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጽሐፋ ምረቃ ወቅት ከመደመር ትውልድ መፅሐፍ ሽያጭ የሚገኘውን ገቢ ክልሎች ለቱሪዝም መዳረሻ ልማት፣ ለቅርስ ጥገና እና ለትምህርት ቤቶች ግንባታ እንዲያውሉ በማበርከት አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ይታወሳል፡፡

በዚህም የተፈጥሮ ጥበብ ማህደር የሆነውን የሶፍ ኡመር ዋሻ ተፈጥሮአዊ ይዘቱን ሳይለቅ የማደስ፣ መንገድና የማረፊያ ሎጆች የመገንባትና በአጠቃላይ ለቱሪዝም መዳረሻው አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ የመሠረተ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑበት ይገኛል፡፡

የማልማት ሥራዎች ሲጠናቀቁም በድንቅ መስህብነቱ በመላቅ የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም ሀገራችን ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ እንደሚያሳድግ ይጠበቃል፡፡

በውብ የተፈጥሮ ገጸ በረከት የታደለውን የባሌን አከባቢ እና የሶፍ ኡመር ዋሻን ይጎብኙ አገርዎን ይወቁ!!

በሠራዊት ሸሎ