ሀገሬ – “ነሞ” – የቦሮ- ሺናሻ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት

የሽናሻ አባቶች የሀገር በቀል እውቀታቸውን ተጠቅመው በማህበራዊ ግንኙነት ውስጥ ግጭቶች እንዳይከሰቱ የሚከላከሉበት እና ግጭቶች ሲከሰቱም እርቅ የሚያወርዱበት የዳበረ የግጭት አፈታት ዘዴ አላቸው። ይህ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት “ነሞ” ይባላል።

ሽናሾች አስቀድመው ግጭት እንዳይከሰት “ኔሞን ኔቶራ” ወይም በህግ አምላክ በማለት ወንጀልን እንደሚከላከሉ ይጠቀሳል።

አንድ ሰው ህግ እንዳይጥስ አስቀድሞ “ኔሞን ኔቶራ” ከተባለ ህጉን አክብሮ ከጥፋት ይታቀባል።

“ነሞ” ሽናሻዎች በማህበራዊ ግኑኝነት ውስጥ የሚያጋጥሙ አለመግባባትና ችግሮችን አስቀድመው የሚከላከሉበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በባህል የሚዳኝበት ባህላዊ የህግ ስርዓትም አለው።

ሽናሻዎች የማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን በ”ኔሞ” ታግዘው እንደሚፈጽሙም ይነገራል።

ከ”ኔሞ” የባህላዊ ግጭት አፈታት ሥርዓት አንዱ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ነው። ይህ የባህላዊ ዳኝነት የተለያዩ የፍርድ አሰጣጥ ሂደቶችን ይከተላል፡፡ ስርዓቱ አራት ደርጃዎች እንዳሉት መረጃዎች ያመለክታሉ ።

እነዚህ አራት የዳኝነት ደረጃዎች “ቡራ” “ኔማ” “ፄራ” እና “ፋላ”በመባል ይታወቃሉ።

“ቡራ” የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ሲሆን አንድ ሽማግሌ ብቻውን ሆኖ የሚፈርድበት ባህላዊ ችሎት ነው።

የ‘’ቡራ” የመጀመሪያ ደረጃ የፍርድ ሂደት የሚዳኙ ባህላዊ ዳኞች ግጭቶችን በፍትሃዊነት በመፍታት የሚታወቁና በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው እና የብሄረሰቡን ባህላዊ እሴቶችን ጠንቅቀው የሚያውቁ መሆን አለባቸው።

የ”ቡራ” ችሎት የመጀመሪያ ደረጃ ግጭት መፍቻ ሲሆን በቅርብ ግዜ ውስጥ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በማየት ውሳኔ ይሰጣል።

በዚህ የፍርድ አሰጣጥ ሂደት ዳኛው ጉዳዩን መፍታት ካልቻለ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ፍርድ እንዲቀጥል ይደረጋል::

ሁለተኛው ደረጃ ባህላዊ ዳኝነት “ ኔማ” ሲሆን ሶስት ሽማግሌዎች በጋራ ሆነውፍርድ የሚሰጡበት ነው። በመጀመሪያው ደረጃ ፍርድ  በ “ቡራ” ዳኝነት ቅር የተሰኘ ሰው ካለም ይግባኝ የሚቀርብበት  ነው “ነማ”። በዚህም ፍርድ የሚሰጡ ዳኞች ግጭት ሲፈጠር በእውነት በመፍታት እና በማስታረቅ የሚታወቁ ናቸው ።

ሦስተኛው ደረጀ ዳኝነት ‹‹ፄራ›› ይባላል። በዚህ ዳኝነት “ኔማ” ችሎት መፍታት ያልቻለው ጉዳይ በጥልቀት የሚታይበትና የሚፈታበት ነው።

ይህ ባህላዊ ችሎት በአንድ ባህላዊ ዳኛ የሚመራ እና በይግባኝ ሰሚ ችሎት “ኔማ”ለመፍታት ያልተቻሉና ከአቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮች ወደ ‘’ፄራ” የፍርድ ችሎት ተሸጋግሮ ቅሬታዎች የሚፈቱበት ሂደት ነው። በዚህ የፍርድ አሰጣጥ ደረጃ ላይ ፍትህ የሚሹ ሁለቱም ወገኖች “ፄራ” የመምረጥ መብት አላቸው::

በ”ፄራ” የፍርድ ችሎት የሚዳኙት ሽማግሌዎች ከአባት፣ ከአያት፣ ከቅድመ አያት ባገኙት የግጭት አፈታት ዕውቀት የሚታወቁ ፣ ወንጀል ነክ ጉዳዮችን በማየት ልምድ ያዳበሩ ናቸው።

አራተኛው እና የመጨረሻው ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት “ፋላ” ይባላል። ከፍተኛ የዳኝነት አካል ነው፡፡ በሽናሻ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት በ”ፋላ” የተሰጠው የፍርድ ውሳኔ የመጨረሻ እና አስገዳጅ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

እነዚህ በሀገር በቀል ዕውቀት የተቃኙና በሽናሻ አባቶች ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፋ የመጡ የባህላዊ የዳኝነት እሴቶች ናቸው። ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓቱ ባለመግባባት የሚፈጠሩ ችግሮችን የመፍታት ሚና ያለውና ችግሮች እንዳይከሰቱ በመከላከልም በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ይታወቃል።

 

ቸር እንሰንብት!!

 

በሠራዊት ሸሎ