የሎጎ ሀይቅ መገኛው በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ነው። በሰንሰለታማ ተራሮች ውበትን የተላበስው ሀይቁ የመልክዓ ምድራዊ ገጽታው ዕይታን የሚማርክ ነው። ከደሴ ከተማ በስተ ሰሜን አቅጣጫ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ምርጥ የመስህብ ሥፍራ ነው።
የሎጎ ሀይቅ ከአዲስ አበባ 430 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከክልሉ ዋና ከተማ ባህር ዳር 470 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። በተሁለደሬ ወረዳ የሚገኘውን ይህንን ውብ የተፈጥሮ ሀይቅ በአቅራቢያው ከከተመችውና ሀይቅ የተሰኘውን ስያሜ ካገኘችው ከሀይቅ ከተማ 2 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ያገኙታል።
ሀይቁ ከባህር ወለል በላይ 1 ሺሕ 950 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ ሲሆን ስፋቱ 35 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍንና አማካይ ጥልቀቱ ደግሞ ከ23 እስከ 88 ሜትር እንደሚደርስ መረጃዎች ያመላክታል፡፡
የሎጎ ሀይቅ ለዕይታ ውብና ማራኪ ከመሆኑ ባሻገር በአካባቢው በዓሣ ምርት ይታወቃል። ቀረሶ፣ ዱቤና አምባዛ የሚባሉ የዓሣ ዝርያዎች በሀይቁ ይገኛሉ፡፡
የሎጎ ሀይቅ በዓሣ ማስገር ሥራ ለተሰማሩ ወጣቶችም የሥራ ዕድል በመፍጠር ብሎም ለህብረተሰቡ የገቢ ምንጭ በመሆን እያገለገለ ይገኛል።
የሞተር ጀልባዎችን ጨምሮ ለጎብኚዎች የትራንስፖርት እና የመዝናኛ አገልግሎት የሚሰጡ ጀልባዎች ያሉ ሲሆን መለስተኛ ሎጆች፣ ሆቴሎችና ካፊቴሪያዎችም በአካባቢው ስለሚገኙ ለጎብኚዎች ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ ነው።
ይህ በመልክዓ ምድራዊ ገፅታው ውበትን የተላበሰው የሎጎ ሀይቅ በአሁኑ ወቅት ወደ መልማት ተሸጋግሯል።
የተደበቁና ሀብት ሳያፈሩ የቆዩ የአካባቢ ፀጋዎችን በማልማት እና ወደ ሀብት በመቀየር የቱሪዝም ዘርፉ በኢኮኖሚ ውስጥ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ለማድረግ ያለመው የ”ገበታ ለትውልድ” አገራዊ ፕሮጀክት ለሎጎ ሀይቅም የመልማት ዕድሉን እነሆ ብሏል።
በዚህም የሎጎ ሀይቅ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሐሳብ አመንጭነት በ”ገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክት እየለማ ይገኛል።
ወደ ሥራ የገባው ይህ ማራኪው የተፈጥሮ መስህብ የሰው ጥረት ታክሎ እና ውበቱን ገልጦ ለትውልድ ተሻጋሪ ሀብት ለመፍጠር ጉዞውን ጀምሯል። ይህ ወሎና አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ታስቦ እየለማ የሚገኘው የፕሮጀክት ሥራ በአሁኑ ወቅት ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል።
ደቡብ ወሎ ዞን ሦስት የተለያዩ የተፈጥሮ ሀይቆች የሚገኙ ሲሆን በስፋት ትልቁ ሎጎ ሀይቅ ነው። ሌሎቹ ሁለቱ የተፈጥሮ ሀይቆች አርድቦ እና ማይባር ይባላሉ። ሎጎ እና አርድቦ ሀይቆች በተሁለደሬ ወረዳ የሚገኙ ሲሆን ማይባር ሀይቅ ደግሞ በአልብኮ ወረዳ ይገኛል። አርድቦ ከሀይቅ ከተማ በስተምስራቅ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ማይባር ሀይቅ ከደሴ ከተማ በስተደቡብ 23 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
ዞኑና አካባቢው የተፈጥሮ፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ሀይማኖታዊ መስህቦች መገኛ ሥፍራ መሆኑንም የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
እነዚህን እና በዞኑ የሚገኙ ሌሎች ውብ እና ማራኪ የመስህብ ሥፍራዎችን ይጎብኙ ሀገርዎን ይወቁ!! ቸር እንሰንብት!!
በሠራዊት ሸሎ