ሮቢን ቫን ፐርሲ የፌኑርድ እግር ኳስ ቡድንን ለማሰልጠን ተስማማ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀድሞው የአርሰናል እና ማንቼስተር ዩናይትድ ኮከብ ሮቢን ቫን ፐርሲ የሆላንዱን ፌኑርድ እግር ኳስ ቡድን ለማሰልጠን ስምምነት ፈረመ፡፡

ቫን ፐርሲ እስከ ፈረንጆቹ ሰኔ 2027 በሚቆይ የሁለት ዓመት ውል ነው ቡድኑን ለማሰልጠን የፈረመው፡፡

ስምምነቱን ተከትሎም የ41 ዓመቱ ቫን ፐርሲ የፌኑርድን ጊዜያዊ አሰልጣኝ ፓስካል ቦሻርት በመተካት የኤርዲቪዜውን ክለብ በዋና አሰልጣኝነት ይመራል፡፡

ቫን ፐርሲ ቀደም ሲል የፌኑርድ አካዳሚ አሰልጣኝ እና የዋናው ቡድን የአሰልጣኞች ስታፍ አባል የነበረ ሲሆን ቡድኑን በመልቀቅ በኤርዲቪዜው 9ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ሄርነቨንን በዋና አሰልጣኝነት ሲመራ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የልጅነት የእግር ኳስ ህይወቱን በፌኑርድ የጀመረው ቫን ፐርሲ የእንግሊዙን አርሰናል እስከተቀላቀለበት ድረስ ለሆላንዱ ክለብ 122 ጨዋታዎችን በማድረግ 46 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል፡፡