ህጻናት የሚባሉት በሳይንሳዊ ምደባ ዕድሜያቸው ከውልደት እስከ 12 ዓመት ያሉትን ልጆች ያጠቃልላል፡፡ እነዚህ ህጻናት ካላቸው አካላዊ ጥንካሬ ማነስና ካለማወቅ ለበርካታ አደጋ ተጋላጭ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው የቤተሰብ የቅርብ ጥበቃና እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው፡፡
ህጻናት በተደጋጋሚ ከሚያጋጥሟቸው አደጋዎች መካከል በእሳት ወይም በፈላ ውሃ መቃጠል፣ መውደቅ፣ መመረዝ፣ በስለት መቆረጥ፣ መታነቅ፣ በውሃ ውስጥ የመስጠም እና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ህጻናት ሊደርሱባቸው በሚችሉ ሁኔታ ወይም በአካባቢዎች የሚነድ እሳት ወይም የፈላ ውሃ ካለ ለአደጋ ተጋላጭ ናቸው፡፡ ጉዳቱን ስለማያውቁትና የሚነድ እሳት መልኩ ሊስባቸው ስለሚችል በቀላሉ ሊነኩት ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ልጆች በአካባቢያቸው ምን እንዳለ የመረዳት እና የጥንቃቄ እርምጃ ለመውሰድ ማመዛዘን ስለማይችሉ ለአደጋው ተጋላጭ ናቸው፡፡
ህጻናት በአካባቢያቸው ያገኙትን ነገር የመንካት፣ የመቅመስ ወይም የማሽተት አዝማሚያ አላቸው፡፡ መርዛማውን ነገር በነኩበት እጃቸው አፋቸውን ስለሚነኩ ሊመረዙ ይችላሉ፡፡
የኤሌክትሪ አደጋ ሌላው ህጻናት ላይ የሚከሰት አደጋ ነው። ልጆች በቤት ውስጥም ይሁን በመጫወቻ ስፍራዎች የተላጡ የኤሌክትሪክ ገመዶች ካሉ በቀላሉ አደጋ ሊደርስባቸው ይችላል፡፡
እድሜያቸው እስከ 4 ዓመት የሆኑ ህጻናት ያገኙትን ነገር ወደ አፋቸው የማስገባት አዝማሚ አላቸው፡፡ ወደ አፋቸው የሚያስገቧቸው ነገሮች ምግብ ነክና ምግብ ያልሆኑ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ህጻናት ምግብ ነኮቹን ነገር በልካቸው መጥነው መጉረስና ማድቀቅ ስለማይችሉ ሊያንቃቸው ይችላል፡፡
ህጻናት በመዋኛ ገንዳ፣ በመታጠቢያ ገንዳ ወይንም በሰፊ የውሃ ማጠራቀሚያ ቦታዎች የመስጠም አደጋ ያጋጥማቸዋል፡፡ በተለይ በቅርብ ሆነው የሚጠብቋቸው አዋቂዎች ከሌሉ እስከሞት የሚያደርስ አደጋ ሊገጥማቸው ይችላል፡፡
እንደ ቢላዋ፣ ምላጭ፣ መርፌ ወዘተ ሹልና ስለታም እቃዎች ለህጻናት መቆረጥና መቁሰል ዋነኛ መንስኤዎች ናቸው፡፡
በህጻናት ላይ አደጋ ከደረሰ በአስቸኳይ ከተቻለ ወደ ህጻናት ሃኪም ካልሆነም ወደ ማንኛውም ህክምና መስጫ ማዕከል መውሰድ ይገባል፡፡
የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎች
አደጋ እንዳይከሰት መከላከልና ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ቀላሉ፣ ምቹው፣ በአብዛኛው ወጭ የማይጠይቅና ተግባራዊ እርምጃ ነው፡፡ ህጻናትን ከላይ ከተጠቀሱትና ሌሎች በርካታ የአደጋ ዓይነቶች ለመጠበቅ በርካታ የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራት ልንወስድ እንችላለን፡፡
ከእነዚህ ውስጥ የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው፡-
- ለአደጋ አጋላጭና የአደጋ ምንጭ የሆኑ ነገሮችን ማስወገድ (ሹል፣ ስለታም፣ መርዛማ፣ ኬሚካሎች፣ ተሰባሪ ጥቃቅን መጫወቻ ነገሮች)
- የአደጋ መከላከያ እርምጃዎችን መውሰድ (አጥር ማድረግ፣ የኤሌክትሪክ ሽቦዎችን ማራቅና መሸፈን፣ መዝጊያና መሸፈኛ ማድረግ፣ መቆለፍ፣ አርቆ ማስቀመጥ ወዘተ)
- ከውሃ ጋር የተያያዙ ጥንቃቄዎች (ወለል እንዳያዳልጥ ማደረግ፣ ሻወርና መታጠቢያ ገንዳ አካባቢ ቁጥጥር ማድረግ፣ የመታጠቢያ ውሃ ሙቀትን መለካት እና ሌሎችም)
- ለልጆች ተስማሚ የመጫወቻ እቃዎች መጠቀም
- ህጻናትን ስለጥንቃቄ በዕድሜያቸው መጠን ማስተማርና ማለማመድ፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ