በሴቶች 1 ሺሕ 500 ሜትር የዓለም የቤት ውስጥ የሩጫ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አሸናፊ ሆኑ

መጋቢት 11/2014 (ዋልታ) በቤልግሬድ በ18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ የሩጫ ውድድር ምሽቱ 4:35 ላይ በሴቶች ምድብ የተደረገው የ1 ሺሕ 500 ሜትር ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ሶስት በመውጣት ድል ተቀዳጅተዋል።
በሰርቢያ ቤልግሬድ የተጀመረው 18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን ትላንት ምሽት በተካሄደ 1 ሺሕ 500 ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ 3 ደቂቃ ከ57 ሰከንድ ከ19 ማይክሮ ሰከንድ በርቀቱ የሻምፒዮናውን ክብረ ወሰን በመስበር አሸንፋለች።
አትሌት አክሱማዊት አምባዬ 4 ደቂቃ ከ2 ሰከንድ ከ29 ማይክሮ ሰከንድ ሁለተኛ ስትወጣ፤ አትሌት ሂሩት መሸሻ 4 ደቂቃ ከ3 ሰከንድ ከ39 ሰከንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች።
ኢትዮጵያ በ3000 ሜትር ሴቶች በአትሌት ለምለም ኃይሉ አማካኝነት የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች ሲሆን አትሌት እጅጋየሁ ታዬ ሶስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘቷ የሚታወስ ነው።
ውጤቱን ተከትሎ የሻምፒዮናውን የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ በሁለት ወርቅ፣ አንድ ብር እና ሁለት ነሐስ በድምሩ አምስት ሜዳሊያዎች በማግኘት በአንደኝነት እየመራች ነው።