በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰበታ ከተማ ድል ሲያስመዘግብ ባህርዳር ከተማ ነጥብ ጣለ

በቤትኪንግ  የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰበታ ከተማ ድል ሲያስመዘግብ ባህርዳር ከተማ ነጥብ ጥሏል፡፡

ረፋድ 4፡00 ላይ የተደረገው የባህርዳር ከተማ እና የጅማ አባጅፋር ጨዋታ 2 ለ 2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

በጨዋታው ጅማ አባጅፋሮች ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩ ሲሆን ተመስገን ደረሰ 14ኛው ደቂቃ ላይ ጅማዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ባህርዳሮች በፍፁም አለሙ እና በምንይሉ ወንድሙ አማካኝነት ሁለት ተከታታይ ግቦችን በማስቆጠር ጨዋታውን መምራት ችለው ነበር፡፡

38ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ደረሰ ያስቆጠራት ሁለተኛ ግብ ጅማ አባጅፈሮችን ከጨዋታው ነጥብ ተጋርተው እንዲወጡ አስችላቸዋለች፡፡

ቀን 9፡00 ላይ የተደረገው የሰበታ ከተማ እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ በሰበታ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ሰበታን በጨዋታው አሸናፊ ያደረገች ብቸኛ ግብ ዳዊት እስጢፋኖስ 78ኛው ደቂቃ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሯል፡፡

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገም ቀጥሎ ሲደረግ ረፋድ 4፡00 ላይ ወልቂጤ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ እንዲሁም ቀን 9፡00 ላይ ደግሞ ፋሲል ከነማ ከድሬዳዋ ከተማ ይጫወታሉ፡፡

በሄኖክ አስራት