በአፋር ክልል በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው

መጋቢት 13/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአፋር ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዕድሜያቸው ከአንድ ዓመት በላይ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት መስጠት ጀምሯል፡፡
የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አስቻለው አባይነህ ኢንስቲትዩቱ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልሎች እና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የኅብረተሰብ ጤና ስጋቶች ላይ የቁጥጥር እና ምላሽ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አራት ወረዳዎች በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ 674 ሰዎች የታመሙና ሰባት ሰዎች ደግሞ ለሞት በመዳረጋቸው በወረዳዎቹ 98 በመቶ የመጀመሪያ ዙር የኮሌራ ክትባት መስጠት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
በአፋር ክልልም የኮሌራ ወረርሽኝ ሊከሰት ይችላል ተብሎ በሚገመቱ የተመረጡና የተፈናቀሉ ዜጎች በሚገኙበት ስፍራ ከአንድ ዓመት በላይ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በዞን 1፣ 2፣ 4 እና 5 በ16 ወረዳዎች በአጠቃላይ ለ174 ሺሕ 780 ሰዎች እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡
የአፋር ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳሬክተር ዶክተር ፈረጅ ሬብሳ በበኩላቸው አሸባሪው ሕወሓት በከፈተው ጦርነት በርካታ ዜጎች መፈናቀላቸውን ገልጸው በትንፋሽ የሚተላለፉ፣ ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎች እንዳይከሰቱ ከሚደረጉ የመከላከል ሥራዎች አንዱ ክትባት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህም የኮሌራ ክትባት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የመጀመሪያ ዙር ሲሆን በቀጣይ የክትባት ሥርጭቱ በክልሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ክትባቱ ከመጋቢት 12 ጀምሮ ለተከታታይ ሰባት ቀናት እንደሚሰጥ ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡