በኢትዮጵያ በልብና በደም ቧንቧ በሽታዎች በቀን በአማካይ 170 ሰዎች እንደሚሞቱ ተገለጸ

መስከረም 19/2015 (ዋልታ) በኢትዮጵያ በልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች ምክንያት በየቀኑ በአማካይ 170 ሰዎች ለህልፈት እንደሚዳረጉ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዓለም ላይ በየዓመቱ በተለያዩ ምክንያቶች ከሚሞቱት ሰዎች መካከል 31 በመቶው በልብና ተያያዥ በሆኑ በሽታዎች ምክንያት እንደሚሞቱ መረጃዎች ይጠቁሟሉ::

የዓለም ጤና ድረጅት መረጃ እንደሚያመለክተው በዓለም ላይ በየዓመቱ በአማካይ 18 ሚሊየን ሰዎች በልብ ህመም ምክንያት ይሞታሉ።

የዓለም የልብ ቀን “ለሁሉም የልብ የጤና ልብ እንበል” በሚል መሪ ሀሳብ በኢትዮጵያ ለ7ኛ ጊዜ በዓለም ደግሞ ለ23ኛ ጊዜ በዛሬው ዕለት ተከብሯል፡፡

ልብ- ነክ በሽታዎች በዓለም ላይ በዋነኛ የሞት መንስኤነት የተቀመጡ ሲሆን በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ሁኔታዎች እየተስተዋሉ መምጣታቸውን ሚኒስቴር አመላክቷል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ የጤና የሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ሩት ንጋቱ በኢትዮጵያ የልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች ዋነኛ የሞት መንስዔ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች ምክንያት በየቀኑ በአማካይ 170 ሰዎች ለህልፈት እየተዳረጉ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ 45 በመቶው በልብ የደም ቧንቧ ጥበት፣ 34 በመቶው በስትሮክ እንዲሁም 11 በመቶ በደም ግፊት ለህልፈት የሚዳረጉ መሆኑን አብራርተዋል።

ለልብና ደም ቧንቧ በሽታዎች ከሚዳርጉ አጋላጭ መንስዔዎች መካከል ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ የደም ግፊት፣ የቤት ውስጥ አየር ብክለት፣ የደም ውስጥ ቅባትና የስኳር መጨመር መሆናቸው በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።

የአልኮል መጠጥ ማዘውተርና ሲጋራ ማጨስም ለዚሁ ህመም ዓይነተኛ ምክንያቶች መሆናቸው ይነገራል።

በሽታውን ለመከላከልም የአልኮል መጠጥና ሲጋራን መተው እንዲሁም የአመጋገብ ሥርዓትን ማስተካከል እንደሚገባ በባለሙያዎች ይመከራል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በሽታውን ለመከላከል ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ሩት ከ300 በላይ የጤና ተቋማት የደም ግፊት ልየታና ምርመራ ህክምና አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የዓለም የልብ ቀንን ምክንያት በማድረግም ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በነጻ የደም ግፊት ልኬትና መሰል አገልግሎቶች የሚሰጡ መሆኑን መግለጻቸው ኢዜአ ዘግቧል።