በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ ዚምባቡዌን 1 ለ 0 አሸነፈች

ጳጉሜ 02/2013 (ዋልታ) ለ2022 የኳታር የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ዚምባቡዌን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አስቻለው ታመነ በፍፁም ቅጣት ምት ብቸኛዋን ግብ አስቆጥሯል።

ትናንት ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ ሰባት በተደረገው ጨዋታ በተመሳሳይ ደቡብ አፍሪካ ጋናን 1 ለ 0 ማሸነፏ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከጨዋታው በፊት “አሸንፈን ድላችንን ለኢትዮጵያ ህዝብ የአዲስ አመት ስጦታ ማደረግ አለብን” የሚል መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

በ10 ምድብ ተከፍሎ የሚካሄደው የአፍሪካ(የካፍ) ዞን የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ከየምድቡ አንደኛ ሆነው የሚያልፉ 10 አገራት በሚወጣላቸው እጣ መሰረት እርስ በእርስ በሚያደርጉት የደርሶ መልስ ጨዋታ በአጠቃላይ ድምር ውጤት የሚያሸንፉ አምስት አገራት ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ ያልፋሉ።