የቦረና ሳይንት ወረሂመኖ ብሄራዊ ፓርክ የተቋቋመው በ2001 ዓ.ም ሲሆን በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የሚገኝ ድንቅ የመስብ ሥፍራ ነው፡፡
ፓርኩ በተለያዩ ሥነ ምህዳር የተከፋፈለ ከመሆኑ የተነሣ የተለያየ አየር ጸባይ የሚመቻቸው የዕጽዋት እና የዱር እንስሳት መኖሪያ ነው፡፡ ከባህር ጠለል በላይ ከ1ሺሕ 900 እስከ 4ሺሕ 280 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ የብዝሃ ተፈጥሮ ማህደርም ነው።
ደጋና ወይና ደጋ የአየር ንብረት ያለው፣ በጥብቅ የተፈጥሮ ደን ሽፋኑ የሚታወቅ፣ የብርቅዬ እንስሳት መኖሪያ፣ የብዙ ወንዞች መገኛ እንዲሁም ዓይንን በሚማርኩ ኮረብቶች ያጌጠ ውብ ፓርክ ነው።
የተለያዩ ወረዳዎችን የሚያካልለው ፓርኩ 15 ሺሕ 262 ሄክታር የሚሸፍን በአራት የሥነ ምህዳር ቀጣናዎች የተከፋፈለ ድንቅ የተፈጥሮ መስህቦች ያለበት የቱሪዝም መዳረሻም ነው የቦረና ሳይንት ወረሂመኖ ብሄራዊ ፓርክ።
ከዚሁ ፓርክ የሚመነጩ ወንዞች ወደ 30 የሚጠጉ ሲሆን ክረምት ከበጋ ሳያቋርጡ የሚፈሱ እና የአባይ ገባሮችም እንደሆኑ የተለያዩ መረጃዎች ይነግሩናል።
በቦረና፣ መሃል ሳይንት፣ አማራ ሳይንት፣ መቅደላ፣ ተንታና ለጋምቦ ወረዳዎች የተከለለው ባለብዙ ፀጋ ፓርክ የዕፅዋት፣ የእንስሳት እና አእዋፍ ክምችት ያለበትም ነው።
ሀገር በቀል ጥብቅ የተፈጥሮ ደን መገኛ እና 496 የእጽዋት ዝርያ የሚገኝበት ነው። ከነዚህም ውስጥ 12ቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡ ዋርካ፣ ወይራ፣ አስታ፣ ጓሳ፣ ዋንዛ፣ ጨረፌ፣ አሸንዳ አልባ አምጃ፣ ጅብራ እና ሌሎችም በፓርኩ ውስጥ ከሚገኙት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
23 አጥቢ የዱር እንስሳትንም አቅፎ ይዟል። ከእነዚህ ውስጥ 5ቱ በኢትዮጵያ ብቻ ይገኛሉ፡፡ ነብር፣ ቀበሮ፣ አነር፣ ድኩላ ጉሬዛ፣ ሰሳ፣ ሚዳቋ፣ አውጭ እና አፍን የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ትልልቆቹ ብርቅየዎቹ ጭላዳ፣ የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮና የሚኒሊክ ድኩላ ሲሆኑ 2 ትንንሾቹ ደግሞ የስታርክ ጥንቸልና አርቪክነተስ አይጥ ናቸው፡፡ በተጨማሪም 77 የአዕዋፍ ዝርያዎች በውስጡ የሚገኙ ሲሆን 4ቱ ብርቅየ አዕዋፋት መሆናቸውን እና የሶረኔ ቆቅ፣ የአቢሲኒያ ድመት መሳይ፣ የአቢሲኒያ ግንደቆርቁር፣ ራስ ጥቁር ጩጨ መሆናቸውን ከአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን የማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ባለ ብዙ የሥነ ምህዳር እና የብዝሃ ሕይወት ማህደር የሆነው ብሔራዊ ፓርኩ በዕድሜ ጠገብ አገር በቀል ዛፎችም የተሸፈነ ውብ እና ማራኪ ገጽታ ያለው ነው፡፡
ፓርኩ ከአዲስ አበባ በመካነ ሰላም 461 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከደሴ ከተማ 196 ኪሎ ሜትር ተጉዘው የሚያገኙት ሲሆን ከመካነ ሰላም ከተማ ደግሞ በ18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያገኙታል፡፡
የቦረና ሳይንት ወረሂመኖ ብሄራዊ ፓርክን ይጎብኙ ሀገርዎን ይወቁ!
ቸር እንሰንብት!
በሠራዊት ሸሎ