ከተሞቻችን – አላማጣ

በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ የጣሊያን ወረራን ተከትሎ የተመሰረተችው አላማጣ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የምትገኝ ከተማ ስትሆን ቀደምት ስያሜዋ “ጀሀን ኢራ” ይባል እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።

“አላማጣ” ለሚለው የከተማዋ ስያሜ ሁለት መላምቶች ይቀርባሉ። አንደኛው “አላምጠህ ብላ” የሚል ከሁለት ወታደሮች ንግግር ከተወሰደ ሐረገ የመጣ ነው የሚል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከረጅም ጊዜ በኃላ ዝናብ ያዩ አባት መገረማቸውን ሲገልፁ “አላህ መጣ” ማለታቸውን ተከትሎ እንደሆነ ይነገራል።

ከአዲስ አበባ በስተሰሜን አቅጣጫ 595 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከራያ ቆቦ ቀጥላ የምትገኘው የአላማጣ ከተማ ከባህር ጠለል በላይ 1ሺሕ 564 ሜትር አማካኝ ከፍታ ሲኖራት ቆላማ የአየር ንብረት እና ሜዳማ መልከዓ ምድራዊ ተፈጥሮን ተላብሳለች።

አላማጣ ለንግድ እና ለመኖሪያ ምቹ ከመሆኗ የተነሳ ከከተማዋ አጎራባች ከሆኑ አካባቢዎች ማለትም ከኮረም፣ ከመኾኒ፣ ከራያ ቆቦ እና ሌሎችም ጋር ጠንካራ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር አላት።

የመተሳሰብ እና የአብሮነት ከተማ የሆነችው አላማጣ አሮጌ ገበያ፣ ኪዳና፣ ዓዲ ሐቂ እና ጤና ጣቢያ ከታወቁ የሰፈር ስያሜዎቿ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

የከተማዋ ግርማ ሞገስ የሆነው “ግራ ካሕሱ” ከአላማጣ ጥቂት ወጣ ብሎ የሚገኝ ተራራ ሲሆን በማራኪ ተፈጥሯዊ ገፅታው እንዲሁም ወደ ኮረም በሚወስደው ጠመዝማዛ እና አስቸጋሪ በሆነው የአስፓልት መንገድ ከብዙዎች ትውስታ አይጠፋም።

ራያ ግራንድ ሪዞርት፣ ማዕዛ ሆቴል፣ ማልዲዮር ሆቴል፣ ወርቅነሽ ሆቴል፣ ኢትዮጵያ ሆቴል፣ ራማ ሆቴል እና ሌሎችም ሆቴሎች በከተማዋ የሚገኙ ሲሆን በትምህርት ዘርፍ ደግሞ አላማጣ ቴክኒክ ኮሌጅን ጨምሮ ኢትዮ ሌንስ ኮሌጅ፣ ታዳጊዋ ሲኒየር ሁለተኛ ደረጃ፣ አላማጣ አንደኛ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተጠቃሾች ናቸው።

የውቦች እና ጀግኖች መፍለቂያ በሆነችው አላማጣ ከተማ ወንዶች በአምባር የሚታጠቁትን በቂቤ የጠቆረ አገልድም እና ትከሻቸው ላይ ጣል የሚያደርጉት ነጠላ እንዲሁም በቅቤ የቀላ በትራቸው ልዩ መገለጫቸው ሲሆን በአንፃሩ ሴቶች ባማረ ሹሩባ እና ቂቤ በጠገበው ቀሚሳቸው አምሮ መታየት የተለመደ ነው።

በዚህች ውብ ከተማ ተወልዳችሁ ያደጋችሁ እንዲሁም በተለያየ አጋጣሚ አይታችኋት ልዩ ትዝታን ያተረፋችሁ ትዝታችሁን አጋሩን።

መልካም ሳምንት!

በአዲስዓለም ግደይ