አብጃታ ሻላ ሀይቆች ብሔራዊ ፓርክ – በአእዋፍት ሀብት የታደለ ሥፍራ


#ሀገሬ

አብጃታ ሻላ ሀይቆች ብሔራዊ ፓርክ – በአእዋፍት ሀብት የታደለ ሥፍራ

በብዝሀ ህይወት ስብጥሩ የሚታወቀው የአብጃታ ሻላ ሀይቆች ብሔራዊ ፖርክ በኦሮሚያ ክልል የሚገኝ የቱሪዝም መዳርሻ ነው።

ፓርኩ ስያሜውን ያገኘው ከአብጃታና ሻላ ሐይቆች ሲሆን በብሔራዊ ፖርኩ ውስጥ አጥቢ የዱር እንስሳት፣ አእዋፍ እና የተለያዩ የዕፅዋት ዝርያዎች ይገኛሉ።

ግዙፉ ሰጎንን እና በክረምት ወቅት በውሃማ ሥፍራዎች ተሰብስበው በድምቀት የሚታዩ ፍላሚንጎዎች የፖርኩ መለያዎች መሆናቸው ይጠቀሳል።

ብሔራዊ ፓርኩ የሚታወቀው በአዕዋፋት ሀብት ሲሆን በፓርኩና በሐይቁ ዙሪያ 453 የአዕዋፍት ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 144ቱ ህልውናቸውን በሀይቁ ላይ ያደረጉ ናቸው፡፡ ፓርኩ አእዋፍን መጎብኘት ለሚፈልጉ ጎብኚዎች ተመራጭ እና ቀዳሚ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራ ነው።

በርካታ ዝርያ ያላቸው አዕዋፍ ፖርኩን መኖሪያ ከማድረጋቸውም ባሻገር አጥቢ እንስሳትም ይገኙበታል፡፡

በፓርኩ ውስጥ ከሚገኙ የዱር እንስሳት መካከል አጋዘን፣ የሜዳ ፍየል፣ ሚዳቋ፣ ከርከሮ እና ብራይሌ የሚጠቀሱ ናቸው።

887 ስኩየር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት እንዳለው ሚነገርለት ብሔራዊ ፓርኩ 482 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሆነው በሀይቆች መሸፈኑን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኘው የተፈጥሮ መስህቡ ከባህር ጠለል በላይ ከ1 ሺሕ 540 እስከ 2 ሺሕ 7 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ እና የተፈጥሮ ፍል ውሃም አለው።

ከአዲስ አበባ 210 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ፓርኩ በጎብኝዎች ከሚዘወተረው ላንጋኖ ሀይቅ ጎን መገኘቱ ለጉብኝት አመቺ ስፍራ ያደርገዋል።
የአብጃታ ሻላ ሀይቆች ብሔራዊ ፖርክን ይጎብኙ ሀገርዎን ይወቁ!!

ቸር እንሰንብት!!

በሠራዊት ሸሎ