ከአዲስ ዋልታ መፅሔት የተወሰደጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ከፍተኛውን የስልጣን ቦታ ከያዙ በኋላ ያደረጉትን ተግባራት እንደ አንድ ጋዜጠኛ በቅርበት ተከታትያለሁ፡፡ በሀገሪቱ የተካሄደውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ ኢኮኖሚያዊ መስኮች፣ ማኅበራዊ ጉዳዮች እና ፖለቲካዊ ዑደቶች በሪፎርም ስራዎች ተቃኝተዋል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ መጋቢት ወር ካስተዋወቀን አዲስ ነገር መካከል ‘’አዲስ-ወግ’’ የውይይት መድረክ ይጠቀሳል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የሚዘጋጀው ይኽው የውይይት መድረክ በየሩብ ዓመቱ እና በየወሩ የሚካሄድ ነው፡፡ እንደ ሀገር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የበቁ ባለሙያዎችና የመንግስት አካላት በ ’’አዲስ-ወግ’’ ተሰባስበው በጥልቀት ውይይት የሚያደርጉበት መረሀ ግብር ነው፡፡ በዚህ ጽሑፌ ውስጥ ቤተ መንግስቱ መግለጫ ብቻ በማውጣት ሳይወሰን፤ በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የመፍትሔ ሃሳቦችን ለማፍለቅና የሰለጠነ የውይይት ባሕል ለማዳበር የወሰዳቸውን ተነሳሽነቶች አለማድነቅ ንፉግነት እንደሚሆን እያሰብኩ፤ በአዲስ-ወግ ያሉ የ4 ኪሎ መልኮችን ባለፉት አምስት ዓመታት የግል ምልከታዬን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
‘’አዲስ-ወግ’’ ፎረም ኢትዮጵያ አስደናቂ የፖለቲካ ለውጦችን ባሳየችበት ዓመት መጋቢት 22 ቀን 2011 ዓ.ም በይፋ ተከፍቷል፡፡ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ 1ኛ ዓመት የለውጥ እንቅስቃሴን ከፖለቲካ፤ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች አንፃር ለመገምገም የተሰናዳ ነበር፡፡ እኔም በተገኘውበት በዚህ መድረክ ያስተዋልኳቸው ተሳታፊ ምሁራንና ባለስልጣናቱ የነበራቸው የውይይት መሻት አንዳች ስሜት ያስተጋባል፡፡ የኢትዮጵያ እውተኛ ዴሞክራሲያዊ ሽግግርን ለመደገፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት ከፊታቸው አነብብ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድንገት በተገኙበት ‘’አዲስ-ወግ’’ መድረክ ንግግር አድርገዋል፡፡ በወቅቱ ለተሳታፊዎች ባደረጉት ንግግርም ‘’አዲስ-ወግ’’ የውይይት መድረክን ሲገልፁት ‘’አዲስ ወግ’’ የተበታተነውን ሐሳባችንንና መንፈሳቸንን ከየመንገዱ ሰብስበን ወደ አንድ የጋራ ቤት የምናመጣበት አጋጣሚ ነው፡፡’’ ሲሉ ነበር የገለፁት፡፡ አዲስ ወግ ዛሬ ከአራት ዓመት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገለፁበት ዐውድ ልክ እናገኘው ይሆን? በኢትዮጵያ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ የተመሰረተው አዲስ ወግ የውይይት መድረክ የ4 አመት ጉዞን የለውጡን 5ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ እድልና ችግሮቹን እንመልከት፡፡
‘’አዲስ ወግ’’ ከፓለቲካ አንፃር ምን አስተዋወቀን?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጀመሪያው የአዲስ ወግ መድረክ ላይ በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስብራቶች መገለጫዎች ናቸው ያሏውን ነጥቦች አንድ በአንድ አንስተው ነበር፡፡ እነርሱም ቡድንተኝነት፤ ፅንፈኝነት፤ የጥላቻ ንግግር፤ ያለፈውን፣ የአሁኑን እና የወደፊቱን የሚያስተሳስር የጋራ መግባባት አለመፍጠር፤ የተገኙ አሁናዊ ድሎችን ግምት ውስጥ አለማስገባት እና በእውነተኛ ምርጫ ዲሞክራሲን ማረጋገጥ አለመቻል ሀገራዊ የፖለቲካ ስብራት መሆናቸውን ማብራራታቸውን አስታውሳለሁ፡፡
እነዚህንም ፖለቲካዊ ስብራቶች በሰለጠነ የውይይት ባህል ልንጠግናቸው የሚገቡ ናቸው በማለት ተናግረው ነበር፡፡ ታዲያ እነዚህን ፈተናዎች ለመወጣት ‘’አዲስ-ወግ’’ የውይይት ወድረክ አንዱ መሳሪያ መሆኑን የተገነዘብኩት ገና ያኔ ነበር፡፡ ታዲያ ባለፉት ዓመታት ፖለቲካዊ ስብራቶቻችን በ‘’አዲስ-ወግ’’ መድረክ ምን መልክ ነበራቸው? የሚል ጥያቄ ማንሳትን ወድጃለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፖለቲካዊ ስብራት ያሏቸው ነጥቦች ጽ/ቤታቸው በሚያዘጋጀው አዲስ ወግ እውን ተዳሰዋል? መድረኩ ሀገራዊ ግንዛቤ በማስጨበጥ የመፍትሔ አድማስ አሳይቶ ይሆን? የሚል ጥያቄ ለማንሳት እገደዳለሁ፡፡ ርዕሰ ጉዳዮቹን እናስታውስ! ዲሞክራሲያዊ ሽግግርና ህግ የበላይነት፤ በዲሞክራሲ ውስጥ አንድ እርምጃ ወደፊት፣ የ6ኛው ብሄራዊ ምርጫ አንድምታ፤ በአዲስ መንፈስ ጅማሮ-የመንግስት ምስረታ እና ሀገር ግንባታ፤ የህልውና እና ኢትዮጵያን የመታደግ ጥሪ እና ከጽንፈኞች መካከል ወርቃማውን አማካይ መፈለግ የሚሉት ናቸው፡፡ ከመጋቢት 22 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት አራት ዓመታት በአዲስ ወግ ትኩረት ያገኙት ርዕሰ ጉዳዮች የፖለቲካ ስብራቶቻችን አንጓ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ፈተናዎች ከፖለቲካ ስብራቶቻችን የሚመነጩ እንደሆነ ስለምገነዘብ፤ አዲስ ወግ መድረክ ለጉዳዩ በሰጠው ትኩረት ልክ ፖለቲካዊ ስብራቶቻችንን ለመጠገን እየተጠቀምንበት እንዳልሆነ ግን እገነዘባለሁ፡፡
በብዙ ምክንያት ከፖለቲካ አንፃር ውይይቶቻችን ግባቸውን መተዋል የሚል አተያይ የለኝም፡፡ አንዳንዴ የውስጥን ስሜት የሚገልፅ መሪ ሲገኝ ደስ እንደሚል ሁሉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይበታተኑ ሰብሰብ ብለው ጠንካራ ፓርቲ መፍጠር ይኖርባቸዋል ቢሉም፤ ዛሬም በስም ከምናቃቸው ይልቅ የማናውቃቸው ፓርቲዎች ቁጥር ብዙ ነው፡፡ ለምን? ፓርቲዎች አማራጭ ሀሳብ የላቸውም፤ አልያም ህብረትን ባለመፈለጋቸው ጥንካሬያቸውን አጥተዋል ወደሚል ድምዳሜ ይወስደኛል፡፡ ይህ ሁኔታም በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የተሻለ አማራጭና ተገዳዳሪና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ሳንመለከት የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ጉዳይ በኢትዮጵያ ጭራሽ የማይታሰብ የሆነ ይመስላል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ በምርጫው ከ90 በመቶ በላይ ፓርላማውን መቆጣጠሩን ስናስተውል፤ አዲስ ወግ ላይ የሚነሱ ሀሳቦች በፖለቲካ ገበያው ገዢ እንዳላገኙ እገነዘባለሁ፡፡ ለአብነት ምርጫን አነሳሁኝ እንጂ ዝቅ ስንል ሌሎችም ችግሮች መሰረታዊነታቸውን ሳይለቁ ቀጥለዋል፡፡ ፅንፈኝነት፤ ቡድንተኝነት፤ የጥላቻ ንግግር፤ የማህበራዊ ሚዲያ ምግባር አልባነት፤ ያለፈውን፣ የአሁኑን እና የወደፊቱን የሚያስተሳስር የጋራ መግባባት ያለመፍጠር ችግሮች ዛሬም አሉብን፡፡ የፖለቲካ ስብራቶቻችንን ባለፉት 4 ዓመት ባካሄድናቸው የአዲስ ወግ ውይይቶች አልጠገናቸውም፡፡ ይህም ገና የውይይትና የሀሳብ የበላይነትን የሚቀበል ልብና ትከሻ አላዳበርንም፡፡ አዲስ ወግ ከፖለቲካ አንፃር መን አስተዋወቀን? የኔ መልስ ‘’ምንም’’ ነው፡፡
‘’አዲስ ወግ’’ ከኢኮኖሚ አንፃር ምን አስተዋወቀን?
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኮሮናቫይረስ፤ በጦርነትና በተፈጥሮ አደጋዎች ክፉኛ ተፈትኗል፡፡ የእነዚህ ፈተናዎችን ለመቀልበስ አሻጋሪ ሐሳቦች በየጊዜው በአዲስ ወግ ተመክሮባቸዋል፡፡ ዘላቂ መፍትሄ የሚሹ የዋጋ ግሽበት፤ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የብድር አከፋፈልን የተመለከቱ ፖሊሲዎች፤ በንግድ ውስጥ ያሉ ማነቆዎችን መፍታትና የመንግስት ልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዞር የተደረጉት እንቅስቃሴዎች የአዲስ ወግ የውይይት አንኳር ነጥቦች ነበሩ፡፡ በዋናነት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ዋነኛ የአዲስ ወግ ትኩረት ሆኖ ተመልክቻለሁ፡፡ በእኔ ምልከታ የዋጋ ግሽበትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ዛሬም የኢኮኖሚው ፈተና ቢሆኑም፤ ማክሮ ኢኮኖሚው በየዓመቱ እድገት አሳይቷል፡፡
በሂደቱ ትልቅ ፈተና የነበረውን የዋጋ ግሽበት፤ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር ለመፍታት፤ መንግስት የግብርና ምርታማነትን እያሳደገ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ከአራት ጊዜ በላይ በተጋበዙበት አዲስ ወግ የውይይት መድረክ ላይ ማብራሪያ ሲሰጡ እንደነበረ ብዙዎች ያስታውሳሉ፡፡ በመንግስት እንደ መፍትሔ የተወሰደው የበጋ ስንዴ ምርታማነት መጨመር ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ ተደርጎ ተወስዶም ነበር፡፡ የግብርና ምርታማነትን ከማሳደግና የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንፃር በአዲስ ወግ የተንፀባረቁ የመፍትሔ አማራጮች ምን ውጤት አምጥተዋል የሚለውን እንመልከት፡፡
የበጋ መስኖ ስንዴ ከየት ወዴት?
ሀገራዊ የስንዴ የፍላጎት ክፍተት ለመሙላት በዝናብ የሚመረተው የስንዴ ምርታማነት ከማሳደግ ጎን ለጎን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በ2011 በጀት ዓመት 3500 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ በአዋሽ፤ ሸበሌ፤ እና ኦሞ ተፋሰስ ላይ በስፋት ተጀምሯል፡፡ በ2012 በጀት ዓመት በእነዚሁ ተፋሰሶች ወደ 20 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ በማስፋፋት ተመሳሳይ ምርታማነት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ በ2013 በጀት ዓመት ከእነዚህ ተፋሰሶች በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል 21 ዞኖች እንዲሁም በአማራ ክልል የቆጋ መስኖ መሰረተ ልማትን በመጠቀም በአጠቃላይ 117 ሺሕ ሔክታር መሬት በማልማት 3.8 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተመዝግቧል፡፡
በ2014 በጀት ዓመት 450 ሺህ ሔክታር መሬት በመስኖ፤ እንዲሁም 298 ሺሕ ሔክታር መሬት በበልግ ደጋፊ መስኖ በክልሎች በማልማት 24.5 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት ተችሏል፡፡ በ2015 በጀት ዓመት 1.3 ሚሊየን ሔክታር መሬት በመስኖ በማልማት 52 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ የማምረት ኢላማ ተጥሏል፡፡ ይህም የሀገር ውስጥ ፍጆታን ሙሉ በሙሉ ከማሟላት ባለፈ ለውጭ ንግድ ማቅረብ ያስችላል፡፡ ከላይ እንደምንመለከተው የስንዴ ምርታማነት በየዓመቱ አድጓል፡፡ ይኸው ጉዳይ የሚያሳየን የውይይት ሀሳቦች ገቢራዊ ሲሆኑ የሚያስመዘግቡትን ውጤት በተጨበጭ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ ወግ ከአንኳር ኢኮኖሚያዊ የውይይት ነጥቦች አንፃር መሰረታዊ ችግር ናቸው ያልኳቸውን ቀጥሎ ላቅርብ፡፡
ከውይይቱ ጀርባ
አዲስ ወግ ባለፉት 4 ዓመት መንግስት የፍጆታ ሸቀጦች ድጎማ ማድረግ እና ለመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ልዩ መብት መስጠት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ምክረ-ሀሳብ ቢያቀርብም፤ መንግስት በተቃራኒው የፍጆታ እቃዎችን ድጎማ እያነሳ የነበረባቸው ዓመታት ናቸው፡፡ ይኽው ጉዳይ የዜጎችን ኑሮ ይባስ እንዳከበደባቸው በግልፅ ታይቷል፡፡
እንደ አለማየሁ ስዩም (ፕ/ር) ያሉ የመስኩ ተመራማሪዎች መንግስት የአቅርቦት ሰንሰለቱን ለማሻሻል እና ለማሳጠር የተወሰዱ ሙከራዎች ማሻሻል፤ በገበያው ላይ መረጋጋትን እንደሚያመጣ በአዲስ ወግ መድረክ ላይ ሀሳቦችን ሰንዝረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬም የአቅርቦት ሰንሰለቱን ማሻሻል አልተቻለም፡፡ የአቅርቦት ሰንሰለቱ በደላሎች የሚጠለፍ በመሆኑ በቂ ምርታማነት የተመዘገበባቸው እንደ ስንዴ ያሉ ምርቶች ዋጋ ተመጣጣኝ አይደለም፡፡ ሲሚንቶ ሌሎችም ምርቶች በተመሳሳይ የአቅርቦት ሰንሰለታቸውን ለማሳጠር የተወሰዱ እርምጃዎች ያን ያህል ውጤት ሲያመጡ አልተመለከትኩም፡፡ የበጋ መስኖ ስንዴን በተመለከተ ይበልጥ ምርታማነታቸው በተረጋገጠ አካባቢዎች ብቻ ተግባራዎ ቢደረግ የተሸለ እንደሆነ በአዲስ ወግ የምሁራን ምልከታ ነበር፡፡ ነገር ግን ፖለቲካዊ አጀንዳ እስኪመስል ድረስ፤ የስንዴ ምርታማነት ባልተረጋገጠባቸው አካባቢዎች ሳይቀር በመዝራት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማስጎብኘት የነበረው እሽቅድድም ጤናማ አልነበረም፡፡ ከዚህ ይልቅ ክልሎች ከአካባቢያዊ መልከዓምድራቸው ሁኔታ በመነሳት የተሻለ ምርታማነትን በሚሰጡ ምርቶች ላይ ማተኮርን መዘንጋት የለባቸውም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ የበጋ መስኖ ስንዴ ስለተናገሩ ብቻ፤ ለሰሊጥ በተዘጋጀ እርሻ ላይ ስንዴ መበተን በእጅጉ ያስተዛዝባል፡፡ ሁሉም ክልሎች በአንድ ቦይ በተመሳሳይ አዝዕርት ከመፍሰስ ይልቅ፤ ቆም ብሎ አካባቢያዊ አቅምን ግምት ውስጥ ባስገባ ልማት ላይ ማተኮር ይሻለናል ባይ ነኝ፡፡ ሌላው አዲስ ወግ እንደ ከተማ ግብርና ባሉ ተግባራት ላይ ማህበረሰቡ እንዲሳተፍ መንገድ ቢያሳይም፤ ምግቡን ከጓሮው የሚሸፍን ማህበረሰብ ስለመፈጠሩ ግን እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ምግቡን ከደጁ የሚሸፍነው ቀርቶብን፤ የእለት ጉርሱን የሚደግፍ እንኳን ማግኘት ከባድ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ቅጥር ግቢ የሚገኙ ክፍት ቤታዎች የጎመንና ሰላጣ እንዲሁም የሽንኩርትና ድንች ማሳ ሆነው የተመለከትን ቢሆንም፤ ወረዳና ክፍለ ከተሞች ይህንን ተሞክሮ ወደ ታች አላወረዱም፡፡ ይህ የሚያሳየው በውይይት የዳበሩና የተሻሉ ሀሳቦችን ተቀብሎ ተግባራዊ የማድረግ ችግር መኖሩን ያሳያል፡፡ ምን አልባትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝቅ ብለው ጓራቸውን ሲያለሙ በተመለከትኩበት ዐይኔ ወረዳና ክፍለ ከተሞች በወጥነት አለማሰቀጠላቸው የሀሳብ ምንዱባን መሆናችንን ያሳየኛል፡፡ አዲስ ወግ የውይይት መድረክ ለኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሰፊ ሽፋን መስጠቱ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንዲኖረው ማድረጉ በ2014 በጀት አመት የ6.4 በመቶ እድገት የተመዘገበ ሲሆን በዘንድሮው 2015 በጀት ዓመት 7.5 በመቶ እድገት ይጠበቃል፡፡ እድገቱነወ ቀደ ልማት መቀየርና የማኅበረሰቡን ኑሮ መሻሻል መቻል ግን ትልቁ የቤት ሥራ ነው፡፡
‘’አዲስ ወግ’’ ከማህበራዊ አንፃር ምን አስተዋወቀን?
ማህበራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በአዲስ ወግ መድረክ በተነሱት ጉዳዮች ላይ የፃፉ፣ ያስተማሩ፣ የተመራመሩ እና የሰሩ ተወያዮች እና ተሳታፊዎች ለፖሊሲ አወጣጥ ግብአት የሚሆኑ ሀሳቦችን አቅርበዋል። ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ማህበራዊ ተቋሞቻችን ከዝግመተ ለውጥ ወደ ሚታይ ሪፎርም እንዲሸጋገሩ ሆኗል፡፡ መንግስታዊ ተቋማት ምቹ የስራ ከባቢን በመፍጠር ምቹ ሆነዋል፡፡ የተለያዩ መንግሥታዊ አስተዳደሮች ሳይገድቡ በፍትሃዊነት የሚሰሩ እና የህብረተሰቡን ተግባር የሚመሩ ጠንካራ ተቋማዊ ማዕቀፎችን እንዲዘጋጁ ‹ተቋም ግንባታ በኢትዮጵያ› በሚል ሀሳብ የተካሄደው አዲስ ወግ መድረክ የሆነ መነቃቃት እንደፈጠረ አልጠራጠርም፡፡
በሀገሪቱ አቅም ያላቸው ተቋማትን ለመፍጠር የሚያስችሉ ሀሳቦች ከአዲስ ወግ ተንፀባርቀው ተጨባጭ ውጤቶችን አመላክተዋል፡፡ ተቋማት ግንባታን ለማፋጠን የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ መስራት እንደ ተቀዳሚ ተግባር ተወስዷል፡፡ በጥቅሉ አዲስ ወግ የህዝብ አቅምን መጠቀም ሁለንተናዊ እድገትን እንደሚያፋጥን በማሳየቱ በኩል ውጤት አምጥቷል የሚል እምነት ቢኖረኝም፤ እንደ ትምህርት፤ ጤና እና ስፖርትና ባህል ልማትን የተመለከቱ የውይይት መድረኮች አለመዘጋጀታቸው ማህበራዊ ጉዳዮቻችን በአዲስ ወግ ችላ የተባሉ ያህል ይሰማኛል፡፡
የአዲስ ወግ ክፍተቶችና ቀጣይ ትኩረቶች
አዲስ ወግ ገና ሲጀምር ውይይቱ የሚሰናዳው በሶስት አይነት ቅርፆች ነበር፡፡ አንደኛው በየወሩ የሚካሄድ ሲሆን ወቅታዊ እርዕሰ ጉዳዮችን ይመለከታል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በየሩብ ዓመቱ የሚካሄድ ሆኖ፤ ጥቅል ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ያተኩራል፡፡ ሶስተኛው አዲስ ወግ የህዝብ ውይይት ሲሆን በክልል ከተሞች ህዝባዊ ውይይት የሚደረግበት መድረክ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ መድረኮች ወጥነት ያላቸው አለመሆናቸው በራሱ ትልቅ ክፍተት ነው፡፡ በአጠቃላይ ባለፉት 4 ዓመታት 20 የአዲስ ወግ መድረኮች ብቻ መካሄዳቸውን ታዝቤያለሁ፡፡ ምናልባትም የወጥነት ችግሩ ለመፈጠሩ ብዙ ምክንያቶችን መዘርዘር ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ወደ ከፍታ በሚደረግ ጉዞ ቁርጠኝነት፤ ፅናት እና ወጥነት ትልቅ ሚና እንዳላቸው አይሸሸግም፡፡
በእነዚህ ሶስት መመዘኛዎች መድረኩን ካየነው በአንድ አልያም በሁለቱ ፉርሽ ይሆናል፡፡ በየሩብ ዓመቱ የሚካሄደውም ብዙውን ጊዜ ወቅቱን ጠብቆ አይካሄድም፡፡ ወራዊውም በተመሳሳይ ወጥነት የለውም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እነዚህን ክፍተቶች በቀጣይ መፈተሸ ይኖርበታል እላለሁ፡፡ አዲስ ወግ የህዝብ ውይይት ለሁለተኛ ጊዜ በድሬዳዋ ከተማ ካካሄደ በኋላ በዛው የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ይህ መሆን ነበረበት የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምክንያቱም በየከተሞች ይካሄድ የነበረው አዲስ ወግ ህዝባዊ ውይይት ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ መንግስት በየደረጃው የሚገኙ የመልካም አስተዳደር፤ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጥያቄዎችን ለመፍታት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርለት በመገንዘብ ነው፡፡ አዲስ ወግ የህዝብ ውይይት ማህበረሰቡ ችግሮቹን በቀጥታ የሚናገርበት ዐውድ በመሆኑ፤ ህዝባዊ መድረኮች ወሳኝ ናቸው፡፡ሌላው የባለሙያዎች ምርጫ ብዙውን ጊዜ ለቤተ መንግስቱ ቅርብ የሆኑ አካላትን የመምረጥ ዝንባሌዎችም እንደ ክፍተት እወስዳቸዋለሁ፡፡
አዳዲስ አተያዮችን የሚያስመለክቱ፤ ሞጋች ሀሳቦችን የሚያነሱ ምሁራንን ካሉበት ማውጣት መድረኩን ይበልጥ ሳቢ ያደርገዋል እላለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ወሳኙ ነገር ቁጥጥር፤ ክትትልና ግምገማ ናቸው፡፡ ይሄን ስል የአዲስ ወግ ጠረንጴዛ ላይ የሚሰፍሩ ሀሳቦች የፖሊሲ ግበዓት መሆናቸውን፤ የመንግስት ትኩረት ማግኘታቸውን፤ የመንግስትን ክፍተት በግልፅ የሚያሳዩ ናቸው ወይ የሚለውን የሚከታተልና ገቢራዊነታቸውን የሚያረጋግጥ አካል ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለውም፡፡ ርዕሰ ጉዳዮች ከአንድ ቀን መነጋገሪያ ያለፈ ፋይዳ ከሌላቸው ቆም ብሎ ማሰብና ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጡ ማስቻል ይገባል ባይ ነኝ፡፡ የውይይቱ ቁምነገሩ ያለው እዚህ ጋር ይመስለኛል፡፡ በአዲስ ወግ የሚቀርቡ ምሁራንና የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ችግሮችን ደፈር ብሎ የመናገር ዝንባሌያቸው አናሳ መሆኑን ታዝቤያለሁ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የሚዘጋጀው አዲስ ወግ ጤና፤ ትምህርትና ባህልና ስፖርት በመሳሰሉ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይም ትኩረት ማድረግ ይኖርበታል እላለሁ፡፡
በተለይም በሀገራዊ ጉዳዮች የምሁራን ሀሳብ አመንጪነት እንዳለ ሆኖ፤ ማህበራዊ እሴቶችን መገንባት የሚያስችሉ ውይይቶች በክልል ከተሞችም አንዲካሄዱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅበታል፡፡ ማህበራዊ ስብራቶቻችን ሲጠገኑ የደበዘዙ ምስሎችን የማጥራት አቅም አላቸው፡፡ በዚህም የማህበረሰብ ተወካዮች ማህበራዊ እሴቶችን ለትውልድ የሚያስገነዝቡበት ዐውድ መፍጠር ለነገ አይባልም፡፡ እንዲህ አይነቱ የውይይት መድረክ ከ4 ኪሎ ተሸግሮ ክልላዊ መልክ ማስያዝ ይገባል፡፡ አዲስ ወግ ቀጣይነትና ወጥነቱን ማስተካከል ከተቻለ በሀሳብ የበላይነት የሚያምንና የውይይት ባህሉ የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር የሚያስችል ትክክለኛ ጎዳና ነው፡፡
መደምደሚያ! አዲስ ወግ ምን አለማመደን?
ሀገራዊ አጀንዳዎች በውይይት ፕሮግራም መምራት መቻሉ የተሟላ የጋራ ሀገራዊ አውድ ለመፍጠር ያሰችላል፡፡ ሁለንተናዊ እድገት ለማምጣት በፕሮግራም መመራት ሙሉ ተፈፃሚነት ያስገኛል፡፡ ማኅበራዊ ጉዳዮችን፣ ፖለቲካዊ ዑደቶችን ጨምሮ መረጃዎችን ወደ ጠረንጴዛ በማምጣት ለውይይትና ምክክር በሩን ክፍት ማድረጉ ያስመሰግነዋል፡፡ መንግሥት ብሔራዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ጥንካሬና ክፍተት በመለየት የመፍትሔ ሃሳቦችን በማፍለቅ ሀገራዊ አጀንዳ ሆነው እንዲተገበሩ የአዲስ ወግ ዐውድ መፍጠሩ የሰለጠነ የውይይት ባህል ለማዳበር የራሱ የሆነ በጎ አስተዋፅኦ አለው፡፡ በተለይም ከፖለቲከኞች በተሻለ የመስኩ ምሁራንን ማሳተፉ የሀገሪቱን መጻኢ ጊዜ ብሩህ ያደርገዋል የሚል መደምደሚያም ያስይዛል፡፡