ኢማክስ – ፈተናዎችን የሚያርመው ሶፍትዌር


#ቴክኖ_ቅምሻ

አሸናፊና ጓደኞቹ “ቀለም ሚዲያ” የተባለ ድርጅት በማቋቋም ለሀገር ፋይዳ ያላቸውን ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂ በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ድርጅቱ እስካሁን 35 ሶፍትዌሮችን ያበለጸገ ሲሆን አሸናፊና ጓደኖቹ ከሰሯቸው ሶፍትዌሮች መካከል በትምህርት ዘርፍ ችግር ፈቺ ያሉትን ኢማክስ የተሰኘ ፈተና ማረሚያ ሶፍትዌር ይገኝበታል፡፡

ሶፍትዌሩ የ6ኛ፣ 8ኛ ክፍል እና ሲኦሲን ማረም የሚያስችል ነው፡፡ በዘንድሮ ዓመትም ከ 2 ነጥብ 6 ሚልዮን በላይ የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ተፈታኞችን ውጤት ለማረም አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡

የቀለም ሚዲያ ቴክኖሎጂ ማናጀር ደሳለኝ ተስፋው እንዳሉት ኢንሳ በሀገር ውስጥ የበለጸጉ ሶፍትዌሮች ወደ ስራ ከመግባታቸው በፊት የደህንነት ፍተሻ ያደርጋል። ይህ ሶፍትዌርም ፍተሸውን አልፏል፡፡ ፈተናን ለማረም ይወጣ የነበረ ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን አስችሏል፡፡

ይህ ሶፍትዌር የቴክኖሎጂ ጥገኝነትን ሙሉ ለሙሉ አሟጦ ያስቀረ እና በራሳችን እንድንኮራ ያስቻለን ሶፍትዌር ነው ብለዋል፡፡

የቀለም ሚዲያ ቴክኖሎጂ የሶፍትዌር ባለሙያና መስራች አባል አሸናፊ ወልዴ የፈተና ባንኩ ኦላንይን ሲስተም አይደለም። ፈተናው ከመጀመሩ 1 ደቂቃ ቀደም ብሎ ወደ ኦላይን በማሰናሰል (ሲንክ በማድረግ) የሚፈተኑበት መሆኑን ገልጿል፡፡

ሶፍትዌሩ ከማረም በተጨማሪም ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሲሆን ኩረጃ ያለበት ትምህርት ቤት የት እንደሆነ፣ የሚያስቸግሩ ተማሪዎች፣ ፈጥነው የሚወጡ ወይም ጥሩ እየሰሩ ያሉ ተማሪዎችን ጨምሮ ሁሉንም ፈተና የሚሰጥበትን ማዕከል በሙሉ በሶፍትዌሩ ለመቆጣጠር ይቻላል፡፡