ኢትዮ-ሳይበር ታለንት ማዕከል ለሌሎች አፍሪካ አገራት ምሳሌ የሚሆን ነው – ሼክ መንሱር ቢን ሙሳላም

ግንቦት 25/2014 (ዋልታ) የዓለም ዐቀፉ የትምህርት ትብብር ተቋም ዋና ጸሃፊ ሼክ መንሱር ቢን ሙሳላም የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና መስሪያ ቤትን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝታቸው በአስተዳደሩ እየተሰሩ ያሉ ሀገር በቀል የሳይበር ቴክኖሎጂ ውጤቶችንና በሳይበር ደኅንነት ዘርፍ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊ ወጣቶች የማልማት ሥራን ጎበኙ ሲሆን ሥራዎቹና ተሞክሮዎቹ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ተምሳሌት ሊሆኑ የሚችሉ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡

ሼክ መንሱር በቴክኖሎጂ የተደገፈ ጥራት ያለው ትምህርትን በማቅረብ፣ በሳይበር ሉአላዊነት፣ በዲጂታላይዜሽንና በታለንት ልማት ዙሪያ በአፍሪካ ደረጃ እየተሰራ ያለውን ሥራ ለመመልከት የሚያስችላቸውን ጉብኝት አካሂደዋል፡፡

አፍሪካውያን በዜጎቻቸው የሚለሙ አገር በቀል የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ በመጠቀም የዲጂታል ሉዓላዊነታቸውን ማረጋገጥ ይገባቸዋል ያሉት ሼክ መንሱር ከዚህ አኳያ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የለሙና እየለሙ የሚገኙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ረገድ ለአህጉሩም ጭምር ተስፋ ሰጪ ናቸው ብለዋል፡፡

ኢመደአ በሳይበር ደኅንነት ዘርፍ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊ ወጣቶች በማልማት ረገድ የጀመረው ሥራ ከሳይበር ደኅንነት ውጪ በሌሎች ዘርፎች ላይም ለተሰማሩ ተቋማት ምሳሌ እንደሚሆን የገለጹት ሲሆን በሁሉም ዘርፍ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊ ወጣቶች እንዳሉና እነዚህን ማልማት እንደሚገባ መግለጻቸውን ከአስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡